ዛሬ በስሱ እንድሰብካችሁ ፍቀዱልኝ !
አውሮፓ ከተሞች አንዱ እግር ከጣለህ የሆነ ነገር ታያለህ፤ መንገድ ላይ ስትሄድ የደላቸው የጠገቡ ርግቦች ያጋጥሙሀል’፤ አጠገባቸው መድረስህን አውቀው መንገድ አይለቁልህም፤ ከመጤፍ ሳይቆጥሩህ፥ለቀማቸውን ወይም ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ፤ እንዳትረግጣቸው ርምጃህን ቆጥበህ ለመራመድ ትገደዳለህ፤
ቅዲስቲቱ ምድር ላይ ነህ፤ አንዲት ወፍ ከከረጢት ያመለጠ እህል እየለቀመች ነው፤ ድንገት ባቅራቢያው ዳናህን ከሰማች ብድግ ብላ ወደ እንጦጦ ብሄራዊ ፓርክ ታፈገፍጋለች፤ በወፎች አይን ስንታይ ጭራቆች ነን፤ ግን ያለ ምክንያት ነው?
አንድ ባለቤት አልባ ውሻ ባጠገቡ ካለፍህ ሽምቅቅ ብሎ ገለል ይላል፤ ይመግቡኛል ብሎ ሳይሆን ይደበድቡኛል ብሎ እንደሚያስብ ግልጥ ነው ፤ በከተማችን የእለት ዱላውን ሳይቀበል የሚውል ውሻ የለም፤ ድሮ ሰዎች የጎዳና ውሻ የሚደበድቡት “ሊጣችንን ደፋብን ከቅርጫው መደብ ላይ አንድ ጎድን መነተፈብን በሚል ሰበብ ነበር፤ አሁን አሁን ያለ ሰበብ ውሻና ድመት የሚነርት ነዋሪ ጥቂት አይደለም ፤ ለመዝናናት ወይም የቆረፈደ ክንዱን ለማፍታት ውሻ የሚደበድብ አለ ፤ ረሀቡን በአንቅልፍ ለማሳለፍ የተኛውን ውሻ ከመንገድ አፈንግጦ በወጣ ኮብል ድንጋይ የሚወግር አይጠፋም፤
በቀደም አንዱ ከሱቅ በር ላይ ተጎልቶ የሚቅም ጎረምሳ ባንድ ምስኪን ውሻ ላይ ድንጋይ ወረወረበት፤ ውሻው ከድንጋዩ ለማምለጥ ደመነፍሱን አስፋልት ለማቋረጥ ሲሞክር ከላይ የመጣ ታክሲ በጎማው እግሩን ዳጠው ! ውሻው እያነከሰ ያለቀሰው ለቅሶ!
ካዲስአበባ እምብርት እየራቅን ስንሄድ እቃ የሚያጉዋጉዙ ጋሪዎችን እናገኛለን፤ አንድ የጠወለገ ፈረስ ትልልቅ ጎማ ያለው ጋሪ ለመጎተት የሞት የሽረቱን ሲፍጨረጨር ታያለሽ፤ በጋሪው መአት የስሚንቶ ከረጢት ተከምሯል፤ ከስሚንቶው በተረፈው ቦታ ቡልኬት ተገጥግጦበታል፤ በዚያ ላይ ጋሪ ነጂው እንደ ፈርኦን ተኮፍሶ ፈረሱን በጅራፍ ያጠብሰዋል፤
በእንስሳት መገልገል አንድ ነገር ነው፤ በአንስሳት አለምክንያት መጨከን ሌላ ነገር ነው፤ የከተማው አስተዳደር የጋማ ፈረሶችን ያላግባብ የሚጨኑ፥ በግልጋሎታቸው ሳይሆን በስቃያቸው የሚደሰቱ ሰዎችን መቅጣት አለበት፤
ለመኖር እንስሳትን መግደል አለብን፤ ይህ የህይወት አንድ አሳዛኝ ግን አይቀሬ ገጽታ ነው፤ ከዚያ ባሻገር ለእንስሳት ርህራሄ የማሳየት ዝንባሌም አናጣም፤ የኢትዮጵያ ባህል ባንድ ገጹ ለእንስሳት መራራትን ያስተምራል፤ ድንግል ማርያም የተጠማ ውሻ እንዳጠጣች ሲነገረን አድገናል፤ ያገራችን የባላባት ወግ ፥ስለ ዝሆን ገዳዮች ጀብድ ባድናቆት የሚተርከውን ያህል ስለ”ቆቅ ማሪ አቦየ”ም ይተርካል፤
እኒህ አቦየ የዳግማይ ምኒልክ አያት የንጉስ ሳህለስላሴ አማች ነበሩ፤ ባንድ ወቅት አንድ ባላገር ቆቅ አጥምዶ እጅመንሻ አመጣላቸው፤ ለባላገሩ የሚገባውን ከሰጡት በሁዋላ ወደ ምኝታ ቤታቸው መስኮት ተራመዱ ፤ ማጀት ውስጥ ገረዶቻቸው ቢላዋ እየሳሉ ነው፤ አቦየ ቆቂቱን መስኮት ላይ አስቀመጡና “ደና ሰንብቺ “ አሉዋት፤ ወደ መጣችበት በረረች፤
ያገሩ ሰው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቦየን “ ቆቅ ማሪ አቦየ” ብሎ ባድናቆት ይጠራቸው ጀመር!
አለምክንያት በእንስሳት ላይ የመጨከንንነ ልማድ አስወግደን የመንፈስ ስልጣኔ ያለን ህዝቦች መሆናችንን እናሳይ !
