ዓይናለም ደበበ
በቁርጥ ቀን ልጅ፣ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ፍፁም ጀግንነትና ጥበብ የተመላበት የጦር አመራር እንዲሁም የሀገር ፍቅርን ታጥቀው፣ ፈጣሪን በልባቸው ሰንቀው ለሀገር ነፃነት ከጫፍ ጫፍ በተሰባሰቡ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች አማካኝነት በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ በደም ስለተፃፈው የዓድዋ ድል ታሪክ ከተለያየ የመረጃ ምንጭና መፃሕፍት ያሰባሰብኩትንና ያጠናከርኩትን ፅሁፍ እንደሚከተለው ለማቅረብ ወደድኩኝ።
ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ ኢትዮጵያን ለአጭር ግዜ በገዙት በአፄ ተክለጊዮጊስ ዘመን ጁሴፔ ሳፔቶ የተባለ ሚስዮናዊ የአሰብ ባላባት ከሆኑት ከሱልጣን ኢብራሒምና ከራሂታው ሱልጣን ከሐሰን መሐመድ ጋር በመወዳጀት ባገኘው ፍቃድ መሠረት በ1862 ዓ.ም አሰብንና ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የቀይ ባህር ዳርቻ መሬትን በ8100 የማርትሬዛ ብር ለመግዛት ተስማማ። ሚስዮናዊው ወዲያውም ሩባቲኖ ከተባለ የጣልያን የመርከብ ኩባንያ ጋራ በመቀናጀት በቀይ ባህር ዳርቻ ወደብ እንዲመሠረት ተነጋግሮ ከኩባንያው ያገኘውን ገንዘብ ፈጥኖ ለሱልጣኖቹ ከፈለ። ገንዘቡን በከፈለ በማግስቱም በኢትዮጵያ ምድር ላይ የጣልያንን ባንዲራ ሰቅሎ በማውለብለብ 28 ግዜ መድፍ አስተኮሰ። ከዚያም ሩባቲኖ የተሰኘው የመርከብ ኩባንያ አሰብ ላይ ወደብ አቋቁሞ ለጥቂት ዓመታት እምብዛም ሲገለገልበት ከቆየ በኋላ መሬቱን ሙሉ ለሙሉ ለጣልያን መንግሥት አሳልፎ ሰጠ። የጣልያን መንግሥትም አሰብ የጣልያን ግዛት መሆንዋን በአዋጅ አሳወቀ።
ምንም እንኳን ጣልያን በአፍሪካ የቀይ ባህር ጠረፍ ላይ እንደመንደርደሪያ የተጠቀመበትን የአሰብን ምድር በዚህ ሁኔታ ለመርገጥ ቢችልም ለቅኝ ግዛቱ መስፋፋት አመቺ ሁኔታን በመፍጠር መሠረት አድርጎ የተነሳው ግን ምፅዋን ነበር።
በንጉሠ ነገሥት አፄ ዩሐንስ አራተኛ ዘመነ መንግሥት የእንግሊዝ መንግሥት የቅኝ ግዛት በነበረው ሱዳን በተቀሰቀሰው የማህዴስቶች ንቅናቄ እንግሊዞች ናላቸው ዞሮ ለችግራቸው መውጫ ምፅዋን ገፀበረከት አድርገው በማቅረብ ያገኙትን መንግሥትና የጦር መሪ ሁሉ አጋር እንዲሆናቸው ያታልሉበት ነበር። በዚሁ አካሄዳቸውም በምፅዋ ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን ጋራ ያደረጉትን ስምምነት በተመሳሳይ መልኩ በግዜው ከኢምፔሪያሊዝም አፍላ ፍቅር ወድቀው መግቢያና መውጫቸውን፣ መቆሚያና መቀመጫቸውን በመፈክር ከሞሉት የጣልያን ባለስልጣናት ጋራም ሚስጢራዊ ስምምነት አደረጉ። የጣልያን መንግሥትም በግዜው በግብፆች እጅ የነበረችዋን ምፅዋንና የቀይ ባህር ጠረፍን ለመቆጣጠር በነበረው ፅኑ ፍላጎት ላይ ከእንግሊዞች ጋራ ተባባሪ የሚሆኑበትን ሚስጢራዊ ስምምነት በማድረጉ የልብ ልብ ተሰምቶት ፈጥኖ ጦሩን በማስፈር የምፅዋ ወደብን ተቆጣጠረ። በሌላ መልኩ ጉዳዩን በእልህ አስጨራሽ ትግስት የሚከታተለው የኢትዮጵያ መንግሥት በገዛ ንብረቱ በምፅዋ ዙሪያ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የገባው ስምምነት ተፈፃሚ ባለመሆኑ በንጉሠ ነገሥት አፄ ዩሐንስ አራተኛ አማካኝነት ተቃውሞውን ገለፀ።
ጣልያኖች ከዚህ ሁኔታ ተነስተውም ግዛት እያሰፉ ወደ መሀል አገር እያማተሩ ዘልቀው መግባት ያዙ። “…በሌላ አነጋገርም ምፅዋ የዓድዋ ጥንስስ ሆነ።” ሲሉም ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 – 1983 በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ፅፈዋል።
እንግሊዞች ከኢትዮጵያ ጋራ በምፅዋ ጉዳይ ቀድሞ ስለገቡት ስምምነት በጣልያን መጣሱን ለማስተባበል የጣልያን ጦር ከምፅዋና አካባቢው ሊርቅ እንደማይችል እየደሰኮሩ ለክራቸው ሟች የነበሩትን ንጉሠ ነገሥት አፄ ዩሐንስን ለማዘናጋት ይሞክሩ ነበር። እውነታው ግን ጣልያኖች በፍጥነት ወደ ውስጥ ዘልቀው ሰሐጢና ዊያ የተባሉ ቦታዎችን መያዛቸው ነው። በዚህ ግዜ ታድያ በጣልያኖች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ የበሸቁት የአውራጃው ገዢ ራስ አሉላ እንግዳ(አባነጋ) ከፍተኛ ተቃውሟቸውንና ቁጣቸውን በጣልያኖች ላይ አሰሙ። በአጭር ቀን ውስጥ ጣልያኖች የያዙትን መሬት ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ ትዕዛዝ አዘል ቀጭን መልዕክት ራስ አሉላ ቢያስተላልፉም ከጣልያኖች የተሰጣቸው ምላሽ ግን ንቀት የታከለበት በመሆኑ ጦራቸውን ለፍልሚያ ያዘጋጁ ጀመር። ዶጋሊ ላይ በተደረገው ጦርነትም ነበልባሉ ራስ አሉላ እንግዳ ትዕቢት የወጠረውን የጣልያንን የጦር ሰራዊት ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይተርፍ አድርገው ዶጋመድ አበሉት። ይህን የሰማው የጣልያን ፓርላማም በእጅጉ ደነገጠ። የሚይዘው የሚጨብጠው አጣ። ሆኖም ግን የሰው ኃይልና የበጀት ማሻሻያ በማድረግ ለበቀል መዘጋጀቱን ቀጠለበት። ያም ሆነ ይህ ግን “ጣልያኖች በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚሰፍሩት እኔ የሮማ አገረ ገዢ መሆን የቻልኩ እንደሆነ ብቻ ነው” በማለት ውዱ የኢትዮጵያ ልጅ ራስ አሉላ ቆራጥ አቋማቸውን ገለፁ። ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የመሪዎች ሽኩቻና ተራ አለመግባባት እንዲሁም በውጪ ጠላቶቿ ብዛት የተነሳ ጣልያኖች ለማንሰራራት እድል አገኙ። መስዕዋትነት ተከፍሎባቸው ነፃ የወጡ መሬቶችም በድጋሚ በጣልያኖች እጅ ወደቁ። ባጭር ግዜ ውስጥ ወረራቸውን በማስፋፋትም የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ኤርትራ የሚል ስያሜ በመስጠት የቅኝ ግዛት ለመፍጠር በቁ።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ረሃብና ድርቅ ተመታ። ጣልያኖች ወደ ምፅዋ ባመጧቸው ከብቶች አማካኝነት የደስታ በሽታ ገብቶ ብዙ ከብት አለቀ። የእህልና የከብት ዋጋ በእጅጉ ናረ። ሰው ሰውን የበላበት ፣ አንዳንዶችም ራሳቸውን ለባርነት አሳልፈው የሸጡበት ሁኔታ ተፈጠረ። ይህን የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት መከራ ሲጠባበቁ የቆዩ የሚመስሉት ጣልያኖችም መላው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ የሚያስችላቸውን ውል የወዳጅነት አስመስለው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ ውጫሌ ላይ ለመፈራረም በቁ። በውሉም አንቀፅ አስራ ሰባት የጣልያንኛው ትርጓሜ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ማንኛውንም የውጪ ግኑኝነት በጣልያን መንግሥት በኩል ብቻ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሲገልፅ ፤ የአማርኛው ትርጓሜው ግን የውጪ ግኑኝነት እንደ አስፈላጊነቱ በጣልያን አጋዥነት መፈፀም እንደሚያስችል የሚያስረዳ ነበር።
ዛሬ ባለንበት ዘመን እንደታዘብነው ሁሉ፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ጥቅም ሽንጧን ገትራ ከምትከራከረው ሩሲያ በስተቀር ኃያላኑ መንግሥታት በሙሉ ጆሯቸውን ደፍነውና አይናቸውን ጨፍነው የውሉን የጣልያንኛውን ትርጓሜ ብቻ እውቅና ለመስጠት ተዘጋጁ። ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ውሉ መሻሩን አሳወቁ። ለማይቀረውም ጦርነት የክተት አዋጅ አወጁ።
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል ይቆፍር ጀመር። በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፣ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም ፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኀኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለምሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ” በማለት አወጁ።
ያገሬው ሰው ይህን የንጉሠ ነገሥቱን ጥሪ ተቀብሎም ከጫፍ ጫፍ ወጣ። ከዚያም አምባላጌና መቀሌ መጨረሻም አድዋ ላይ በተደረጉ አውደ ውጊያዎች የጣልያን ጦር ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ ፍርክስክሱ ወጥቶ ድል ተመታ። የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ፖሊሲም ከጣልያን ጦር ጋር በአንድነት ተሸነፈ። ድሉ በዓለም ሕዝብ ዘንድ የነፃነትና የእኩልነት ተምሳሌት ተደርጎም ተወሰደ። በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ለሰው ልጆች ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ወደር የማይገኝለትን አዲስ ርዕዮተ ዓለምን አበረከተ።
ዛሬ ባለንበት በዚህ ዘመን ይህን በደም የተፃፈውን የዓለም ሕዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚደነቅበትን አኩሪ ታሪክ ለማወደስና ለማስታወስ የምንራኮትበትና የምንሻኮትበት ሁኔታ መፈጠሩ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ከመሆኑ የተነሳ እየተጓዝንበት ያለንበትን መንገድና የተገኘንበትን አረንቋ ቆም ብለን እንድንመረምር የምንገደድበት ብሎም አስመሳዮችን በማሳፈር ወደ ትክክለኛው ጎዳና የምንሸጋገርበትን ተግባር የምናከናውንበት ግዜ ላይ እንዳለን ይሰማኛል።
በቸር ያቆየን!
