የኢትዮጵያ ወጣቶችከግጭት ማገዶነት ወደ ግንባታ

Date:

በታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር )

በግጭት በሚታመስ ማኅበረሰብ ውስጥ ወንዶችን እና ወጣቶችን የግጭት ጠማቂዎች፣ ልጃገረዶችን እና ወጣት ሴቶችን ደግሞ ሰለባዎች አድርጎ መመልከት ተለምዷዊ እውነታ ነው፡፡ ይህ እምነት በተጨባጭ ማሳያዎች ሳይቀር ሊደገፍ የሚችል ነው፡፡

ምንም እንኳን አስተማማኝ የስታቲስቲክስ መረጃ ማግኘት ቀላል ባይሆንም የኢትዮጵያ ወጣቶች [በተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ባሉት] ግጭቶች ተጎጂ ከኾኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ግንባር ቀደም እንደኾኑ መገመት ይቻላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአንድ በኩል መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ አደረጃጀቶች ወጣት ወንዶችን ለእኩይ ዓላማ የማሰለፍ ጉዳይ በመኖሩ ነው።

በሌላ በኩል ስንመለከተው ደግሞ፣ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች በእነኚህ ግጭቶችና ጥፋቶች በመቶኛ ሲሰላ ከፍተኛውን የሰለባነት ደረጃ እንደያዙ መገንዘብ እንችላለን፡፡

በኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር አብዛኞቹ ወጣቶችና ሕፃናት መኾናቸው፣ በመንግሥት እና በአብዛኛዎቹ የሲቪክ ድርጅቶች ዘንድ በድህረ ግጭቶቹ ሰብዓዊ ተግባራት ላይ የተረባረቡበትን አመክንዮ ግልጽ ያደርገዋል።

“በርካታ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ከኾነ የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ ወጣቱ የሰላም ግንባታ ሂደት ተሳታፊ እንዲኾን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት መሠራት አለበት

ኢትዮጵያ ሰፊ የወጣት ሕብረተሰብ ክፍል ያላት ሀገር ናት፡፡ ከ15 እስከ 29 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል ‹‹ወጣት›› አድርገን የምንይዘው ከሆነ 28.4 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሕዝብ  ወይም በግምት 32 ሚሊዮን የሚኾኑ ዜጎች ወጣት ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት (81.4 በመቶ ገደማው) በገጠር የሚኖር ሲሆን ቀሪው 18.6 በመቶው ደግሞ የከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በመቶኛ ሲታይ በአንጻራዊነት አነስተኛ ቢመስልም፣ የኢትዮጵያ የከተማ ወጣቶች በተለይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጥ (dynamics) በመቅረፅ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶም በኢትዮጵያ የማይናቅ የፖለቲካ ኃይል ነበሩ፡፡  በንጉሠ ነገሥቱ፣ በወታደራዊ አስተዳደር እና በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥታት ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጦችን ለማድረግም ወጣቶች ፈር ቀዳጅ ነበሩ፡፡

የዘመናችን ወጣቶችም ኢሕአዴግ በግማሽ የጋገረውን ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ከምጣዱ እንዲያነሳ በማስገደድ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እነኚህ መደበኛ ያልሆኑ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ኤጄቶ፣ ዘርማ…) ከ2015 – 2018 በኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ለዘለቀው ተቃውሞ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወሳኝ ኃይል ኾነው በመውጣታቸው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሊመጡ ችለዋል፡፡ 

እዚህ ጋር የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ወጣት ወንዶችና ሴቶች መኾናቸውን ማወቅ ጠቃሚ ነው፡፡ ምናልባትም ይኽ የወጣቶች ጣምራ ሚና የኢትዮጵያ መንግሥት ወጣቶችን የመንግሥት ደህንነት ሥጋትም ዋስትናም አድርጎ እንዲመለከት ምክንያት ኾኖት ሊሆን ይችላል።

ይህ ጣምራ ባለሚናነት ሰፋ ያለ አንድምታ እንዳለው የ2004ቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እና የእርግዝና ቁጥጥር አዋጅ (VCP) (384/2004) የፖሊሲ ሰነዶች ማሳያ ሊኾኑ ይችላሉ።

ብዝኃ ወጣት (YouthBulge)

‹‹ብዝኃ ወጣት›› (Youth Bulge) በሕዝብ ምጣኔ ፒራሚድ ውስጥ ከፍተኛ የወጣት መቶኛ ቁጥርን የሚወክል ንባበቃል ነው፡፡ ሶሲዮሎጂስት ጉናር ሄይንሶን የወጣቶች መበራከት፣ በተለይም የወጣት ጎልማሳ ወንዶች ቁጥር ከመጠን በላይ መብዛት ወደ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ ጦርነት እና ሽብርተኝነት ሊያመራ ይችላል ብሎ ይከራከራል።

እንደ ሂንሶን ፣ ጋሪ ፉለር እና ጃክ ኤ ጎልድስቶን ፣ ሊዮኔል ቢነር  እና ሌሎች ማኅበራዊ የሥነ ሰብዕ (አንትሮፖሎጂ) ባለሙያዎች ዕምነት ደግሞ በፍጥነት እያደጉ ያሉ ወጣት ሕዝቦች ያሏቸው ሀገሮች ሥራ አጥ የሚኾኑበት ዕድል ከሰፋ ወደ አመፅ አልያም ለአሸባሪ ቡድኖች ምልምል የመኾን ዕድላቸው ሰፊ ነው።

የ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት፣ የ2000ዎቹ የምጣኔ ሃብት ውድቀት፣ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፋሺዝም፣ የ2010ሩ የዐረቡ ዓለም አብዮቶች እና ሌሎችም እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ሽብርተኝነቶች ከወጣቶች ቁጥር መብዛት ጋር የተቆራኙ ናቸው ብለው ይከራከራሉ።

ደካማ የፖለቲካ ተቋማት ያሏቸው አገሮች፣ ከወጣቶች ጋር ተያይዞ ለሚመጣ አመጽ እና ማኅበራዊ አለመረጋጋት በጣም ተጋላጭ ናቸው ሲሉም ያስጠነቅቃሉ። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት የማኅበራዊ ሳይንስ ምሑራን የወጣት ሕብረተሰብ ቁጥር መብዛት በመጥፎ ገጽታው ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑንም ያስረዳሉ።

ለወጣቶች ተስማሚ ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ተግባራዊ ከሆኑ ከወጣት ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሥጋት ወደ “ሥነ ሕዝብ ምጥጥን” (demographic dividend) ዕድልነት ሊለወጥ ይችላል። በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች ውስጥ እንደታየው በርካታ በሥነ ምግባር ተገርቶ እና በሙያ ሰልጥኖ በኢኮኖሚው መስክ የሚሳተፍ የማኅበረሰብ ክፍል የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ሊያሳድግ ይችላል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች መበራከትም የተቀናጀ ጥረት ቢደረግ ከችግር ይልቅ ወደ ዕድሉ የሚያመዝነው ለዚህ ነው። ለወጣቶች ተስማሚ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ፣ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር፣ የቤተሰብ ዕቅድ ትግበራዎች ተደራሽነትን ማሻሻል እንዲሁም የሕፃናትን ሞት መጠን መቀነስ ደግሞ ለዚህ መሠረታዊ የፖሊሲ ማዕቀፎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሰው ማሳሰቢያ እንዳለ ኾኖ፣ የ“ብዝኃ ወጣት” (youth bulge) ጽንሠ ሀሳብ ወጣቱን በአንድ በኩል እንደ አሉታዊ ኃይል በሌላ በኩል ደግሞ “በዕድሜ ከፍ ባለው ክፍል መመራት ያለበት” የማኅበረሰብ ክፍል አድርጎ ከማቅረቡ የተነሳ ወጣቱ ሕዝብን (ሀገርን) በሚመለከቱ ጥቅል ጉዳዮች በንቃት የመሳተፍ መብቱን አያበረታታም።

የዚህን ፁሑፍ የመጨረሻ ክፍል በነገዉ ዕለት ይዘን እንቀርባለን።

This project implemented by Youth and Cultural Development Foundation (YCDF) is supported by The Fund for Local Cooperation (FLC) Embassy of Finland

ይህ በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን የሚተገበረው ፕሮጀክት በፊንላንድ ኤምባሲ የአካባቢ ትብብር ፈንድ (ኤፍኤልሲ)ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...