‹‹ከተማዋ ከ81 ቢሊየን ብር በላይ ለኢንቨስትመንት ፈሰስ ተደርጎባታል››

Date:

አቶ አሰግደው ሽመልስ

በቅርቡ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ በኾነችውና የሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች ማዕከል እየኾነች በመጣችው ደብረ ብርሃን ከተማ ለዐሥር ያህል ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ይዘጋጃል፡፡ ኤክስፖው በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንት፣ በማዕድን፣ በሆቴል፣ በቱሪዝም እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሰማሩ አካላት የሚሳተፉበት እንደኾነ ነው የኤክስፖው የማስታወቂያ እና የሚዲያ ጉዳዮች አስተባባሪ የኾኑት አቶ አሰግደው ሽመልስ የሚናገሩት፡፡ ለመኾኑ ኤክስፖው ከዚህ ቀደም ሲዘጋጁ ከነበሩ መሰል ኤክስፖዎች ምን የተለየ ነገር አለው? ደብረ ብርሃን ከተማስ እንዴት ተመራጭ ልትኾን ቻለች? ኤክስፖው ዓለም ዓቀፍ ከመኾኑ አንፃር ለውጭ ኢንቨስተሮች ምን የተለየ ነገር ተዘጋጅቷል? የሚሉትንና ሌሎችንም የዝግጅት ክፍላችንን ጥያቄዎች አቶ አሰግደው ሽመልስ እንደሚከተለው መልሰዋል፡፡ እንኾ! 

ግዮን፡- ራስዎትን ለአንባቢያን ቢያስተዋውቁ?

አሰግደው፡- አሰግደው ሽመልስ እባላለሁ፡፡ በኤክስፖ 2023 ከፕሮሞተሮቹ አንዱ ነኝ፡፡ አጠቃላይ የፕሮሞሽንና የሚዲያ ጉዳዮች አስተባባሪ ነኝ፡፡

ግዮን፡- የኤክስፖው መርሐ ግብር ዝግጅት ለስንት ቀናት የሚቆይ ነው?

አሰግደው፡- ኤክስፖው ከጥር 4 ቀን እሰከ 14/2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲኾን የሚቆየው ለ10 ቀናት ነው፡፡ በዚህ ኤክስፖ ውስጥ በዋናነት የተካተቱት አራት ቁልፍ ኹነቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኢንዲስትሪዎችና ኢንቨስተሮች በአገልግሎት ዘርፍ፣ በአምራች ኢንዲስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ እንዲሁም በመሰል ቱሪዝምና ሆቴል ዘርፎችን ጨምሮ በቴክኖሎጂ የተሰማሩ ባለሀብቶች፤ ተቋም በተቋም የሚያደርጉት ግኑኙነትና ትብብርን በሃገራችን ለማዳበር መሥራት ነው፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ልምድ እንዲያወርሱ የሀገር አቀፍ ተቋማት ደግሞ የሚማሩበት፣ የንግድ ትስስር የሚያደርጉበት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ትስስር የሚፈጥሩበት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ኤክስፖዋችን ለፋይናንስ ተቋማት ግብዣ አድርጓል፡፡ ግብዣው በዋናነት ባንኮች ብድርና ቁጠባ ተቋማት ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር ተጣምረው በኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ክፍተት የሚሞሉ እንዲኾኑ ማድረግን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡ ድጋፍና ብድር መሠል ተጓዳኝ ተግባራትን አብረው መሥራት የሚችሉበትን ማዕቀፍ ለመፍጠርም ተሞክሯል፡፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የኢንቨስትመንቱ ማኅበረሰብ ከኢንዱስትሪ ተቋማት ጋር አብሮ እንዲሠራ የተዘጋጀ ኤክስፖ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ወረዳ፣ ዞኖች፣ ከተሞች፣ ክልሎች አቅሞቻቸውን በአንድ መድረክ ውስጥ በማድረግ የየአካባቢያቸውን ጸጋ እንዲያስተዋውቁ እና ኢንቨስተር እንዲጠሩ የጋራ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ትልም እንዲኖረንና አልፎም በጋራ መሥራትን እንድንለምድ የሚያስችል የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ፈጥረናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችና ማኅበራት ከኢንቨስተሮችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አብረው መሥራት የሚችሉባቸው ማዕቀፎች ለመፍጠር እና እንዲሳተፉ ለማድረግ ግብዣና ጥሪ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ኤክስፖው የልምድ ልውውጥ የሚደረግበትና አዳዲስ ሐሳቦች የሚፈልቁበት ነው፡፡

ግዮን፡- በኤክስፖው ምን የተለየ ፕሮግራም ተይዟል? በ10 የኤክስፖው ቆይታ ቀናት ውስጥስ በየዕለቱ የታቀደ ፕሮግራም አለ?

አሰግደው፡- በኤክስፖው የኢንቨስትመንት ሴሚናር አዘጋጅተናል፡፡ የኢንቨስትመንት ሴሚናሩ በዋናነት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በምን መልኩ ተሳስሮ ሊቀጥል ይገባዋል? በምን መልኩስ አዲስ የሥራ መስክ መፍጠር አለብን? እንዴት ዓይነት ሥራዎችስ መሠራት አለባቸው? የሚለውን እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች የገጠሟቸው ፈተናዎችና ያሏቸው እድሎች አልፎም የፋይናንስ ተቋማት ለኢንቨስትመንት ያላቸው ሚና ምንድነው? በሚለው ላይ አንድ አምስት ጽሑፎች በዓለም አቀፍ እንግዶች ይቀርባሉ፡፡ ከመክፈቻው ዕለት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ሰፊ የኾነ ዓለም ዓቀፍ ውይይት /ዲያሎግ/ ይካሄዳል፡፡ በቀሪዎቹ ተከታታይ ቀናት ደግሞ ከዋናው ፕሮግራም ጎን ለጎን የተለያዩ ትርኢቶች ይቀርባሉ፡፡ ወጣቶች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ያሳያሉ፡፡ በኤክስፖው የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ማኅበረሰቡ እና መላው ኢትዮጵያውያንና ሚዲያዎች ይሳተፉበታል፡፡

ግዮን፡- ከኤክስፖው ትልቅነት አንጻር ከአዲስ አበባ ይልቅ ደብረብርሃን ከተማ እንዴት ለዚህ ኤክስፖ ተመራጭ ልትኾን ቻለች ?

አሰግደው፡- ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ከመኾኗም በተጨማሪ በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የምትገኝ ከተማ በመኾኗ ነው፡፡ የሪጂዮፖሊታን የከተማ ደረጃን በማሳካቷ እና በሁሉም ዘርፍ መልካም የኢንቨስትመንት አቀባበል በመኖሩ እና በመሰል ምክንያቶች ደብረብርሃን ከተማ ለኤክስፖው ተመራጭ ልትኾን ችላለች፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተማዋ ምቹ አየር ጸባይ፣ በርካታ ተቋማት የግብይት ግብዓትን የሚያገኙባት በመኾኗ እንዲሁም ለገበያና ለትራንስፖርት አመቺ በመኾኗ አልፎም ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያለባት ከመኾኗ አኳያም ነው፡፡ ከተማዋ በዓመት እስካሁን ባለው የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ81 ቢሊየን ብር በላይ ፈሰስ የተደረገባት ነች፡፡ ከሌሎች ከተሞችም በተሻለ የኢንቨስትመንት ልምድ ስላላት ኤክስፖውን ለማዘጋጀት ተመርጣለች፡፡   

ግዮን፡- በመክፈቻ ንግግሩ ላይ እነማን በእንግድነት ይገኛሉ? እነማንስ ተጋብዘዋል?

አሰግደው፡- የሀገሪቱ ትልልቅ የፌደራል ባለሥልጣናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች፣ ከ20 በላይ የኢንባሲዎች አምባሳደሮች፣ የአማራ ክልል የካቢኒ አባላትም በሙሉ ይገኙ ዘንዱ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ የቢዝነስ ሰዎች፣ የኪነጥበብ ሰዎችና ሌሎችም ይገኛሉ ብለን እናምናለን፡፡

ግዮን፡- ከዚህ ቀደም ከተዘጋጁ ኤክስፖዎች የእናንተ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው? ከቀድሞዎቹ ኤክስፖዎችስ የወሰዳችሁት ልምድ አለ?

አሰግደው፡- እስካሁን ሲካሄድ የነበረው ይህን መሰል ትርኢት በሁለት መልኩ የሚገለፅ ነው፡፡ ይኸውም አንዱ ባዛር እና የንግድ ትርኢት የሚባል ሲኾን በዋናነት ሸማችና ሻጭን በማገናኘት የሚካሄድ የችርቻሮ ግብይት ሂደት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኤክስፖ ተብሎ በውስን ነገሮች ላይ የሚያጠነጥን ዝግጅት ነው፡፡ ለምሳሌ የማዕድን ኤክስፖ፤ የሆቴል ኤክስፖ፤ የግብርና ኤክስፖም ሊኾን ይችላል፡፡ አሁን የሚካሄደው ኤክስፖ ግን ከእነዚህ ይለያል፡፡ በመጀመሪያ እንዳለፉት ውስን ኤክስፖዎች በሆቴሎች ተዘጋጅቶ በሁለትና ሦስት ቀናት ብቻ የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ሲቀጥል ኤክስፖው በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ የተዘጋጀ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ በመኾኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ወሳኝ የሚባሉት ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ በመኾኑ ነው፡፡ እነዚህ ወሳኝ አካላት ሀገር አቀፍና አልሚ ባለሀብቱ፣ የፋይናንስ ተቋማት እንደ ባንክ ያሉት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ልማት ባንክ ጨምሮ ከ8 በላይ የሚኾኑ ባንኮች የዚህ ኤክስፖ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ኤክስፖው በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን፣ ከተሞች፣ ዞኖችና ክልሎችንም በአንድ ላይ አጣምሮ የሀገርን ኢኮኖሚና ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሳይ ነው፡፡

ግዮን፡- ከጸጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከፌደራል መንግሥቱስ ጋር ምን ዝግጅት አድርጋችኋል?

አሰግደው፡- የጸጥታ ችግር በሚመለከት ከጥቂት ወራት በፊት ከጉዞ ደህንነት አንፃር ችግሮች ነበሩ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ስር በሚገኙ እንደ ሸኖ፣ አሌልቱ እና መሰል ከተሞች ላይ አንዳንድ እንግልቶች ነበሩ፡፡ ይህ ማለት ግን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አቋም ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህን መሰል ችግር የተፈጠረው በአንዳንድ ልዩ ተልዕኮ ባላቸው የጸጥታ አካላት ነው፡፡ ይህን በተመለከተ የፌደራል መንግሥትና ክልሉ በመነጋገር አቅጣጫ ተቀምጦለት ችግሩ ተፈቷል፡፡ አሁን ላይ ከአዲስ አበባ እስከ ደብረብርሃን ያሉ ከተሞች ይህን ኤክስፖ በመደገፍ የጸጥታው ሥራ ላይ በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ አሁን ላይ እነዚህ ከተሞች ወረዳዎቻቸውም የኤክስፖው ተሳታፊ ስለኾኑ በማስተባበር ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ችግሮች በተፈጠሩበት ወቅት የነበሩ ተልዕኮ ተቀባይ አባላት አሁን የሉም፡፡ በዚህ መስመር ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ እጅግ ሰላማዊ የትራንስፖርት ፍሰት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ዓላማ እና ግብ ተይዞ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ቀጣይነት እንዲኖረው እየተሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም የሰላምና ደህንነት ተቋማት ስምሪት ወስደው እየሠሩበት ስለኾነ ምንም ዓይነት የፀጥታ ስጋት የለም፡፡

ግዮን፡- ኤክስፖው ዓለም ዓቀፋዊ ከመኾኑ አንፃር ከውጭ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ምን የተለየ ነገር አቅርባችኋል? 

አሰግደው፡- ከውጭ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች በዋናነት ጥሪውን ያስተላለፈው የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ የኢፌዲሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እውቅና በመስጠት፤ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ በሁሉም የኢትዮጵያ የቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች ጥሪውን በማድረግና በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ የከተማው ሕዝብም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የኤክስፖው ተሳታፊ አካላትን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ግዮን፡- ኤክስፖው ዓለም አቀፋዊ ከመኾኑ አኳያ በማስተዋወቅ በኩል ምን ምን ሥራዎች ተከናውነዋል?

አሰግደው፡- ኤክስፖውን በማስተዋወቅ በኩል በመጀመሪያ የተከናወነው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድረ-ገፅ የማልማት ሥራ ነው፡፡ “promote Ethiopia.com” የተሰኘ ይህንን ኤክስፖ የሚያስተዋውቅ ድረ-ገፅ ተዘጋጅቶ ይፋ ተደርጓል፡፡ ለዓለም የማስተዋወቁ ሥራ የተጀመረው በዚህ ድረ-ገፅ ሲኾን በርካታ መረጃዎችም በገጹ ላይ ታክለውበታል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ድረ-ገፅ የኦንላይን ምዝገባ እንዲቻል ተደርጓል፡፡ ከዚህ ድረ-ገፅ በተጨማሪም የተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች ለምተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከሀያ ሰባት በላይ ለሚኾኑ ሚዲያዎች አዲስ አበባ ላይ ጥሪ በማድረግ ስለ ዓለም ዓቀፍ ኤክስፖው ገለጻ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ ሚዲያዎች ውስጥ ከ6 በላይ የሚኾኑት የውጭ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በተለያየ መንገድም ከፍተኛ የኾነ የሚዲያ ንቅናቄ ተደርጓል፡፡ የተለያዩ ትላልቅ ማሕበራዊ አንቂዎችም ልዩ ልዩ ቅስቀሳን አድርገውበታል፡፡ አሁንም ሁሉም የክልልና የፌደራል ሚዲያዎች እንዲሁም የግል ሚዲያዎችንም/ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና ፕሬሶችን/ በመጠቀም ከፍተኛ ንቅናቄ እያደረግን ነው የምንገኘው፡፡ የዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ በተቻለ መጠን መረጃ ሊያገኝባቸው የሚችሉ በተለያዩ ቋንቋዎች ለምሳሌ በቻይንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣በፈረንሳይኛና በዐረበኛ ቋንቋዎች ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት መረጃውን ለማድረስ ተሞክሯል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናትም ከ7 ባላነሱ ሚዲያዎች ላይ የውል ስምምነት ወስደን ከፍተኛ የማስታወቂያ ንቅናቄ ለመፍጠር በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

ግዮን፡- ከዚህ ኤክስፖ በኋላ መሰል ኤክስፖ ታዘጋጃላችሁ? በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለም ይጨምሩበት?

አሰግደው፡- እንቅስቃሴያችን በዚህ ኤክስፖ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ 2021 ዓ.ም የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ሁኔታ እስካልተለወጠ ድረስ ለሚቀጥሉት 6 ዓመታት በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች ይህን መሰል ኤክስፖዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ለዚህ እቅድ ይዘን እየሠራን ነው፡፡ በዋናነት በጅማ፣ ድሬድዋ፣ ሐዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻ፣ አዳማን ጨምሮ አዲስ አበባ ላይ ይህን መሰል ኤክስፖዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ስለዚህ ሁኔታው በፈቀደ መጠን በጠቀስኳቸው ከተሞች በቀጣይ ደረጃ በደረጃ ይዘጋጃል፡፡ በጥቅሉ ይህ ኤክስፖ የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ኢትዮጵያውያን መጪው የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደኾነች እንዲያውቅና የዚያም አብሳሪ ኤክስፖ እንዲኾን እየተሠራ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም በዚህ መልኩ የተቀየሰ ኤክስፖ የማዘጋጀት እቅድ ተይዟል፡፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ይህን እንዲረዳ እንፈልጋለን፡፡   

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...