ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተቀየረች ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የሺህ ዘመናት የሰው ልጅ የድካም ጉዞን እረፍት ሰጥቷል፡፡ የሰው ልጅ የአዕምሮው ምጥቀት፣ የሥልጣኔው ፍጥነት ልፋት የበዛው የሕይወት ውጣ ውረድን በእጥፍ ድርብ አቅልሎለታል፡፡ ዓለምን በሦስት ጎራ ከፍሎ የነበረው የሰው ልጆች የሥልጣኔ ማዕቀፍ ተወደደደም ተጠላ አሁን ላይ ወደ አንድ ጎራነት እየቀየረው ይገኛል፡፡ ይህን የግሎባይላዜሽን ዘመን ያፋጠነው ደግሞ የቴሌኮም ሲስተምና መሰል ቴክኖሎጂዎች ናቸው፡፡ በእግር የሚሔደው በአየር ሲተካ፤ ዓይን ለዓይን የነበረው ንግግር ምሥልና ድምጽን አስደግፎ በስልክ ሲተገበር፤ አካል ለአካል በገንዘብ ወይም መሳ ለመሳ የነበረው የግብይት ሥርዓት ባንክን በመሰሉ የሥልጣኔ ሐዲዶች መፈጸም ሲጀምር የዓለም አንድነት ጎልብቶ የሰው ልጆች ድካም በእጅጉ ቀነሰ፡፡ የኾኖ ኾኖ የዚህ ዲጂታል ዓለም ሞተር የኾኑት ቴሌኮምና ባንክ በሀገራችን የረጅም ጊዜ የአገልግሎት ዳራ ያላቸው ናቸው፡፡ የባንክ አገልግሎት በሀገራችን ከተጀመረ ከሰማኒያ በላይ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮ ቴሌኮምም ቢኾን ከ129 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የሀገሪቱ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡
ሰሞኑን እነዚህ ሁለት አንጋፋ ተቋማት በሁለንተናዊ የልማት እና የዕድገት ጉዞ ውስጥ ቀዳሚ ሚና በመጫወት የሚታወቁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በአጋርነት፤ ዜጎች ዲጂታል የብድር እና የቁጠባ አገልግሎቶችን በቴሌብር እንዲያገኙ የሚያስችል የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት በአጋርነት ያስጀመሩት አገልግሎት የባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋግጥ የሚያስችል፣ ዜጎች ባሉበት ኾነው ፈጣን እና ቀላል በኾነ አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያግዝ የዲጂታላይዜሽን አንዱ መገለጫ ገጽ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት የባንክ አገልግሎት በመስጠት ኢንዱስትሪውን በመምራት ላይ የሚገኘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው ጥቅም ላይ በማዋል የደንበኞቹን ፍላጎት እና እርካታ ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት በአሁኑ ጊዜ ከ38 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የተቀማጭ ገንዘቡን ከ1.1 ትሪሊየን ብር በላይ ማሻገሩ ባንኩ በቅርቡ ባወጣው መረጃ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተለያዩ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የኢትዮጵያን ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር በበላይነት እየመራ የሚገኝ ሲኾን፣ በሀገራችን የፋይናንስ አካታችነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
እንደባንኩ ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ ተቋም ነው፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ በሚማቅቁበት ወቅት ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ነበረች፡፡ ላለፉት 129 ዓመታት በሃገራችን የቴሌኮም አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ ኾኗል፡፡ በዚህም ቴሌብር የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ባስጀመረ በ2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ34.05 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እና የዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደቻለ ሰሞኑን ተቋሙ ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአጋርነት ለመሥራት መስማማታቸውን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ከአንጋፋው ተቋም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጥምረት መሥራቱ ሕብረተሰቡ አሁን ከሚያገኛቸው አገልግሎቶች የተሻለ እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።
በዚህ አገልግሎት ግለሰቦች፣ በንግድ ሥራ የተሠማሩ ተቋማት እንዲሁም ሕጋዊ ወኪሎች የአነስተኛ ቁጠባ እና የብድር አገልግሎቶችን በቴሌብር ማግኘት እንደሚችሉም ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ የግለሰብ ደንበኞች እና ተቋማት በቴሌብር የሚያከናውኗቸውን ግብይቶች መሠረት አድርጎ በሚሰራ የብድር ቀመር ስሌት፣ እንዲሁም በቴሌብር የደሞዝ ተከፋይ መኾናቸውን መነሻ በማድረግ ያለ ማስያዥያ በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ የብድር አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ስንቅ፡- (ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ ምጣኔ የሚታሰብባቸው የተንቀሳቃሽ እና የጊዜ ገደብ ተቀማጭ የቁጠባ አገልግሎት)፣ እንደራስ፡- (የግለሰብ ደንበኞች በቴሌብር እንደሚያከናውኑት የግብይት መጠን እስከ ብር 15,000 ድረስ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት)፣ ድልድይ፡- (ለነጋዴዎች/ወኪሎች አነስተኛ ንግድ/ቢዝነስ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያስፋፉ እስከ ብር 50,000 የሚደርስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አገልግሎት) እንዲሁም አድራሽ፦ (ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች ለደሞዝ መዳረሻ እስከ 50,000 ብር ድረስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችሉ የብድር አማራጮች) የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ማግኘት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ጊዜው የዲጂታል መኾኑን ገልፀው፣ ባንኩ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ አቤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ ለመሥራት የተስማሙበት ውል ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ጠቁመው ይህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ የሚሰጥ አገልግሎት በገጠርም ኾነ በከተማ ያሉ ደንበኞች ተያዥ ሳያስፈልጋቸው ያለዋስትና የቴሌብር እና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመኾናቸው ብቻ የብድር አገልግሎት ማግኘት ማስቻሉ ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡ ደንበኞች የተበደሩትን ብድር በወቅቱ በመመለስና የተለያዩ ግብይቶችን በቴሌብር በመፈጸም መበደር የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ማሳደግ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ80 ዓመታት የፋይናንስ ዘርፍ ቆይታው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት በመኾን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋፅዎ ያበረከተ አንጋፋ የፋይናንስ ተቋም መኾኑ ግልጽ ነው። ይህ በመኾኑም የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አገራዊ ቁጠባን በማስፋፋት፤ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና አገራዊ ገቢና ወጪ ንግድን በማሳለጥ፣ አዳዲስ እና ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ያሳረፈው አሻራ አጅግ የጎላ ነው፡፡ ባንኩ በግንባር ቀደምትነት የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የኢትዮጵያን የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር በበላይነት እየመራ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ ተቋማት ሰሞኑን ያደረጉት ስምምነት “የፋይናንስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መርህ የዲጂታል ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶችን መስጠት ነው። ተቋማቱ በመርሐ ግብሩ ወቅት እዳስታወቁት በቀጣይም ሁለቱ አንጋፋ የሀገራችን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀደምት አጋርነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ሊያሻሽሉ እና ሊያሳድጉ በሚችሉ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲሁም በሌሎች መስኮች ላይ በጋራ ይሠራሉ፡፡
