ስብሰባዉ ‹‹ፍትሃዊ የንግድ ፖሊሲዎችን›› ጨምሮ ‹‹በጋራ ፍላጎቶች እና ግቦች›› ላይ ያተኩራል ብሏል ዋይት ሀውስ፡፡
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የካናዳዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በታሪፍ ውዝግብ ውስጥ ቢሆኑም በንግድ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ለማድረግ ትናንት በሮም ተገናኝተዋል።
በአሜሪካዉ አምባሳደር መኖሪያ ቤት የተካሄደው መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ ፍትሃዊ የንግድ ፖሊሲዎች እና የሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ግንኙነትን ጨምሮ ‹‹የጋራ ፍላጎቶች እና ግቦች›› ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ውይይቱ የተካሄደው ካርኒ ከአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በታሪፍ ዙሪያ ከፍተኛ ውይይት ካደረጉ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ህዝባዊ በዓለ ሲመትን ምክንያት በማድረግ ነው።
የአሜሪካ እና የካናዳ ግንኙነት በከፍተኛ የንግድ መሰናክሎች በትራምፕ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን በእጅጉ አሽቆልቁሏል።
በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ዋሽንግተን በአብዛኛዎቹ የካናዳ ምርቶች ላይ 25በመቶ ታሪፍ እንዲሁም በካናዳ ዘይት እና ኢነርጂ ኤክስፖርት ላይ ደግሞ 10 በመቶ ታሪፍ ጥላለች፡፡
ትራምፕ ለንግድ አለመግባባቶች እና ለደህንነት ጉዳዮች መፍትሄ እንደሆነ በመግለጽ ካናዳ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንድትሆን ደጋግመው ሀሳብ ቢያቀርቡም ይህ ሀሳብ የካናዳ ባለስልጣናት ለሉዓላዊነታችን ስጋት ነዉ ብለው ውድቅ አድርገውታል።
