
የሶማሌ ክልል ህዝብ “ወደ ጫካ ተመልሶ ሰላሙን የሚያውክ ኃይል” አይፈልገም ሲሉ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ረሺድ ተናገሩ።
የሶማሌ ክልል ህዝብ ለዘመናት የነበሩት የልማትና የሰላም ጥያቄዎች “ባለፉት የለውጥ ዓመታት መመለሳቸውን” አቶ አብዱልቃድር ትናንት በሰጡት መግለጫ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
ይህንን ሰላም “ለማደፍረስ የተለያዩ ኃይሎችና ግለሰቦች የሚያሰራጩትን የፀረ-ሰላም መልዕክቶች የክልሉ ህዝብና መንግሥት እንደማይታገስ” ተናግረዋል።
ለክልሉ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ አካላትና ኃይሎች፣ የተፈቀደው የትግል አይነት ሰላማዊ ትግል ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ያሉት አቶ አብዱልቃድር፤ “ወደ ጫካ ተመልሶ የሚደረግን ትግል” የሶማሌ ክልል ህዝብ እንደማይፈልግ አስገንዝበዋል።
ይሁን እንዲ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው እነዚህን ያስጠነቋቋቸውን አካላት “ኃይሎችና ግለሰቦች” ከማለት ውጭ በስም አልጠቀሱም።
አቶ አብዱልቃድር “በሀገርም ሆነ በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን” ጠቁመው፤ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የፖለቲካ አቋማቸውን ለማራመድ የተመዘገቡት ቡድኖች የህዝቡን ሰላም በማያውክ መንገድ በመንቀሳቀስ፣ አብሮነትን ከሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎች እና ፕሮፓጋንዳዎች መቆጠብ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
ኃላፊው ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት በቅርቡ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ እና የክልሉ መንግስት በመግለጫ መወቃቀሳቸውን ተከትሎ ነው። የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ የካቲት ወር መገባደጃ ላይ “በክልሉ ሙስና ተንስራፍቷ፤ ፕሮጀክቶች ተንጓተዋል” ሲል ያቀረበውን ክስ የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፤ “ሀሰት” እና “ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው” ሲል ውድቅ ማደረጉን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል።
ቢሮው መረጃው የፓርቲው መግለጫ “በህዝብና በመንግስት መካከል ጥርጣሬ ለመፍጠር ያለመ” እና እንደ ጤና ፣ ትምህርት ፣ ንጹህ ውሃ ፣ የከተማ ልማት እና የመንገድ ግንባታ ባሉ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ጥረቶችን ለማዳከም የተቀናጀ ጥረት አካል ነው ሲል ተችቷል።