
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባለንበት ወቅት የገጠማትን ቀናኖዊ እና ሃይማኖታዊ ችግር አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል ፤ እያሳለፈም ይገኛል፡፡ እኛም እነኚህን መግለጫዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የመጀመሪያ ውሳኔ
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ እንዲሁም በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
በዚህም ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሶዶ ዳጩ ወረዳ፣ ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአባ ሳዊሮስ መሪነት እጅግ አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አንዱ ሲሆን፤ በአባ ሳዊሮስ መሪነት የተፈጸመው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፳፮ መነኰሳትን ከቀኖና የወጣ ሢመት በመስጠትና ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ ሃይማኖትን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት … የሚያጋጭና ደም የሚያፋስስ ፀጥታን የሚያናጋ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝቧል፤ በመሆኑም፤
ሐዋርያት በሦስተኛው ቀሌምንጦስ በሃያ አምስተኛው አንቀጽ “በአውራጃው ሁሉ ያሉ ኤጲስ ቆጶሳት አለቃቸው ማንም እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ አለቃ ያድርጉት፤ ያለ ፍቃዱ ጥቃቅኑንም ደጋጉንም ሥራ ምንም ምን አይሥሩ፤ እርሱም ዳግመኛ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሳይፈቅዱ ደጋጉን ሥራ አይሥራ ጥቃቅኑን ቢሠራ እዳ የለበትም፡፡ ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ ሁነው በአንድነት ይኑሩ” ብለው ወስነዋል፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ይህን የሐዋርያት ቀኖናን በመሻራቸው፡፡
ሁለተኛም በአርባ አራተኛው አንቀጽ “ሊቀጳጳሳት (ፓትርያርክ) ኤጲስ ቆጶሳት በተሾሙባቸው አገሮች የሚሠሩትን ሥራ፣ የሚያዙትን ትእዛዝ ይመርምር፡፡ የማይገባ ሥራ ሠርተው፣ የማይገባ ትእዛዝ አዝዘው፣ ቢያኝ ለውጦ የተገለጸለትን ትእዛዝ ይዘዝ፡፡ እርሱ ለሁሉ የሹመት አባታቸው ነውና፤ እነሱም ልጆቹ ናቸውና…” ብለዋል፡፡ ይህን ኢ-ቀኖናዊ ሥርዐተ ሲመት የፈጸሙት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ በአደባባይ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን እና የቅዱስ ፓትርያርኩን መብት በመጣሳቸው፡፡
ሢመተ ክህነትን በተመለከተ “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር … እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም” (ዕብ 5፤4) እንደሚለው የእግዚአበሔር ቃል ከዲቁና ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ሹመት ድረስ ያለው ሹመት በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መጠራቱን የሚጠይቅ ሲሆን እንኳንስ ለተሿሟዎች ለመራጮችና ለአስመራጮች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርት ያለው፣ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልእክቱ በሰፊው ገልጾታል፡፡ (ጢሞ.3፣10፣ ቲቶ፣ 1፣5-7 ፍትሕ መን አንቀጽ 4)
ይህንም ቅዱሳን ሐዋርያት ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በ3ኛው ቀሌምንጦስ “ኤጲስ ቆጶስ የሀገሩ ሰዎች፣ የሀገሩ ጳጳስ፣ ፈቅደውለት ይሾም፤ ቢገኙ ሦስት፣ ባይገኙ ሁለት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ሁነው ይሹሙት” ብለዋል፡፡ ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ በሌለበት ሀገር፣ ፓትርያርክ በሌለ ጊዜ ምእመናን እንዳይበተኑ ተብሎ የሚደረግ ነው እንጅ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን በመጋፋት የሚፈጸም ከሆነ ግን ይህን ቀኖና በሕገወጥ መንገድ ለተፈጸመ ድርጊት መጥቀሱ በቅዱስ ወንጌል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል እንደመናገር ተቆጥሮ የማይሠረይ ኃጢአት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ (ማቴ.12፣30-32 ሉቃስ 12፣10፣ ማርቆስ 3፡28-29 1ኛ ጢሞ 1፣13) የእነዚህ ሰዎች ተግባር በሥራ ላይ ያለውን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ የመፈንቅል፣ የታላቋን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የመናድ፣ ሕጋዊ ተቋምን የማፍረስ ወይም የመናድ ተግባር በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዟል፣
ሠለስቱ ምዕትም ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በኒቅያ በጻፉት ቀኖና በዘጠነኛው አንቀጽ አንዱም አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾም ቢሻ፣ የሀገሩ ሰዎች ቢፈቅዱለት፣ የሀገሩ ጳጳስ ካልፈቀደለት ኤጲስ ቆጶስነት መሾም አይገባውም ይህን አፍርሶ ቢገኝ ሲኖዶስ ያወግዘዋል፤ ሹመቱም ይቀራል” ብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ወቅት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲየን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ስልጣን በመጋፋት በድፍረት ተፈጸመ የተባለው ሹመት አስቀድሞ በአበው ቅዱሳን የተወገዘ ነው፤
ከዚህም ጋር ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት በሚፈጸምበት ጊዜ፣ ያለ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ማንም ወደ ቤተ መንግሥት እንዲሔድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይፈቅድም፡፡ ይህንንም የተላለፈ ቢኖር ከጳጳሳና ከኤጲስ ቆጶሳት ማንም ማን ሊቀጳጳሳቱ ሳይፈቅድለት ወደ ንጉሥ ቤት አይሒድ ወለኲሉ ዘዐለወ ዘንተ ሲኖዶስ ያወግዞ ይህን ትእዛዝ ያፈረሰውን ሲኖዶስ ያወግዘዋል” ተብሎ ስለተወሰነ ዛሬም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ውጭ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ሕገወጥ በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን … ሰው ሁሉ ማዕርጉን ጠብቆ ይኑር እንጅ፣ አንዱ ወደ አንዱ ማዕርግ አይተላለፍ፤ ይህን የሠራነውን ሥርዐት ያፈረሰውን ሰው ሲኖዶስ ያወግዘዋል ተብሎ በተጻፈው መሰረት እነዚህ ሕገወጥ አካላት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ የጣሰ በመሆኑ፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና መደንገጉ፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 5 የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሕግጋትንና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ /ኤጲስ ቆጶስ/ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዟቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በአጠቃላይ ተቀባይት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ
1ኛ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጩ ወረዳ ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ
1ኛ. አባ ሳዊሮስ
2ኛ. አባ ኤዎስጣቴዎስ
3ኛ. አባ ዜና ማርቆስ
የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 26 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት በማኅህበራዊ እና በብሮድካስት ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ድርጊታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ ለይቷቸዋል፡፡
በመሆኑም፡-
ሀ. ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤
ለ. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡
ሐ. በነዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ በለያቸው ግለሰቦች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት በማከናወን ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ ብፁዐን አባቶችን
• ለደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት
• ለኬንያ፤ኡጋንዳ፤ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ሀገረ ስብከት
• ለኢሉ አባቦራ እና በኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
• በሰሜን አሜሪካ ለሜኒሶታ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት
• ለጉጂ፤ ምዕራብ ጉጂ እና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት
• ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም
በአባትነት የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
ይሁን እንጅ ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል፤
2. የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሺመት አግኝተናል፤ ተሸመናል እያሉ የሚገኙ 25 መነኰሳት በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል፡፡
3. ከነዚሁ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ጸጋዘአብ አዱኛን ከቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ ስብሰባ በፊት የቀኖና ጥሰቱንና ሕገ ወጥ አድራጎቱን በመረዳትና በመጸጸት ድርጊቱን በመቃወም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ባቀረቡት የይቅርታ አቤቱታ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታውን የተቀበላቸው ሲሆን እንደሳቸው ሁሉ ከላይ የተወገዙት 25 ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን እንገልጻለን
4. በዚህ ጸረ ቤተ ክርስቲያን እና ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ እየኖሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወይም በቦታው በመገኘት የጥፋት ድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን በተመለከተ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተገቢውን ክትትልና አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ፤
5. ይህን ታሪክ ይቅር የማይለውን ሕገ ወጥ አድራጎት እና የቀኖና ጥሰት በሐሳብ፤ በገንዘብ እና በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ እና በማድረግ ላይ ያሉ ማናቸውም ተቋማት እና ግለሰቦች ከዚህ ሕገ ወጥ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ ባይሆን በሕግ አግባብ ተገቢው እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
6. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማህበራት እና ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኃላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፤ ዓርማዋን፤ አድራሻዋን፤የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያ ቅዱሳትንና አልባሳት እንዲሁም መጻሕፍት መገልገል የማይችሉ መሆኑ ታውቆ ይህንን ጉዳይ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በተጨማሪም ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ተገቢውን ሕግ አግባብ ተከትሎ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለማት የሚያስፈጽም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሁሉ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
8. አሁን የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲሰየም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
9. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ከክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጃው ላሉት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲከናወኑ እና ይህ ውሳኔ ከሸኚ ደብዳቤ ጋር እንዲደርሳቸው ተወስኗል፡፡
10. ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ክፍለ ዓለማት ለሚገኙ የቤተ ክርስቲኒቱ አገልጋዮች እና ምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረኮች እንዲካሔዱ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በማእከል የአህጉረ ስብከት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ታላቅ የንቅናቄ እና የግንዛቤ መድረክ እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
11. በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ መንግስታዊም ሆነ መነግስታዊ ያልሆነ ተቋማት፤ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት፤ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት ጉባዔ እና ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች በሙሉ እነዚህ የተወገዙት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ማናቸውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኑቱ ስም እንዳያደርጉ በጽሑፍ አንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
12. እነዚህ ግለሰቦች ከሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ አንዱ እኩይ ተግባራቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ማስመሰል ሲሆን ይኽ ተግባር ሃይማኖቱን የሚወድ፣ አባቶቹን የሚያከብር እና አስተዋይ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ የማይወክል፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ያደረጉት ሕገወጥ የቀኖና ጥሰት መሆኑ እንዲታወቅ፤ በተጨማሪም ለሚያሠራጩት የሐሰት አሉባልታ ወደፊት ተገቢው መልስ እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤ እስከ አሁን ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሆን አጋርነታችሁን ያሳያችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የበኩላችሁን በመወጣት መግለጫ የሰጣችሁ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እያመሰገንን ለወደፊቱም በጸሎታችሁ እና በመልካም አጋርነታችሁ ከጎናችን እንድትሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ለሚመለከተው ሁሉ
እሁድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት በተፈጸመው የሕግ ጥሰት 26 ኤጲስ ቆጶሳት በመሾማቸው፣ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቋሚ ሲኖዶስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ላሉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት አስቸኳይ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
ጥሪ የተደረገላቸው አባቶችም በቅጽበት ደርሰው ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ አድርገው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ኢሕጋዊ ድርጊት ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸው በዚያው ዕለት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም በተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በሰፊው ተገልጿል፡፡
መግለጫውን ያዳመጡ በውስጥም በውጭም ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ሁሉ ብርቱ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት እና መንፈሳውያን ተቋማት ድጋፋቸው ከመግለጻቸው በላይ የታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ኅብረት ተጠብቆ እንዲኖርም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
እኛም ድጋፋቸውንና መልካም ምኞታቸውን ስለገለጹልን የላቀ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፤ ምስጋናችን በያሉበት ይድረሳቸው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎች የክርስትናና የእስልምና መሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው ድንገተኛ ክስተት ተደናግጠውና ተጨንቀው መጥተው የችግራችን ተካፋይ መሆናቸውን በመንፈሳዊ ስሜት ገልጸውልናልና ምስጋናችን ይድረሳቸው፤ እግዚአብሔርም ያክብራቸው እንላለን።
አሁንም በድጋሚ ለመንግሥትና ለሰፊው ሕዝባችን የምናስተላልፈው የአደራ መልእክት አለን፤ እሱም፡-
1. የታሪካዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት (ቀኖና) እንዲከበርልን፤
2. ጸጥታ እንዳይደፈርስና የንጹሐን ክርስቲያን ደም እንዳይፈስ ከወዲሁ ብርቱ ጥንቃቄ የተመላበት ጥበቃ እንዲደረግ በእግዚአብሔር ስም በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
ለጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠው ምላሽ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ማብራሪያ ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ።
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ የሃይማኖት፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት አስመልክቶ በሰፊው ተወያይቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ልዩ ልዩ ሕግጋት ውጭ ጳጳስ ሾመናል ባሉ አካላት እና ተሹመናል በሚሉት አካላት ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት በሚፈቅድለት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ የለያቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ይኸው ውግዘት በመላው ዓለም ለሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ውግዘቱን እንዲያውቁት መንግሥትም በዚህ ጉዳይ የሚፈጠር ችግር እንዳይኖር ሰላም እንዲያስከብር ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ኖሮት ቤተ ክርስቲያን ለወሰነችውም ውሳኔ ግንዛቤ እንዲወስድ በመግለጫ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡
በዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆኑ አገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን በመላው ዓለም የሚገኙት ደስታቸውን በመግለጥ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ሳይሸራረፍ እንደሚያስፈጽመ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት የተፈጸመውን ድርጊት በመቃወም እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የወሰነችውን ውሳኔ በመደገፍ ከጎናችን እንደሆነ እና አብረውን እንደሚሰሩ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹልን ይገኛል፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ከጎናችን ለቆሙትና ድጋፋቸውን ለገለፁልን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሃይማኖት እና የሲቪክ ተቋማት ምስጋናዋን አቅርባለች። እነዚህ በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላትም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከማዕከላዊ መዋቅር ውጭ ተወግዘው ተለይተው እያለ በሌላቸው ሥልጣን ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት በታዎች በመግባት በሚያደርጉት ግብ ግብ በዕምነቱ ተከታዮች፣ በማህበረ ካህናትና ምዕመናን ላይ ሁከት እየተፈጠረ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንግሥት ያቀረበችው ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማስፈን ሥራ ጥሪ ተቀብሎ በሕገወጦች ላይ የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ እየታየ አለመሆኑም ታውቋል፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈፀም መንግሥት ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታያለፈውን ጉዳይ በጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሚኒስትሮችና ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በማንሳት ልዩ ልዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
ይኸውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ሲኖዶሱ እና ውጭ ባሉ አባቶች መካከል ሲካሄድ የነበረውን የዕርቅ ሒደት እልባት እንዲያገኝ ማድረጋቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችና ሕንጻዎች መካከል 4ኪሎ የሚገኙትን ሁለቱን ቀደምት ሕንጻዎች ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሀገረ ስብከት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሥሪያ ቦታ ማድረጋቸው! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗን መግለጻቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗ መዳከም ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን ለሀገረ መንግሥቱም ጭምር መሆኑን መግለጻቸው፣ አግባብነት ያለውና ለዚህም : አድራጎታቸው ቤተ ክርስቲያናችን በወቅቱ በእውቅና ሽልማት አጅባ አመሰግናለች፡፡ ሆኖም ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎች በተላለፈው 36 ደቂቃ በሚፈጀው በሰላምና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት የሰጡትን ማብራሪያ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ተመልክታዋለች፡፡ በመሆኑም በቀረበው ማብራሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አቋም እንደሚከተለው በዝርዝር እንገልጻለን፡፡
1. መንግስት በቤተ ክርስተያናችን የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናው ጥሰትን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት አቅልለው በአሁኑ ወቅት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ጉዳይ በጣም ቀላል ነው” በማለት ያዩበት መንገድ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩ ቀላል እና በንግግር የሚፈታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህ አገላለጽ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ከዚህም አልፎ ሁለቱም ወገን ውስጥ እውነት አለ፣ ሁለቱም አባቶቻችን ናቸው፣ ለማንም አንወግንም፤ ማንም የካቢኔ አባል እዚህ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ፣ የሚሉት አገላለጾች በሕግ እውቅና የተሰጣትን ቤተ ክርስቲያን እና በሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተነሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖች በአቻ እይታ ተመልክተው ሊወያዩ ይገባል በማለት የስጡት ማብራሪያ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሕጋዊ ተቋማት መንግሥት ያለበትን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ያደረገ፣ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲታመሱና እንዲተራመሱ ይሁንታ የሚሰጥ፣ ሕግንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ታሪክና የሀገር ባለውለታነትዋን ያላገናዘበ፣ ማብራሪያ በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
ከዚህም በተጨማሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውም ካቢኔ በዚህ ጉዳይ እጁን እንዳያስገባ በማለት የሰጡት የሥራ መመሪያ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ሰውነት አክብረው እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉትን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደርግና በሕገመንግሥቱ ለአስፈጻሚው አካል የተሰጠውን ሥልጣን የሚሽር፤ ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያበረታታ፤ የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አድራጎት በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትና የተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል፡፡
በሕገ መንግሥቱ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በግልጽ የተደነገገ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ላይ እጁን ማስገባት እንደሌለበት የምናምንበት ሐቅ ሲሆን ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጭ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመውን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ጥሰትን እንደተራ ግጭት እና የግለሰቦች አለመግባባት በመቁጠር ትንታኔ ለመስጠት የተሄደበት ርቀት ሲታይ በአሁኑ ሰዓት ሕጋውያን የሆኑትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ከኤርፖርት ታግተውና ለሃይማኖታዊ አምልኮ የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያን አዝኖ እንዲበተን በማድረግ ለአንድ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ሊቀጳጳስ የማይመጥን እንግልትና ማዋከብ መደረጉ ሳያንስ ይባስ ብሎ ለሕገወጡ የቡድን አባላት
ለአብነትም ያህል በምዕራብ ወለጋ፤ በምሥራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋና ሆሮጉድሩ ዞኖች በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አባላት ልዩ የፓትሮል እጀባና እንክብካቤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ተቋማት በሕገወጥ መንገድ ተደፍረው እንዲገቡ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮና የአስተዳደር ተቋማት ተሰብረው በሕገወጥ ቡድኖች እንዲወረሩ መደረጋቸው፤ ይህን ሕገወጥ አድራጎት የተቃወሙትን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት አባቶችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለእስር እንዲዳረጉ መደረጉ፣ ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ተሽከርካሪ መኪኖች ለማንኛውም
አገልግሎት እንዳይንቀሳቀሱ፣ በክልሉ መንግሥት አመራር ተሰጥቷል በሚል እገታ መከናወኑ ሲታይ መንግሥታችን ሕገመንግሥታዊ ጥስት በመፈጸም በሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱንና በእርሱም ይሁንታ መፈንቀለ ሲኖዶስ እየተከናወነ እንዳለ እምነት የሚያሳድር በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልናና መብት እንዲያስከብር ንብረቶቿ በሕገወጥ ቡድኖች ከመወረር እንዲጠብቅ፣ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትና የሥራ ኃላፊዎች ያለምንም እንግልትና የደህንነት ስጋት ተመድበው ሲሠሩባቸው በቆዩበት አህጉረ ስብከት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃና የሕይወት ዋስትና እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
2. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቀደምት ሥርዓተ መንግሥታትን በዋቢነት አሁናዊው የብልጽግና መንግሥት በውጭ የነበረውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በእርቅ አንድ ማድረጋቸውን ሲገልጹ በሀገር ውስጥ ሁለት መንበርና ሁለት የፕትርክና መሪነት እንደነበረ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ፡- በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተከሰተውን ልዩነትና የሲኖዶስ መከፈል በእርቀ ሰላም ማለቁ የማይካድ ሐቅ ቢሆንም በተፈጸመው የእርቅ ስምምነት ውሳኔ መሠረት በግልጽ እንደሰፈረው ሁለት ፓትርያርክ በአንድ መንበር ላይ የነበረ ሳይሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ክብራቸው ተጠብቆ በጸሎትና ቡራኬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በአባትነት እንዲያገለግሉ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ የመሪነት ሥራን በአባትነት እንዲመሩ በግልጽ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ በውሳኔው መሠረት ተግባራዊ የሆነና በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚታወቀውን እውነታ በሚንድ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንድ መንበር ሁለት ፓትርያርክ ሲመራ ቆይቷል ተብሎ የተገለጸበት አካሄድ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን
በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራር በመጣስ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈጸመውን “ሢመተ ጵጵስናና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግከው የተለዩት ግለሰቦች ቀድሞውንም ሹመቱን ፈጽመን በዕርቅ እና በድርድር አንድ እንሆናለን : በሚል ሲገልጹት የነበረውን ሀሳብ የሚያረጋግጥና አሁንም በድርድር ሃይማኖታዊ መመሪያችሁን ጥሳችሁ ቀኖናዊ ሥርዓታችሁን አፍርሳችሁ፤ አስተዳደራዊ መዋቅራችሁን ንዳችሁ ተቀብሏቸው እንደማለት የሚያስቆጥር ማብራሪያ አዘል መመሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
3. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈጸመው የእርቀ ሰላም ሂደት ወቅት በውጭ ሀገር የነበሩት አባቶች ሹመታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሀገር ሊገቡ የቻሉት በየደረጃው አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው ነው በማለት የሰጡትን በተመለከተ፡- በውጭ የነበሩ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት በእርቀ ሰላሙ ወደሀገር ተመልሰው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊሆኑ የቻሉትና ተቀባይነት ያገኙት ሹመታቸው የተከናወነው በቀኖና ጥሰት ሳይኖን በሕጋዊ ፓትርያርክ የተፈጸመ ሲመት ከመሆኑም በላይ በስደት ሊቆዩም የቻሉት በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ጫና እየታወቀና ከአሁኑ ሕገወጥ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ መሠረት የሌለው ሹመት ጋር ግንኙነት የሌለው ሆኖ እያለ ሕጋዊውን ከሕገወጡ ጋር በማቀላቀልና በማነጻጸር የተሰጠው ማብራሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
4. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በቋንቋ የመገልገል መብትን መንግሥት ማፈን አይችልም በማለት የተሰጠው ማብራሪያ በተመለከተ፡- እናት ቤተ ክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኳ እንደሚያረጋግጠው የቋንቋ አገልግሎትን በሕጎቿ እውቅና የሰጠች፣ ከዚህም አልፎ በተለይም ግለሰቦች በተደጋጋሚ በሚጠቅሱት በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእምነት ተከታዮች የቋንቋ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየች በመሆኑ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን
የአምልኮና የሥርዓት መጻሕፍቶች በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተርጎም ለአገልግሎት ያበረከተች፣ ሕገወጥ ሹመቱን ከፈጸሙት ሦስቱ የተሻሩት ሊቃነጳጳሳት ጨምሮ በርካታ የቋንቋው ተናጋሪ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትን በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት መድባ አገልግሎት እየሰጠች የክልሉን ተወላጆች በቋንቋቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን እውቀት ቀስመው ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆነ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በመክፈት፤ በሁሉም አህጉረ ስብከት የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን አደራጅታ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋይ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ እና _ ሰባክያነ ወንጌል አስተምራ ለአገልግሎት አሰማርታ እያለች የቋንቋ አገልግሎትን እንደተቃወመችና ለአገልግሎቱም በሯን እንደዘጋች በሚያስቆጥር ሁኔታ የተሰጠው ማብራሪያ ከእውነታቸው የራቀና የሕገወጥ ሥልጣን ፈላጊዎችን ሕገወጥ አካሄድና መግለጫ እውቅና የሚሰጥ አድራጎት በመሆኑ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
5. ለቤተ ክርስቲያን ተሰጠ ስለተባለው ይዞታና ስለ ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የተሰጠውን ማብራሪያ በተመለከተ፣ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከአምልኮ ሥፍራ የመሬት ይዞታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች ቤተ እምነቶች በተሻለ መልኩ ከአንድ አንድ ሚሊዬን አርባ አምስት ሺህ ካሜ ይዞታ በላይ እንደተሰጣትና ይህም የይዞታ ስፋት ለሌሎች ቤተ እምነቶች በድምሩ ከተሰጠው በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ እና አዲስ ይዞታ እንደተሰጠ ተደርጎ በማስመሰል የተሰጠው ማብራሪያ ፍጹም ስህተት እና ሕዝብን የሚያሳስት በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ይኼውም ለቤተ ክርስቲያን ተሰጠ የተባለው ይዞታ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞውን በእጂ አድርጋ ለዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን ሕጋዊ ይዞታዋ እና ይሄው በካርታ ተረጋግጦ እንዲሰጥ ስትጠይቅ የቆየች ንብረቷ እንጂ እንደ አዲስ በሊዝ አዋጁ መሠረት በምደባ ያገኘችው አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በተገለጸው ልክ አልተሰጣትም እንጂ ቢሰጣት እንኳን ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ውስጥ ከ75% በላይ የሚሆነውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ቤተ እምነቶች በተሻለ የሰፋ ይዞታ ማግኘቷ እንደልዩ ጥቅም የሚያስቆጥር አይደለም፡፡ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ መሆኑ እየታወቀ፣ የውጪ መንግሥታት በዕርዳታ ለመሥራት ፈቃዳቸውን መስጠታቸው በራሳቸው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደበት የተገለጸ ሆኖ እያለ፣ መንግሥት ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት የቱሪስት መዳረሻ መሆኑ እየታወቀ የቤተ ክርስቲያን ሀብት ብቻ ተደርጎ ከፈረንሣይ መንግሥት የተገኘውን ድጋፍ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ ልዩ ጥቅም በማድረግ ማቅረብ አግባብነት የለውም፡፡
6. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልል ትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በወቅቱ ሰጥተውን የነበረውን መግለጫ አንድም ተቃውሞ ሳይቀርብበት አሁን በኦሮምያ ለተከሰተው ይህን ያህል ተቃውሞ አግባብ አይደለም በማለት የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በክልል ትግራይ የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ከሰጡት መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንደሚያውቀው የቤተ ክርስቲያኒቷን ሕጎችና ቀኖናዎች ጥሰው ሕገወጥ ሲኖዶስ አልመሠረቱም፤ ጳጳሳትንም አልሾሙም፣ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመውን ሕገወጥ ሹመትና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ለማድረግ በሚያስመስል ሁኔታ ሁለቱ የማይገናኙ ድርጊቶችን በንጽጽር የተሰጠው ማብራሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም መንግሥታችን በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና፣ በሕግ የተሰጣትን መብትና ጥቅም በማስከበር ሕገወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በደላችንን ለዓለም ሕዝብ ችግሩ ተፈቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕትን ድረስ በመክፈል የምናሳውቅ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ ይገልጻል፡፡