የኢትዮጵያ ነጋዴዎችና ላኪዎች የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የንግድ ሥርዓት በተሻለ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ ዩኬ ገበያ የመግባት ዕድላቸውን እንዲያሰፉ ጥሪ ቀረበ።
ይህ ጥሪ በአዲስ አበባ በተካሄደው የሥልጠና መድረክ ላይ የተላለፈ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ላኪዎች የዕድሉን፣ የመስፈርቶቹንና የተግባራዊ ሂደቶቹን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከዩኬ የንግድና ልማት መሥሪያ ቤት፣ ከብሪታንያ ኤምባሲና ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ፣ የዩኬ ገበያ ለመግባት የሚያስፈልጉ የጥራት ደረጃዎችና የቁጥጥር መስፈርቶች ተብራርተዋል።
አምባሳደር ብሩክ መኮንን እንደገለጹት፣ ቡና፣ የግብርና ምርቶችና ጨርቃጨርቅ በዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የወጪ ንግድ ዘርፎች ናቸው።
ሆኖም፣ የቀረጥ ቅናሹ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ላኪዎች ተወዳዳሪና ቀጣይነት ያለው ምርት ለማቅረብ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሥልጠናው ዓላማ የኢትዮጵያ ንግድ ተቋማት ወደ ዓለም አቀፍ የገበያ ሰንሰለቶች እንዲገቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸማቸውን በማሳደግ ለኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማገዝ ነዉ ተብሏል።
