ቀጸላ ክፍሌ
ሰሞኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አክብሯል፡፡ በርካታ አባላቶችና ደጋፊዎቹ በተገኙበት 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ተከብሮ የዋለው በኢትዮጵያ አንጋፋው የፖለቲካ ድርጅት የኾነው ኦነግ እለቱን ማስታወስ ያስፈለገው በትግል ሂደቱ የወደቁትን ለማስታወስ፣ ትግሉ የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም እና መዳረሻውን ለማስታወስ እንዲረዳ ነው ተብሏል፡፡ በኦነግ የ50ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ከ20 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በመድረኩ ተገኝተው የአጋርነት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ኦፌኮ፣ ሕብር ኢትዮጵያ፣ ኢሕአፓ፣ መድረክ፣ አገው ሸንጎ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እና ቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በክብረ በዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር ግንባሩ የተመሠረተው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለዜጎች መብት መከበር መኾኑን ጠቅሰው ፓርቲው ሲመሠረት የነበረውን ፊውዳላዊ ሥርዓት ጨቋኝነት አውግዘዋል፡፡ እንደ አቶ ዳውድ ገለጻ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሥራቾችና በመጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው እንደ ማሞ መዘምር እና ባሮ ቱምሳ ያሉ መሪዎች በወቅቱ የነበረው ሥርዓት እንዲቀየር ተፋልመዋል፡፡
ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ስለግንባሩ ይህን ቢሉም ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ አካላት ግንባሩ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ‹‹አንዳች ፖለቲካዊ ድል ማስመዝገብ ያልቻለ ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አልፎም ግንባሩ እንደስኬት የሚያያቸው የጥላቻ ትርክቶችን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መጫኑን እንጂ ከዚያ በላይ የተራመደው ነገር ስለሌለ ስኬት ሊባል አይችልም በማለት ይተቹታል፡፡ በተለይም አንድን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ በእሱ ላይ በመዝመትና በሐሰት ትርክት ሀገሪቱን ለመናድ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የግንባሩ ሚና ምን እንደነበር የሚካድ እንዳልኾነም ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህ ማሳያነትም ግንባሩ ሕልው ኾኖ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ‹‹ጠላቴ›› ባለው ማኅበረሰብ ላይ በየጊዜው ያደረሳቸውን ግፍና ሰቆቃዎች ከፍ ሲልም የዘር ማጽዳት ተግባሩን ያነሳሉ፡፡
እነአርባ ጉጉ፣ ጋራ ሙለታ፣ አሁነኛው ወለጋና መሰል የክልሉ አካባቢዎች ምን ያህል ዜጎች በዚህ ግንባር እንደተጨፈጨፉም አባሪ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህ ግንባሩ የሚያወሳው 50 ዓመት፣ የዘለቀው ታላቅ የፖለቲካ ድል በማስመዝገብ ሳይኾን ሀገርና ሕዝብ ላይ ጥላቻን በመንዛትና ንጹሐንን በመጨፍጨፍ መኾኑን ያሰምሩበታል፡፡ ከዚህ አንጻር ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በተለይ በንጉሣዊው ሥርዓት ጊዜ የነባሮ ቱምሳው ኦነግ ‹‹ሥርዓቱን ታግሏል›› ይሉት ተረክ ከእውነት የራቀ ኾኖ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም የንጉሡን ሥርዓት ታግለው የገረሰሱት ድፍን ኢትዮጵያውያን እንጅ እንደኦነግ ዓይነት የወቅቱ እንጭጭ ድርጅቶች እንዳልኾነ የሚታወቅ በመኾኑ ነው፡፡ ኦነግም ኾነ ማናቸውም የወቅቱ ድርጅቶች አቅም አልባ በመኾናቸው ሥልጣነ መንበሩን ወታደሩ ጠልፎ እንደወሰደው ማንም አይዘነጋውም፡፡ በወቅቱ አቅም ያለው ድርጅት ቢኖር ኖሮ ከየካቲት እስከ ነሐሴ 1966 ዓ.ም ያሉ ስድስት ወራትን ተጠቅመው 50 ዓመትም ይሁን 17 ዓመት ሳይታገሉ የሻቱለትን የፖለቲካ ጥያቄ ባሳኩ ነበር፡፡
የኾኖ ኾኖ አቶ ዳውድ፤ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር እዚህ መድረስ እና በትግሉ ለመጣው የባሕል-ማንነት ውጤት በትግሉ የወደቁት ሊታወሱ እንደሚገባ ጠቁመው አሁን ላይም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ይደርሳል ያሉት የሰላም እጦት እና ወከባ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አሁን በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሊቆም ይገባል፡፡ ትልቁ የዚህ አገር ችግር የዜጎች መብት፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ በጋራ ተቀምጦ አለመወያየት ነው፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ሌሎች አጋር የፖለቲካ ድርጅቶችም ለዚሁ ቢጥሩም ሰሚ በማጣታችን ነው ወደ ማንወጣው ጦርነት የገባነው፡፡ አሁን ጊዜው ቆም ብለን ስለዚህ የምናስብበት ነው›› ሲሉ አሁናዊ የክልሉን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹የኦሮሚያው ጦርነት መልሰን መላልሰን እንደተናገርነው፤ ኢትዮጵያን በኦሮሚያ ላይ በኃይል ለመጫን ያላትን ፍላጎት ያሳያል፡፡ ጦርነቱ ኦነግን ሰብሮ የራስን ፍላጎት እውን የማድረግ ፍላጎት የሚጎላበት ነው፡፡ እየተካሄደ ያለው ጦርነትም ይህ አይኾንም የሚል አንድምታ አለው፡፡ ግን ሁሉም ሊገነዘብ የሚገባው በጦርነት መፍትሄ አይመጣም፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄ መምጣት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ይህ ጦርነት መቆም አለበት፡፡ በኦሮሚያ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ በቻልነው መጠን እንሰራለን›› ብለዋል፡፡
ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በዚህ ንግግራቸው በክልሉ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ‹‹ኢትዮጵያን በኦሮሚያ ላይ በኃይል ለመጫን›› ሲባል እንደኾነ አመላክተዋል፡፡ እውነታው ግን ድርጅታቸው ኦነግ የሚታገልለት ዓላማ በተግባርም እንደሚታየው አንድም ከተሳካ ኦሮሚያን በኢትዮጵያ ላይ መጫን አልያም ካልተሳካ የራስን እድል በራስ ለመወሰን ነው፡፡ ለእነዚህ ሁለት ዐበይት ተግባራት መሳካት በየጊዜው የተለያዩ ድጊቶችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው አልፎም የልሂቃኖቻቸውና የፖለቲከኞቻቸው ፍላጎትና ጥያቄ እነዚሁ ነጥቦች እንደኾኑ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ መደመጡ አይዘነጋም፡፡ በግልጽ በግዴታ ‹‹ቋንቋዬን ተናገሩ፤ ባሕሌን ባሕላችሁ አድርጉ፤ ሀገሪቱ እኛን መምሰል አለባት›› ወዘተ የሚሉ ቃላት የሚደመጡት እርሳቸው ከሚመሩት ጎራ እንጂ ከሌላ እንዳልኾነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ኦቦ ዳውድ በየት በኩል ዞረው ‹‹ኢትዮጵያን በኦሮሞ ላይ ለመጫን›› የሚል ትችት ለማንሳት እንዳስቻላቸው አስቸጋሪ ነው፡፡
በሌላ በኩል የኦቦ ዳውድ ኢብሳ ድርጅት አሁን ጦርነት ላይ የሚገኘውና ራሱን ‹‹የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት›› ብሎ የሚጠራው ቡድን እንደማይወክለው ገልጾ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደምም በኦሮምያ ክልል ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰው አሁን ላይ ግን አብዛኞቹ እንደሌሉ እና እንደከሰሙ ገልጸዋል፡፡ አክለውም በአሁኑ ሰዓት በክልሉም ኾነ በሃገሪቷ ውስጥ ከሚመለከተው አካል ሕጋዊ ፍቃድ ወስዶ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በኦቦ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው እና ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ለኦሮሞ ነጻነት እና እኩልነት የታገለው ኦነግ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከዛ ውጪ በፓርቲው ስም የሚንቀሳቀሱም ኾነ የሚጠሩ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርቲው ምንም ዓይነት እውቅና ያልተሰጣቸው መኾናቸውን አስረድተው ነበር፡፡
ራሳቸው ኦቦ ዳውድ ኢብሳም ‹‹የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር አሁን ላይ ግንኙነት አለው ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ ‹‹ያ ሠራዊት የፖለቲካ ጥያቄ ያለው ሠራዊት ነው፡፡ አባላቶቹን ለምን እንደሚታገል አስተምሮ ነው ወደ ጦር የሚያሰማራው፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ደግሞ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ይህን ትግል በሰላማዊ መንገድ እያካሄደ ነው፡፡ ይህ መንግሥት አለመግባባቱ በተፈጠረ ጊዜ ኦነግን ገመድ ውስጥ አስገብቶ ሁለት ጥያቄዎችን ነው የጠየቀው፡፡ ትጥቅ አልፈታም ያለው ያ ሠራዊት የኔ ነው ወይስ አይደለም እንድንል፡፡ በወቅቱ ከአባገዳዎች ጋር ኾነን በኦሮሞ ባሕል ማዕከል ባደረግነው ጉባኤ መንግሥት ስምምነቱን አፍርሷል ብለን በማመናችንና ጦሩን ማስገባት ሥርዓት ስላለው እኛ በወቅቱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለአባገዳዎች ሰጥተን ነው ከመሐል የወጣነው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከጦሩ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡” ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
ይህ በኾነበት ሁኔታ ግን ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ‹‹ጦርነቱ ኦነግን ሰብሮ የራስን ፍላጎት እውን የማድረግ ፍላጎት የሚጎላበት ነው›› ሲሉ መደመጣቸው ‹‹ወዴት ወዴት?›› የሚያሰኝ ነው፡፡ ሠራዊቱ ያነገበው የፖለቲካ ጥያቄ እነርሱ ከሚያነሱት የፖለቲካ ጥያቄስ የሚለየው ‹‹በምን ይኾን?›› የሚለው አወዛጋቢ ነው፡፡
