ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት እስከ መንግሥቱ ኃይለማርያም

Date:

የኢትዮጵያ መሪዎች በታዛቢዎች አንደበት!

አዳነ ጥላሁን ዳኜ (ወልድያ)

ክፍል2

ከንግሥት ዘውዲቱ ሞት በኋላ ከዙፋኑ ላይ ወጥተው ለ44 ዓመታት የቆዩት ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ናቸው፡፡ ተፈሪ ‹‹ኃይለሥላሴ›› በሚል የንግሥና ሥም ለረጂም ዓመታት ኢትዮጵያን አንቀጥቅጠው ገዝተዋል፡፡

በዐፄ ኃ/ሥላሴም ዙሪያ የታዛቢዎች አስተያየት የተለያየ ነው፡፡ ትምህርት እንዲስፋፋ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ከታህታይ እስከ ላዕላይ መዋቅሩ ያሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንዲዘምኑ ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ሀገሪቱም በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ ተገቢውን የክብር ቦታ እንድታገኝ ማድረጋቸውን፣ እርሳቸው ራሳቸው ጭምር ‹‹የአፍሪካ አባት›› እስከመባል መድረሳቸውን፣ ባጠቃላይ በሁሉም የልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ እንድትዘምን ያላሰለሰ ጥረት መፈፀማቸውን ይቀበሉና ነገር ግን አንድም ብልጣብልጥና ቂመኛ፣ ሲቀጥልም ከልክ ያለፈ የሥልጣን ሱስ ያሰከራቸው ስግብግብ፣ ሲሰልስም ከእርሳቸው ውጭ በሕዝብ አካባቢ ተወዳጅና ታዋቂነትን የሚያተርፍ ካለም የሚመቀኙ ቀናተኛና ግፈኛ መሪም ነበሩ ይሏቸዋል፡፡

ለሥልጣናቸው እጅግ ሰግብግብ ስለነበሩ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በሚዘጋጅበት ወቅት ዙፋናቸውን የማይነካባቸው ከሆነ ሀገሪቱን በሞግዚት አስተዳዳሪነት ሊሰጡት ፈቃደኛ ስለመሆናቸው ጭምር መደራደራቸውን የሚገልፁ የታሪክ ሰነዶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ እያሉ ነው፡፡

ንጉሡን ከሚኮንኗቸው ታዛቢዎች ውስጥ ብዙዎቹ የሚያቀርቡት መከራከሪያ የኢያሱን የግፍ አገዳደል ነው፡፡ ጋራ ሙለታ ታስረው የነበሩትን ልጅ ኢያሱን እንደዕቃ በሳጥን አሳሽገው በአባሐና አጃቢነት በባቡር አዲስአበባ ካስመጧቸውና ከባቡር ጣቢያው አሁን ዩኒቨርሲቲ እስከሆነው ያኔ የእርሳቸው መኖሪያ ቤት ድረስ ዘውዴ ባልቻ፣ መኮንን ባልቻ፣ ደሴ ባልቻ፣ ፈንታ ባልቻ፣ ለማ ባልቻ፡ ኃይሌ ባልቻና በላይ ባልቻ በተባሉት የፊታውራሪ ባልቻ ጉግሣ ልጆች ተሸካሚነት ካስወሰዷቸው በኋላ እጅና እግራቸውን በመጫኛ ጠፍረው በማሳሰር በመኮንን  እንዳልካቸው እጅ በሎንደን ጎራዴ እንዳሳረዷቸው በኤርምያስ ሁሴን አስናኝነት የተዘጋጀውን ‹‹እሳትና ውሃ›› የሚለውን የሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን መፅሐፍ በዋቢ መረጃነት ያቀርባሉ፡፡ (ገፅ 21)

ዐፄ ኃይለሥላሴ የ44 ዓመቱ ንጉሣዊ አገዛዝ ጤነኛ አለመሆኑን ቢያውቁትም እርሳቸው ግን አገዛዛቸውን በማሻሻል ፈንታ ቀድሞ በነበረው መልክ ቀጠሉበት የሚሉት ታዛቢዎች ንጉሡ ለሀገር አሳቢ ቢሆኑ ኖሮ ከራያና አዘቦ፣ ከእንደርታ፣ ከጎጃም፣ ከባሌና ይፋትና ጥሙጋ ገበሬዎች አመፅ ብዙ ትምህርት በወሰዱ ነበር ካሉ በኋላ ንጉሡ በ1952 ዓ.ም ሶቪየት ሕብረትን ሊጎበኙ በሄዱበት ወቅት አብሯቸው ተጉዞ የነበረው የሕዝብ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊያቸውና ኋላ ላይ ከ1953ቱን መፈንቅለ አገዛዝ ሞካሪዎች አንዱ የነበረው ሌ/ኮ ወርቅነህ ገበየሁ አገዛዛቸውን በጃፓን ወይም በእንግሊዝ ሞደል እንዲያሻሽሉ ሲነግራቸው ተገርመው ‹‹አየ ወርቅነህ እኔ የበሰልክ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካንስ ልጅ ነህ፡፡ ከልጅ ጋር ነው የምንሠራው፡፡ ለመሆኑ ማን ሥልጣኑን ለሌላ አሳልፎ የሰጠ አይተሀልን?›› የሚል መልስ ስለመሰጠታቸው አቶ አየለ እሸቱ ባዘጋጁት ‹‹ክብር ዘበኛ የስልጣኔ ፈር ፤ የለውጥ ፋና ወጊ›› በሚለው መፅሐፍ ላይ መከተቡን ይናገራሉ፡፡ (ገፅ 298)

ከ1953ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ንጉሡ አገዛዛቸውን እንዲያሻሽሉ ደፍረው የነገሯቸው እንደነበሩና ከነዚህም ውስጥ ልዑል ራስ አሥራተ ካሣ፣ ጀኔራል ዐቢይ አበበ፣ ጀኔራል መርዕድ መንገሻ፣ ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት፣ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣ ኮ/ታምራት ይገዙና አምባሳደር ሐዲስ ዓለማየሁ የሚጠቀሱ ሲሆን በተለይ ደራሲና አምባሳደር የነበሩት ሐዲስ ዓለማየሁ ጥያቄውን ያቀረቡት የንጉሡን ክብርና ዝና አጉልቶ በሚያሳይ አጻጻፍ ቢሆንም ዐፄ ኃይለሥላሴ ግን ያነጋገሯቸው ከፍተኛ ቁጣና ተግሣፅ በቀላቀለ አነጋገር ነበር፡፡ ‹‹እኛ ከንቱ ውዳሴ እንወዳለን? እንዲህ ብለህ ያቀረብከው? እኛኮ በሚገባ እናውቅሀለን!!›› ሲሏቸው በንግግራቸው የተበሳጩት ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁም ‹‹እኔምኮ በሚገባ አውቀዎታለሁ፡፡ ሊገድሉኝ፣ ሊያስሩኝ፣ ሊገርፉኝ እንደሚችሉ በሚገባ አውቃለሁ›› የሚል መልስ እንደሰጧቸው አቶ ብርሃኑ አስረስ ‹‹ማን ይናገር የነበረ ፤ የታህሳሱ ግርግርና መዘዙ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ማስፈራቸውን በዋቢ መረጃነት እንድናነበው ይጠቁሙናል፡፡ (ገፅ 352)

የ1966 ዓ.ም አብዮት ተቀጣጥሎ ጣራ በነካበት ወቅትም የብዙ ዘመን ታማኝ ባለሥልጣናትን ጠ/ሚኒስትር አክሊሉ ኃ/ወልድና ካቢኔያቸውን ጨምሮ ለደርግ ካራ አሳልፈው በመስጠት እርሳቸው በዙፋኑ ላይ ለመቆየት ጥረት ያደረጉት ለሥልጣን በነበራቸው ስግብግብነት እንደነበር የአቶ ፋሲካ ሲደልልን ‹‹የሻምላው ትውልድ›› መጽሐፍ በምሥክርነት የሚያቀርቡ ታዛቢዎችም አሉ፡፡ (ገፅ 123)

ንጉሡ ከእርሳቸው ውጭ ስመገናና እንዲኖር የማይፈልጉ ቀናተኛ ሰለመሆናቸው የሚተቿቸው ታዛቢዎች የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ማስረጃ ደግሞ በኢትዮ – ኢጣሊያ የ1928ቱ ዓ.ም ጦርነት ወቅት በሰሜን ጦር ግንባር ውሱን ወጣቶችን አስተባብሮ በደፈጣ ውጊያ የኢጣሊያንን ጦር ትንፋሽ ለማሳጠር ከፍተኛ ጀብዱ በመፈፀሙ በሁሉም ቦታ እውቅና በማግኘቱ በኦሮሞኛ ዘፈን የተዘፈነለትን ‹‹አብቹ›› የተባለ የሰላሌ ለግላጋ ወጣት ጀግና፣ ጣሊያኖችን እንዳይወጋ እምቢ የሚል ከሆነም ራስ ካሣ ጦር እንዲያዘምቱበት ንጉሡ የሰጡትን ትዕዛዝ በመጽሐፉ ላይ የከተበውን ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፎ በዚያ ጦርነት የተሳተፈውን የቸከ ሪፐብሊክ ተወላጁ አዶልፍ ፓርለሳክ ጽፎት ተጫን ጆብሬ ‹‹የሀበሻ ጀብዱ›› በሚል ርዕስ የጠቀሰውን መፅሐፍ ነው፡፡ (ገፅ 233)፡፡

ዐፄ ኃይለሥላሴ ቂመኛ ንጉሥ ነበሩ የሚሉ ታዛቢዎችም አሉ፡፡ ለዚህም በወሎ ጠቅላይ ግዛት በቦረና አውራጃ መካነሠላም ዙሪያ በምትገኘው አደሬማርያም ቤተክርስቲያን በግዞት ይኖር የነበረውና ጣሊያን ወደመሀል አገር ዘልቆ ሲገባ ለጣሊያኑ ቲሊንቲ አሳልፎ ሊሰጠው የነበረውን አባዱላ የተባለ አሽከሩን ገድሎ የሸፈተውና በ5ቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን በቤጌምድርና ሰሜን አካባቢዎች ብርቱ ተጋድሎ ሲያደርግ የቆየው ዮሐንስ ኢያሱ፣ ነፃነት እንደተመለሰ የጠበቀው እሥር እንጂ ሹመትና ሽልማት እንዳልነበረና፣ ግርማ ኢያሱ ከነልጁ ኬንያ በመርዝ  መገደሉን፣ጌድዮን ኢያሱና ጎሹ ኢያሱ ጋሞጎፋና ሲዳማ መታሰራቸውን፣ ሚናስ ኢያሱ አዲስ አበባ ከፎቅ ተወርውሮ መገደሉን፣ ምኒልክ ኢያሱ አፍንጮ በር በግዞት መቀመጡን  ባጭሩ ኢያሱንና የኢያሱን ዘር ብሎም የኢያሱን ታሪክ እንዲጠፋ በርካታ ግፍ የፈፀሙት  ቂመኛ ንጉሥ ስለነበሩ ነው ካሉ በኋላ አያይዘውም ሥራ ለሰሪው ነውና የግፍ ጽዋው ሲሞላ ግን እርሳቸው የኢያሱን ዘር ለማጥፋት እንደተሯሯጡ ሁሉ የእርሳቸውም ዘር በዓለም መድረክ እንዳይወጣ፣ እርሳቸው የኢያሱን መቃብር ደብዛውን እንዳጠፉት ሁሉ የእርሳቸውም መቃብር በይሆናል ከሚነገረው ውጪ በትክክል የት እንደሆነ ሳይታወቅ ደብዛው እንዲጠፋ የአምላክ ፈቃድ ሆነ በማለት ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ወጭ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን፣ ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህን፣ ፊታውራሪ ኃይሉ ክብረትን፣ ፊታውራሪ አበረ አዳሙን፣ መቶ አለቃ በቀለ አናሲሞስን እና እጅግ በርካታ ሀገር ወዳድ የጎበዝ አለቆችን ከፖለቲካው ሜዳ ውጭ ያደረጉ ግፈኛ ንጉሥ ነበሩ የሚሏቸውም አልታጡም፡፡

ያም አለ ይህ ዐፄ ኃይለሥላሴ በዙፋኑ ላይ ለ44 ዓመት ቆይተው በስተመጨረሻም በእርጅና ብዛት በሀገር ደረጃ ምን እየተሠራ እንዳለ ማወቅ ተስኗቸው ዙፋኑ ላይ እያንቀላፉ ባለበት ወቅት ኮትኩተው ያሳደጉት የወታደር ስብስብ ከዙፋኑ ላይ አወረዳቸውና ፍጻሜያቸውን አሳፋሪ አደረገው የሚሉ ታዛቢዎች እጅግ በርካቶች ናቸው፡፡

በእርግጥም የንጉሡ ፍፃሜ አሳዛኝ ነበር፡፡ የ108 ወታደሮችና የበታች መኮንኖች ስብስብ የነበረው ደርግ በሕልሙም በእውኑም አስቦት በማያውቀው የምኒልክ ዙፋን ላይ በድፍረት ከወጣ በኋላ የለወጠው ንጉሥ ኃይለሥላሴን ብቻ ሳይሆን ከሺህ ዓመት በላይ የቆየውን ሰለሞናዊ ሥርዓተንግሥና ዘመን ዘለቅ የነበረውን ሥዩመ እግዚአብሔር አስተሳሰብና ነባሩን የሕዝብ አኗኗር፣ ትውፊት፣ ባሕል፣ ልምድና እምነት ጭምር ነበር፡፡ በሌላ አባባል ባገር ደረጃ የነበረውን ሁሉ ገለባብጦ የነበረውን እንዳልነበር አደረገው ማለት ነው፡፡

ታዛቢዎች እንደሚሉት የደርግ አገዛዝ ብልሽት የጀመረውም ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!›› የሚለውን ቅዱስ መፈክር በመሻር 60 የሚሆኑ የቀድሞ ባለሥልጣናትን ሕዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በግፍ ከረሸነበት ዕለት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ኢሕአፓ የከተማ ሽምቅ ውጊያ በመጀመሩ መነሻነት ‹‹ሀገሪቱን የደም መሬት አደረጋት›› ሲሉ ቀሪዎቹ ደግሞ የከተማውን ሽምቅ ውጊያ ኢሕአፓ አለመጀመሩንና  ደርግ በሰነዘረበት በትር የተነሳ ግን የራሱን ሕልውና ለማስጠበቅ ‹‹የመከላከል እርምጃ ውስጥ ነው የገባው›› በሚል የአቶ ክፍሉ ታደሰን ከቅፅ 1 እስከ 3 የተከተቡ ‹‹ያ ትውልድ›› መጻሕፍት በመከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡ ‹‹ኢሕአፓ ነው ጀማሪው›› የሚሉት ታዛቢዎች በበኩላቸው የከተማውን ውጊያ ኢሕአፓ ጀማሪ ለመሆኑ ፓርቲው የ1ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ‹‹ዴሞክራሲያ›› በሚለው ልሳኑ ባቀረበው ልዩ ዕትም የትጥቅ ትግሉን ዝግጅት በማፋጠን ጠላቶቹን እንደሚመታ ሲገልፅ፣ በዴሞክራሲያ ልሳኑ ቅፅ 3 ቁጥር 9 መስከረም 3 ቀን 1969 ዓ.ም በወጣው ዕትም ደግሞ ‹‹ጦርነቱ ታውጇል›› በሚል ርዕስ  የፓርቲውን ሥም የሚያጠፉና ለሻለቃ መንግሥቱ የሚሰልሉትን ጭምር እንደሚመታ የጦርነት አዋጅ አውጆ መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም በሻለቃ መንግሥቱ ላይ የግድያ ሙከራ ማካሄዱን ከዚያም መስከረም 16 ቀን 1969 ዓ.ም ገ/እግዚአብሔር ተስፋየ፣ አቡበከር አብዱልመጂድና ክንፈ አያሌው የተባሉትን የመኢሶን ወጣቶች ሲገድል አስፋው ጫኔ፣ ዘሪሁን ዜናና ተስፋየ ገላን የተባሉትን ደግሞ ማቁሰሉን ከዚያም መስከረም 21 ቀን 1969 ዓ.ም ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድን መግደሉን ገልፀው ዋቢ መረጃቸውን የበለጠ አጠናክረው ሲያቀርቡም፣ ዴሞክራሲያ ቅፅ 4 ቁጥር 11 ላይ ‹‹ፋሺሽቶች ሲወጠሩ›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለከተማው ትጥቅ ትግል አመቺነቱን አብራርተው ትግሉን እንደጀመሩ የሚገልፀውን ጽሑፍ እንደመከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

በ17ቱ የጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ዘመነ አገዛዝ በሀገሪቱ ተከስቶ ለነበረው ሁለንተናዊ ኪሣራ  ደርግንም የመከላከያ ሠራዊት አዛዦችንም ተጠያቂ ለማድረግ የሚፈልጉ ታዛቢዎች እንዳሉ ሁሉ ሁሉንም በጅምላ ተጠያቂ ማድረግ አግባብ አለመሆኑንና ከደርግ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት መካከል ‹‹ለእናት ሀገራቸው በቅንነትና በሀቀኝነት የተጋደሉ ብሎም ሕይወታቸውን ጭምር የገበሩ አሉ ፤ ያ ማለት ግን ሁሉም ሀቀኞች ነበሩ እያልን አለመሆኑ ይታወቅልን›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አጋጥመውኛል፡፡ እኒህ ታዛቢዎች አያይዘውም እጅግ ከፍተኛ የሰው ሕይወት በተገበረበት የኤርትራና የትግራይ ጦርነት ወቅት ሊታመን በማይችል ሁኔታ ላገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ የሠራዊቱ አባላትና መኮንኖች ነበሩ፡፡ የነዚህ ክፍላተ ሀገራት ውጊያ በሸማቂዎች ድል አድራጊነት የተጠናቀቀውም ‹‹እነጀኔራል ገብረክርስቶስ ቡሊን የመሰሉ ጀብደኛ አመራር ሰጪዎች ሲሰጡት በነበረው ያልተጠናና ከስሜት ያልፀዳ የውጊያ ትዕዛዝ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት የተሳሳተ የውጊያ ትዕዛዝ የተነሳ እነኮሎኔል ካሣ ገ/ማርያምን ኮሎኔል አይተነው በላይን፣ ኮሎኔል ሰይፉ ወልዴን የመሰሉ ጀግኖች አጥተናል›› በማለት በፀፀት ይናገራሉ፡፡

የትግራይ ሸማቂዎች በትግራይ መሬት መንቀሳቀስ መጀመራቸው እንደተሰማ ሲንቀሳቀሱበት በነበረው ሽራሮ በተባለው አካባቢ የአየር ወለድ ጦር ከአውሮፕላን በፓራሹት በማውረድና በመክበብ ጠራርገው ለማጥፋት ያለበለዚያም ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበው የነበሩት የ2ኛው ክፍለጦር አዛዥ የጀኔራል ወርቁ መኮነን ጥያቄ ተቀባይነት ማጣቱ ሳያንስ ኋላ ላይ የትግራይን ክፍለ ሀገር ዕጣ ፈንታ የወሰነውንና የኢትዮጵያን ሠራዊት አቋም ሙሉ በሙሉ አዛብቶ ለወያኔ ደማቅ ድል ያስጨበጠው የሽሬ እንዳሥላሴ ማጥቃት ትዕዛዝ የተሰጠው ከሻምበል ለገሰ አስፋው እንደነበር የሚናገሩት ታዛቢዎች፣ የጀኔራል ወርቁ መኮነን ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ወያኔ ጥፍር ሳያወጣ ያከትምለት እንደነበረና ጓድ ለገሰ አስፋው ከስሜት ባልፀዳ ትዕዛዝ ለ604ኛ ኮር የማጥቃት ትዕዛዝ ሳያስተላልፉ ውጊያውን ልምድ ላካበቱት የጦሩ አዛዦች ትተውላቸው ቢሆን ኖሮ ኋላ ላይ ‹‹ወያኔ በጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሥልጣንም ሆነ አገዛዝ ዙሪያ ወሳኝ መሆኑ ያከትም ነበር›› በማለት ጀኔራሉ ከላይ የጠቀስኩትን የተቀደሰ ሐሳብ አቅርበው ግን በአንዳንድ ሴረኛ ባለሥልጣናትና የጦር መሪዎች የተፈፀመውን ደባ የሚዘረዝረውን ‹‹ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነት›› የሚለውን  የኮሎኔል እስጢፋኖስ ገ/መስቀል መፅሐፍ እና ‹‹ትውልድን ያናወጠ ጦርነት›› የሚለውን የሻለቃ ንጋቱ ቦጋለን መጽሐፍ በጥሞና እንድናነብ ይመክሩናል፡፡ 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...