ባሳለፍነው ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አንብሮተ ዕድ ተፈጽሟል፡፡ በዕለቱ በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉ ብፁዓን አባቶች መካከል አንዱ ደግሞ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በንግግራቸው በበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች፣ ማኅበራት እና ሊቃውንት ጥያቄ ሲነሳበት የነበረውን ይኽንን ሢመት የተመለከቱ ሐሳቦችን እና ምላሾችን አንስተዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም የብፁዕነታቸውን ንግግር ሙሉ ክፍል ለአንባቢያን እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ!
‹‹ማእረሩሰ ብዙኅ ወገባሩ ኅዳጥ፡፡ ሰአልዎ እንከ ለበዓለ ማእረር ከመ ይወስክ ገባረ ለማእረሩ››
(ማቴ 9፥37)
“መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደመከሩ ሠራተኞች እንዲልክለምኑት” ማቴ. 9፥37 አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አልጫ ዓለም ለማጣፈጥ በማስተማር፤ ሕሙማንን በመፈወስ፤ ሙታንን በማንሣት፣ ርኁባንን በመመገብ ለሰው ልጆች ያላደረገው ነገር የለም፡፡ ከዚህም በላይና ይህን ሁሉ እያደረገ ለጐደላቸው እንዲያስተውሉ፤ ርኅራኄ ለሌላቸው ርኅራኄ እንዲኖራቸው ከላይ በተጠቀሰው አምላካዊ ቃሉ መክሯል፤ መመሪያም ሰጥቶአል፡፡ ኀዘኑንም ሲገልጽ ‹‹ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው፡፡ (ማቴ 9:36) ዛሬም በዘመናችን የተጣሉ ተመልካች ያጡ የተበተኑ ሰብሳቢ የሌላቸው ፍቅረ እግዚአብሔርን፣ ፍቅረ ቢፅን የተራቡ መጋቢ የሌላቸው የጠፉ ፈላጊ የሌላቸው የብዙ ብዙ ናቸው፡፡ ዋይታቸው ጩኸታቸው በስም ብቻ ጠባቂዎች እረኞች ሰብሳቢዎች የተባልነውን በዘመኑ ያለነውን ይከሳል፣ ይወቅሳል፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ “ጆሮ ዳባ ልበስ” እንዲሉ እኛም ለመስማት ኀላፊነታችንን ለመወጣት በርኅራኄ በፍቅር ለመጠበቅ አልታደልንም፡፡ ምክንያቱም ከዓላማችንና ከተልእኮአችን ወጥተን የዓለሙ ጠባይና ማዕበል ቀዛፊና መልሕቅ እንደሌለው መርከብ ዮኅሊና ዕረፍት ነሥቶ ስለሚያገላታን ነው ለማለት አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ዛሬም አለን ለማለት ብንጥርም ጥቂቶች ነን መከሩ ብዙ ነውና ሠራተኛ ያስፈልጋሉ በሚል ቅዱስ ሲኖዶስ እረኞችን መርጧል፤ ሠይሟል፡፡ የአሁኑን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና ሢመት ልዩ የሚያደርገው በ205 ዓ.ም በወርኃ ጥር መከሩን (ምእመናንን) ምክንያት በማደረግ በቋንቋ በፖለቲካ በዘር ተጠልፈን ለተፈጠረው ችግር በቤተ ክርስቲያን ሕግና ቀኖና ብቻ ሳንወሰን ክቡር ምንስትሩ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የተደረገውን ስምምነት ማዕከል አድርጐ የተካሄደ ምርጫና ሢመት መሆኑ ነው፡፡
ከዚህም የተነሣ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያልተለመደና እንግዳ ነገር (ደራሽ) በመሆኑ ሊቃውንቱ ፤ ካህናቱ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለምን? እንዴት? ብሎ ከመጠየቅም አልፎ ጽፈዋል ፤ ተችተዋል ፤ አባቶችንም ተማፅነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስ የሊቃውንቱን ጩኸት የሁሉንም ወገኖች ጥሪ በማቃለል ሳይሆን ችግሩ በተፈጠረ ጊዜ የሞት ሰለባ የሆኑ ካህናት ፤ ምእመናን ወጣት አዛውንት መከራና ሐዘን ከህሊናችን ሳይወጣ የታሰሩት የድረሱልኝን ጥሪ በጆሮአችን እየቃጨለ ከሥራ የተፈናቀሉት ተራብን ተጠማን አቤቱታ ሳይቋረጥ ስምምነት ጥሰን በቀኖና ቤተ ከርስቲያን ብቻ ይሁን ብለን ብንወስን ወደኋላ ተመልሰን ካህናቱን ምእመናንን ለመከራ አሳልፈን ላለመስጠት ጳጳሳት ሆናችኋል ከተባሉ በኋላ በስምምነቱ መሠረት ያወለቁትን ልብስ ጳጳሳት እንደገና ለብሰው እንዳይሰማሩ ቀኖናን በቀኖና በማስተካከል ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አጽድቆ መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው ብሎ ተቀብሎታል፡፡
ይኸም ሆኖ ውጤታማ መሆን ከተቻለ ተመስገን የሚያሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተ ከርስቲያኒቱ ፈተና ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆን ሁላችንም መለያየቱን ትተን በአንድነት መተቸቱን ትተን በስምምነት በመመካከር አባቶቻችን እና እናቶቻችን እንዲት ቤተ ክርስቲያን ሁሉ እኛም ለነገው ትውልድ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንድናስረክብ እረኞች ለመነው መንጋው ለእረኞ የአባቶች ለምእመናን ምእመናን ለአባቶች ርኅራኄና ፍቅር ይኑረን፡፡
በሃይማኖታችን ምንጊዜም ከማንም ከምንም ጋር አንደራደር፡፡ ይልቀንም አባቶች፣ ሊቃውንት፤ ካህናት፤ እረኛ እንደሌላቸው በች ተጨንቀው የሚገኙትን ወገኖቻችን ለማገልገል እንትጋ! በተለየ ሐሳብ ሳይሆን በአንድ ሐሳብ በየቋንቋቸው ለአንዲት እናት ቅድስት ቤተ ከርስቲያን እናስተምራቸው፣ ለመንግሥቱ ሰማያትም በቅተን እናብቃቸው፡፡ “የመከሩን ጌታ ወደመከሩ ሠራተኞች እንዲልከ ለምኑት በተባለው መሠረት እንለምነው፡፡ ምንም እንኳ ከላይ እንደገለጽኩት የአሁኑ ምርጫና ሢመት በምክንያት ቢፈጸምም ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አልሆነምና ሁላችንም እንቀበለው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ለመንጋው ጠባቂዎች ትሆኑ ዘንድ የተጠራችሁና የተመረጣችሁ ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳትም የኦርቶዶክሳውያን ሁሉ አባቶች ናችሁና መለያየትንና ጥላቻን በማውገዝ አንድነትንና ፍቅርን በማስተማር ጥንታዊት ሐዋርያዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቃችሁ እንድታስጠብቋት ፤ የጠራችሁና የመረጣችሁ መንፈስ ቅዱስ መክሊቱን ሰጥቶአችኋል፡፡ ማትረፍ ማብዛት ከእኛና ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ የጠራችሁን የመረጣችሁን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡ ለዚህ ታላቅ ሐዋርያዊ አገልግሎት በመመረጣችሁ ደስ ብሎናል፡፡ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ከህነት ስም መልካም የሥራና የአገልግሎት ዘመን ይሁንላችሁ፡፡
ብፁዕ አብርሃም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
