የዋዜማው ምልክት
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደኖረ የሚነገርለት እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ ጊበን `The Decline and fall of the Roman Empire` በሚል ርዕስ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ በመጽሐፉም በዘመኑ የነበረውን የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን እውነታ በመሠለው መልኩ ሊገልጸው ሞክሯል፡፡ ገለጻው በኋለኛው ዘመን አንባቢም ኾነ የታሪክ ተመራማሪ ዘንድ ወጥ የኾነ ቅቡልነት አግኝቷል ብሎ መደምደም ባይቻልም መነጋገሪያ ለመኾን መብቃቱ ግን አልቀረም፡፡ ታሪክን ከሥነ መንግሥት ይልቅ ከማኅበረሰብ አንጻር ሊመረምሩ በሚሞክሩ ወገኖች ዘንድ ግን ከቁብ የሚገባ ጭብጥ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ከትችት አላስተረፉትም፡፡
በዚህ ረገድ ዶ/ር ሽመልስ ቦንሳ የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ ከዓመታት በፊት በርዕዮት ሚዲያ ላይ ቀርበው “ጊበን መመልከት የፈለገው በመንግሥት ደረጃ ከአውሮፓውያን ገዢዎች ጋር ይደረግ ስለነበረው ኦፊሴላዊ ግንኑነት ካልኾነ በስተቀር፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ ግልም ይኹን በቡድን ወደመላው ዓለም ተዘዋውረው መቅሰም የሚገባቸውን ከመቅሰም ወደኋላ አላሉም ነበር” ሲሉ የተናገሩትን ለአብነት መጥቀስ ይችላል፡፡
ይኽንን የጊበን ሃሳብ ወደዚህ ያመጣሁት እንበለ ምክንያት አለመኾኑ ይታወቅልኝ፡፡ በርዕሴ ሹክ ለማለት እንደሞከርኩት ዓድዋ “የትንሣዔ ጥላ” ለመኾኑ ጥሩ ማስረገጫ ኾኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ ጊበን የመሳፍንት የግዛት ትርምስን አደብ አስገዝታ ማዕከላዊ አስተዳደሯን ማጽናት ዳገት የኾነባት የዘመኑን ኢትዮጵያ የገለጻት እንዲህ በማለት ነበር፡፡ “Encompassed on all sides by the enemies of their religion, the Ethiopian slept near a thousand years forgetful of the world by whom they were forgotten.” (ዙሪያቸውን በእምነት ባላንጣዎቻቸው በመከበባቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ዓለምን ረስተው ዓለምም እነርሱን ዘንግታ ለሺህ ዓመታት አንቀላፉ)፡፡
ይኽ ዓረፍተ ነገር ድንግዝግዝ በዋጣት የዘመነ መሳፍንቷ ኢትዮጵያ፣ ለትንሣዔዋ ችቦን የለኮሰ ንግግር ነበር፡፡ መከፋፈሏ፣ መቧደኗ፣ ዓለም ከተጥለቀለቀበት አብርኾት መናጠቧ በቁጭት ያትከነከናቸውን ነገሥታት አምጦ ለመውለድም አስችሏል፡፡ ከቴዎድሮስ መነሳት በኋላ ኢትዮጵያ የሥነ መንግሥት ታሪኳን አድሳ የተቋረጠውን የትውልድ ክፍተት ለመጠገንም ዕድል ሠጥቷታል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ብርቱ የጦር ሠራዊትና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ለመገንባት ሂደቱ ጉልህ መግፍኤ በመኾኑም ሃሳቡ እንደቀሊል ሊታይ አይችልም፡፡ ከአንድነት፣ ከጥንካሬና ከትንሣዔ ዋዜማ መከፋፈል፣ መቆራቆስና መውደቅ መሰናክል ኾነው የሚመጡትበትን አዙሪት ዞር ብሎ ለማስተዋልም ዕድል ሰጪ ነው፡፡
ትልቁ የሕይወት ዘመን እውነት ግን ሌላ ነው፡፡ የንግግሩን ጭብጥ የኋለኛው ዘመን ትውልዶች መለስ ብለን በመረመርነው ቁጥር በተኙበት መቅረት፣ በተረቱበት ማንቀላፋት ሕያው ኾኖ እንደማይዘልቅ ማረጋገጫ ኾኖናል፡፡ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከውድቀት ማግሥት መነሳት ዑደት ኾኖ እንደሚመጣም ቋሚ ምሥክር ይኾናል፡፡ አሸናፊነት እና ድል አድራጊነት ዳግም እንደሚመለሱ፣ የጠፋ የመሰለው ታላቅነት ራሱን እንደ ንሥር አሞራ አድሶ እንደሚነሳም ግዙፍ አብነት ይኾነናል፡፡
ይኽ ኹሉ የሕይወት ዘመን እውነት ሲታወሰን ታዲያ አብሮ ሊታሰበን የሚገባ ብርቱ ቁምነገርም አለ፡፡ ይኽም ሁሌም በትንሣዔው ዋዜማ መሥዋዕቱ ይበዛል ፤ መከራው ያይላል ፤ ተስፋ አስቆራጭ ነገሩ ይበረክታል፡፡ አንባቢ ኾይ ዓድዋን በወግ በወጉ መበለት የሚያስፈልገውም ለዚህና ለዚህ ነው፡፡ ዓድዋ ትናንት ላይ ተሰርቶ ትናንት ላይ ያበቃ፣ ትናንት ላይ በቅሎ ትናንት ላይ የተወቃ አንድ የድል አውድማ አይደለም፡፡ በልተን ያልጠገብነው፣ ዘግነን ያልጨረስነው የመኖር ሌማት ነውና መቁረሳችንን እንቀጥል፡፡ እንኾ ምኒልክ!
ጥቁሩን ሰው ከጥቁሮች መዝገብ?
የዓድዋ ድል የተለመዱትን የዓለም የድል መዝገቦች ታሪክ ከታች ወደ ላይ ነቅንቆ በመገልበጥ ረገድ ተስተካካይ የለውም። እንዲህ ያለ ሁነትን የቲያትር ጥበብ ሰዎች “ድንቃይ” ወይም “ሜሎ ድራማ” የሚል ሥም ይሰጡታል። ድንቃይ ተውኔት በሁለት የወደረኛነት ችግር ባለባቸው አቀንቃኝ እና ተቀናቃኝ ገጸባሪያት መካከል በሚደረግ የጠነከረ ግጭት ሳቢያ በጥንካሬውና በብቃቱ የደከመ አቅምን የተላበሰው ገጸባህሪ ጉልበቱና ጡንቻው የፈረጠመው ኃያሉን ገጸባህሪ ድል በማድረግ የሚያጠናቅቅበት የተውኔት ዓይነት ነው (ሚዳቆ እንደምንም ተፍጨርጭራ ነብርን ዘርራ የመጣል ያህል ተደርጎ ሊታሰብም ይችላል)። ዓድዋ በአሸናፊነት ውስጥ ከፈረስ ጉልበት ይልቅ እውነት ፣ ከትምክኽት ይልቅ ዕምነት ፣ ከመሣሪያ ጋጋታ ይልቅ የሥነልቦና ጥንካሬ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ያስተማረን ፣ የክብርና የማያልቀው ኩራታችን ምንጭ የሆነ ትልቅ ድል ነው።
የዓድዋው መሪ ዳግማዊ ምኒልክ ድኅረ ድሉ ባለው ዘመን የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ምልክት ተደርገው ይታሰቡ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ይኽ ንጥረ ሃቅ ሆዳቸውን እንደኮሶ የሚመርረው ኢትዮጵያዊ የታሪክ አተሎች ግን በለመዱት የሴራ ተሰጥኦዋቸው ትዕምርትነታቸውን ሊፍቁ የቻሉት ርቀት ድረስ መጓዛቸውን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ “በጥባጭ ካለ ጥሩ አይጠጣም” እንዲሉ ሁሌም በትንሣዔ ዋዜማ ጨሬያቸውን አሹለው፣ ካራቸውን ወልውለው የጥላቻ እንገራቸውን ሊግቱ የሚደክሙ ስሁታን በመኖራቸው መከራው ይረዝማል፡፡ የትንሣዔ ዋዜማ አመሉ እንዲህ ነውና!
ሮበርት ስኪነር የተባለው የመጀመሪያው አሜሪካዊ ዲፕሎማት ንጉሠ ነገሥቱን አስመልክቶ “ምኒልክ እኔ ኔግሮ አይደለሁም ፤ ኮኬሽያን ነኝ (I am not a Negro, I am Caucasian)” አሉ ብሎ መጻፉን ተከትሎ እነኚህን ኃይሎች “ጥቁር በመኾናቸው ያፍራሉ” የሚል ሙግት ፈብርከው ነበር፡፡ እንደእውነቱ ከኾነ ግን እነኚህ ወገኖች የምኒልክ “ጥቁር አይደለሁም አሉ” ማለት አስቆጭቷቸው ያደረጉት አልነበረም፡፡ ጥቁሩን ሰው ከጥቁሮች የጀብድ መዝገብ ለመፋቅ ያደረጉት ከንቱ ሙከራ እንጂ፡፡
በርግጥ ምኒልክ በ1878 ለንጉስ ሊዎፖልድ በጻፉት ደብዳቤ “የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሱማሌ መልኩ ኣንድ ነው፡፡ ሁሉም ጥቁር ነው፡፡” በማለት መከራከሪያውን ውድቅ አድርገውታል፡፡ (ምንጭ Acta Ethiopia vol 3 Edited by Sven Rubenson p.302፡፡) ይኽ ብቻም ሳይኾን፣ ዳግማዊ ምኒልክ ጥቁረታቸውን ከመቀበል አልፈው ከአፍሪካዊ ጌቶች ጋር ጥቁረትን መሠረት ያደረገ ትብብር ይጠይቁም እንደነበር ከሱዳኑ የማህዲስት መሪ ጋር ሲደራደሩ ተናግረውት የነበረውን ቃል ኢጣሊያናዊው መኮንን ባራቴሪ በማስታወሻው አስፍሮት ክሪስ ፕሮቲ በእንግሊዝኛ ተርጉማ “Empress Taitu and Menilk” በተባለው መጽሐፏ ገጽ 119 ውስጥ ያሰፈረችውን መመልከት ይቻላል፡፡
“Between us there has been no war. Now we have worse enemy who will make slaves of you and me. I am black :and you are black. Unite with me”(“በአንተ እና እኔ መሃል ጠብ ኖሮ አያውቅም፡፡ ሁለታችንን በባርነት ሊገዛን የተሰናዳ የከፋ ጠላት አለብን፡፡ እኔ ጥቁር ነኝ፡፡ አንተም ጥቁር ነህ፡፡ እንተባበር፡፡”)
ከሁሉም በላቀ ደግሞ ደራሲ ንጉሤ አየለ ከኹለት ዓመት በፊት ለንባብ ባበቁት “ታላቁ ጥቁር” በተባለው መጽሐፍ ያስቀመጡልን አስረጂ የንጉሠ ነገሥቱን የጥቁር ትዕምርትነት ያገዝፈዋል፡፡ ይኸውም የሄይቲ ተወላጅ የኾነው ሲልቬይ የተባለ ሰው ከሀገሩ መንግሥት ለዳግማዊ ምኒልክ መልዕክት ይዞ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ ጋር ይያያዛል፡፡ ሲልቬይ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣና ምኒሊክንም ከተገናኘ በኋላ ንጉሡ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ያላቸውን ቁርጠኝነትና ጥረት በመረዳቱ ለንደን ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው ‹‹የአፍሪካዊያን ማኅበር›› ፕሬዝዳንት እንዲሆኑና የመክፈቻ ንግግርም በቦታው ተገኝተው እንዲያደርጉ ጋብዟቸው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ለግብዣው አመስግነው ሲልቬይን ወኪል በማድረግ ሀሳባቸውን በማኅበሩ ጉባዔ ላይ ገልጸዋል፡፡ ይህም ሁነት በወቅቱ የአውሮፓና የአሜሪካ ጋዜጦች ሰፊ ሽፋን አግኝቶ ነበር፡፡
ኤሊስ የሚባል ሌላኛው የአሜሪካ ዜጋ ደግሞ ከምኒልክ ጋር በነበረው ቆይታ ‹‹አወጉኝ›› ያላቸውን ሀሳቦች ሁሉ ለበርካታ ጋዜጦች ገልጹዋል፡፡ እንደትንግርት የሚታሰበው ማንነታቸውም ሰፊ ሽፋን አግኝቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ ንጉሡ ለነጻነትና ለጥቁር ሕዝብ ያላቸው አመለካከት በዘመኑ በነበሩ ብዙኃን መገናኛዎች ተነብቧል፡፡ ከነዚሀም መሀል አንዱ ኤሊስ፡- ‹‹[ምኒልክ] እኔ ጎበዞችን አደንቃለሁ ፣ ነገሥታት ሁሉ እንደ ሩዝቬልት ጎበዞች ሊሆኑ ይገባል፡፡… አንድሪው ካርኒጊ ጥቁሮች ትምህርት እንዲያገኙ ስላበረከቱት መልካም ሥራ የሰሙ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ ‹እግዚአብሔር እንዲህ ያሉ ጎበዞችን እንዲባርካቸውና እንዲጠብቃቸው እለምነዋለሁ›… ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ ትኖራለች፡፡ በተለይም የነጻነትን ምንነት የምታውቁ እንደናንተ እንደ አሜሪካኖች ያላችሁትን እንቀበላለን›› ብሎ መናገሩ ተመዝግቧል፡፡
እንግዲህ ታሪክን ከመስኩ ሳይኾን ከፖለቲካ ፓርቲዎች መስኮት የተማሩት ልኂቃን ዐድዋን ከንጉሠ ነገሥቱ ነጥሎ ለማክበር መጣደፋቸውም ኾነ የጥቁሮች ትዕምርት የኾነውን መሪ እንዲህ ባለ ዓይን ባወጣ የፈጠራ ክስ ሊያጠለሹት መሞከራቸው የሚነግረን ብዙ መልዕክት አለው፡፡ ታሪክ ፈልስሞ፣ ያልኾነን ኾነ ፣ ያልተደረገውን ተደረገ ብሎ ሀገር ወደነበረችበት ታላቅነት እንዳትመለስ ቀፍድዶ የመያዝ ተግባር ምንጩ ሌላ አይደለም ፤ ጉዳይ አስፈጻሚነት ነው፡፡ ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ የተባሉ ጸሐፊ ይኽ ዐይነቱን ተደጋጋሚ ሀገርንና የሀገር ምልክት የኾኑ ግለሰቦችን የማሳነስ ተግባር “አውሮፓዊያኑ ኢትዮጵያን ስለዓድዋ አሸናፊነቷ እያወራረዱት ያሉ የእጅ አዙር ሒሳብ” ሲሉ በጥሩ መንገድ ገልጸውታል፡፡
የጥቁር መዝገብነታችን
ኢትዮጵያ ቅድመ ዓድዋ እና ድኅረ ዓድዋ በተለያዩ ተላውጦዎች ውስጥ አልፋለች፡፡ ዓድዋ በኩራት የምንታበይበትን ነጻነት ከማጎናጸፍ የተሻገረ ዘመኑን በዋጀ የታላቅነት እሽቅድምድም ውስጥ እንድንገባ አብሪ ጥይት ኾኖም አገልግሏል፡፡ ወዳጆች አበርክቷል ፤ አፋሽ አጎንባሽም አብዝቷል፡፡ ከምንም በላይ ግን ድሉ የወለደው መነቃቃት፣ ዓለም ከደረሰበት ቁሳዊ ሥልጣኔ አንጻር ኋላ ያስቀራትን የመሳፍንት ጉተታ ለመቀየር በጎ አጋጣሚ ከፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከመንደር ግዛት አስፋፊዎች ቁርቁስ ወጥታ ቴክኖሎጂን፣ ትምህርትንና ዘመናዊ የመንግሥት አሠራርን “አንድ” ብላ እንድትጀምር ቀንዲል ኾኗታል፡፡
እዚህ ጋር መታወስ የሚገባው ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ድሉን የምንዘክርበት አመክንዮ፡፡ የሚከተሉት ዐሥር ነጥቦች ድኅረ ዓድዋ ባለው ኅላዌያችን ትርጉማቸው ግዘፍ የነሱ ጭብጦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዓድዋ ለእኛ፡- ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያገናኘ (የታሪክ መበጠስ እንዳይፈጠር ያደረገ) ድልድይ ነው ፤ የጥንቶቹን አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸው ፍቅር የተመሰከረበት ማኅተም ነው ፤ ባሕላችን ተጠብቆ እንዲኖር ያስቻለን(ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በባሕል ቅኝ ግዛት ብንወረርም) ባለውለታ ነው ፤ የኢትዮጵያን አንድነት እውን ለማድረግ ያስቻለ ትልቅ ክስተትም ነው ፤ ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ መድረክ እንድትታወቅና እንድትከበር ምክንያት የሆነ አጋጣሚም ነው፤ ነጻነታችንን አስከብረን መኖር እንደምንችል ያስመሰከርንበት ማስታወሻም ነው፣ ለሌሎች ሀገራት ሕዝቦች አርአያ መኾን የቻልንበት ምልክትም ነው ፤ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለማቀፍ ደረጃ(በተለይም በአፍሮ አሜሪካዊያንና በአፍሪካዊያን እንዲቀነቀንና እንዲያብብ) ምክንያት የኾነ ተጋድሎም ነው ፤ ጥቁር ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚችል (የሰው ዘር ሁሉ እኩል እንደሆነ) አውሮፓውያን ትምህርት ያገኙበት መጽሐፍ ነው(በመሆኑም ቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል)፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ በዕውቅና እንዲረጋገጥና ድንበሯን በአግባቡ ለመከለልም ጭምር አቅም የፈጠረ ታላቅነት ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን ዓድዋ ባፈነጠቀው ብርሃን ኢትዮጵያ በርካታ ትሩፋቶች መጥተውላታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለፈውን አንድ መቶ ዓመት ተላውጦ መለስ ብሎ መቃኘት በቂ ነው፡፡ የጠንካራ መንግሥት ተቋማዊ አዕማዶችን ከመትከል ጀምሮ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት መሥራች አባል እስከመኾን ድረስ፣ ከአፍሪካ እስከ ኤዢያ ለሠላም ማስከበር ግዳጅ ኃላፊነትን ከመወጣት ጀምሮ፣ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ኾኖ እስከመመረጥ ድረስ ዓድዋ እስከሚሌኒየማችን ባለው አንድ መቶ ዓመት ለአዳዲስ አብርኾቶች መሠረት ኾኖ አገልግሎናል፡፡
መጪው ትንሣዔ
የዘንድሮው 125ኛው ዓመት የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡ የዘንድሮው ክብረ በዓል በርካታ ልዩ የሚያደርጉት አጋጣሚዎችን ከመያዙ በላይ ስለመጪው ትንሣዔ የሚነግረን ጥቁምታ ቀላል አይደለም፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት ለበዓሉ የሰጠው ትኩረት ዓድዋ በቀጣዩ ዘመን የአብሮነታችንና ገመድ ኾኖ እንዲቀጥል መንገድ መጥረጉን የሚያመለክት ነው፡፡ እርስ በእርስ ካለው ሽኩቻ፣ መጠራጠርና መገዳደል ማግሥት እንዲህ ያለው የአንድነት ማሠሪያ ገመድ የሕልውናችን ማጥበቂያ ኾኖ እንዲመጣ መፍቀድ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያም ኾነ የኢትዮጵያዊያን መዳኛ ውሉ የተቋጠረው በፍኖተ ዓድዋ መኾኑን ጠልቆ ለመገንዘብና ለመረዳትም ዕድል ይሰጣል፡፡ የካቲት ወርን ለዝክረ ዓድዋ ከማዋል ጀምሮ በመንግሥትና የግል ብዙኃን መገናኛዎች ላይ የተሰጠው ትኩረት መጪው ዘመናችንን ብሩህ ለማድረግ ጠንካራ መደላድልም ይኾናል፡፡
በሌላ ገጽ ደግሞ የዘንድሮ ዓድዋ ያለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የጨለማው ንጉሥ ኾኖ የቆየውን ስብሰብ እስትንፋሱ በተነነ ማግሥት የሚዘከር መኾኑ ስለዛሬም ኾነ ስለነጋችን መንገድ ብዙ ይነግረናል፡፡ ኢትዮጵያ ለዳግም ትንሣዔዋ ማኮብኮብ ጀምራለች፡፡ በዚህ ከዓድዋ ፈልቀው ዓድዋን ያደበዘዙት የታሪክ መርገምቶች ግብዓታቸው ተፈጽሞ በኩራትና በልበ ሙሉነት ድሉን ለመዘከር መታደምም ትልቅ በረከት ነው፡፡
ኾኖም በየዓለማቱ ተቀምጠው ዘመኑ በፈቀደላቸው ዘዴ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሕልውና ፈተና ላይ ለመጣል ሌት ተቀን የሚሞክሩ አልጠፉም፡፡ ታሪክ ራሱን እንዲደግም የተፈደረደበት ሀገር ነውና ዳግማዊ ምኒልክ በዘመናቸው ለገጠማቸው ፈተና “ኢልግ” ለተባለው ወዳጃቸው የሰደዱትን መልዕክት አስፍረን ነገራችንን ብንቋጭ እጅጉን መልካም ኾኖ አገኘነው፡፡
“በነጉግሳና በነቅጣው ነገር ምን ያናድድሃል። እኔ መስደዴ ጥበብ የተማሩ እንደሆነ ይጠቀሙበታል ብዬ ነበር። አሁንም እኔን ጠልተው ከሄዱ የሄዱበት አገር ይኑሩ ጥጋባቸውን ይፈጽሙ። እኔንም እንምጣ ብለው ቢልኩብኝ አንድ ጊዜ ጠልታችሁኝ ሄዳችሁዋል ከሄዳችሁበት አገር ኑሩ ብዬ ላክሁባቸው። ለነዚያ ቀረባቸው እንጂ እኔን ምን ጎዱኝ ብለህ ነው።” ክብር ለአበውና እመው!
