የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን (FCSC) የመንግሥት ሠራተኞችን ሁለንተናዊ ብቃት ለመመዘን ያዘጋጀው የብቃት ማዕቀፍ፣ የሙያ ዕውቀትን፣ የሥራ ባህሪንና ተግባራዊ የውሳኔ አሰጣጥ ችሎታን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አጣምሮ የሚመዝን መሆኑ ተገለጸ።
ምዘናው እያንዳንዱን የብቃት ዘርፍ እንደ አስፈላጊነቱ የተለያየ የክብደት ድርሻ በመስጠት የሠራተኞችን አጠቃላይ አቅም ለመገምገም የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ብቁና ውጤታማ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ማረጋገጥ ነው።
በምዘናው ውስጥ ከፍተኛውን 50 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የቴክኒክ ብቃት ምዘና ነው። ይህ ክፍል ሠራተኞች ከተሰማሩበት የሥራ መስክ ጋር በቀጥታ የተያያዙ 15 ወሳኝ የዕውቀትና የክህሎት ዘርፎችን ይመዝናል።
ከእነዚህም መካከል የፖሊሲ ልማትና ትንተና፣ የዕቅድና ፕሮግራም አስተዳደር፣ የክትትልና ግምገማ፣ የምርምርና የውሂብ ትንተና እንዲሁም በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የመሥራት አቅም ይገኙበታል።
በተጨማሪም የፕሮጀክት፣ የአደጋ፣ የጥራት፣ የመረጃ፣ የፋይናንስ፣ የግዥና ውል አስተዳደር፤ የቁጥጥርና ፍተሻ ክህሎት፣ የሪፖርት አጻጻፍና ሰነድ ዝግጅት፣ የአይሲቲና ዲጂታል ክህሎት እንዲሁም ከየሥራ መስኩ ጋር የተያያዘ ልዩ ሙያዊ ዕውቀት በዚሁ ምዘና ይካተታሉ።
ሁለተኛው የምዘና ክፍል 30 በመቶ ድርሻ ያለው የባህሪ ብቃት ሲሆን፣ የሠራተኞችን የሥራ ባህሪ፣ አመለካከትና ማኅበራዊ መስተጋብር በ12 መመዘኛዎች ይገመግማል።
በዚህ ክፍል ታማኝነትና ሥነ-ምግባር፣ ለሕዝብ አገልግሎት ያለ ቁርጠኝነት፣ በዜጋ ላይ ያተኮረ አገልግሎት፣ ሙያዊነትና ተግሣጽ የሚመዘኑ ዋና ዋና እሴቶች ናቸው።
የመግባባት ክህሎት፣ የቡድን ሥራና ትብብር፣ የመሪነት ችሎታ፣ የለውጥና የግጭት አስተዳደር፣ ችግር የመፍታት አቅም፣ የውሳኔ አሰጣጥና በውጤት ላይ ያተኮረ አስተሳሰብም በምዘናው የሚካተቱ መመዘኛዎች ናቸው።
ቀሪውን 20 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የሁኔታ ግምገማና የጉዳይ ትንተና ክፍል ነው። ይህ ምዘና ሠራተኞች በሥራ ላይ ሊያጋጥሟቸው በሚችሉ እውነተኛና ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ የሚወስዱትን እርምጃ ይፈትሻል።
በዚህም ሠራተኞች የሚቀርብላቸውን የሥራ ጉዳይ በመተንተን ተገቢ መፍትሔ የማቅረብ አቅማቸው፣ ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ ችሎታቸውና ውሳኔ የመስጠት ብቃታቸው ይገመገማል።
የብቃት ማዕቀፉ ከምዘና መስፈርቶቹ በተጨማሪ ሠራተኞችን በየዕድገት ደረጃቸው ከጀማሪና መካከለኛ እስከ ከፍተኛና ልዩ ባለሙያ ድረስ ይለያል።
በተለይም በዳይሬክተር ደረጃ ላይ ለሚገኙ አመራሮች ስትራቴጂካዊ መሪነት፣ የፖሊሲ ትርጓሜና ትግበራ፣ በአደጋ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የተቋምና የአፈጻጸም አስተዳደር እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የማረጋገጥ ብቃቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በአጠቃላይ የተቀናጀው የብቃት ምዘና ማዕቀፍ የመንግሥት ሠራተኞችን በሙያዊ ዕውቀት፣ በተግባራዊ ክህሎትና በሥነ-ምግባር ለመገምገም የተዘጋጀ ሲሆን፣ ብቁና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት ለመገንባት ያለመ ነው።
