የካቲት 12 ፤ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን!

Date:

በዚያ ቀን፣ ልክ የዛሬ 85 ዓመት፣ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በተካሄደው ጭፍጨፋ አዲስ አበባና አካባቢዋ ውስጥ ብቻ ወደ 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን፣ ዘንድሮ 85ኛ ዓመቱ ላይ ነው። የካቲት 1929 ዓ.ም. ያህል ለኢትዮጵያ የመከራና የጽልመት ወራት ኖሮ አያውቁም። በጣም የሚገርመው፣ በዚሁ በወርኃ የካቲት 1888 ዓመተ ምህረትም ከሰባ ሺህ በላይ ወገኖቻችንን መሥዋዕት አድርገናል። ግፈኛው የንጉሥ ኡምቤርቶ ጦር፣ በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ሃይማኖት ሊቀለብስ፣ መሬት ሊቆርስ፣ ነፃነታችንን ሊገስ መጥቶ ማጭድና ጎራዴ፣ ጦርና ጋሻ የያዙትን በመድፍና በዘመኑ መሳሪያዎች ፈጃቸው።

ከአርባ አንድ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ለወረራ የመጣው በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራው የፋሺስትም ጦር፣ ከየካቲት 12 ቀን እስከ የካቲት 14 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ከሠላሳ ሺህ በላይ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያንን ገደላቸው። ዕለቱን ሀገር ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ ከአገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በተለያየ ዝግጅቶችና ፕሮግራሞች በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን በማሰብ የሚያከብሩት ነው።

ሰማዕትነት ሲገለጽ

በአንድ እምነት ወይም አቋም ወይም ማንነት ላይ የሚገኙ ምንም ዓይነት የኃይል ርምጃ ለመውሰድ ያልሞከሩ፣ ሰላማዊና ንጹሐን ሰዎች ሌላው በኃይል ርምጃ ሲያሰቃያቸው፣ ወይም የአካልና አእምሮ ጉዳት ሲያደርስባቸው፣ ወይም ሕይወታቸውን ሲያጠፋባቸው እነዝያ ሰዎች ሰማዕታት ይባላሉ። በዚሕ ዓይነት፣ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ያለቁት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰማዕታት የሚለው መጠርያ በትክክል የሚገባቸው ናቸው። የሰማዕታት ሐውልት እየተባሉ የሚጠሩ ሌሎች ቢኖሩም፣ በትክክል የሚገባው (ምናልባትም ብቸኛው) በአዲስ አበባ፣ ስድስት ኪሎ አደበባይ ላይ የቆመው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ያለቁትን ንጹሐን መታሰቢያ የኾነው ሐውልት ነው።

አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ 5 ሐውልቶች አንዱ የኾነው፣ ሾጣጣው የሰማዕታት ሐውልት በ1929 ዓ.ም የካቲት 12 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ያኽል በፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች ለተጨፈጨፉ ሠላሳ ሺሕ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ ይኾን ዘንድ የቆመ ሐውልት ነው። በየካቲት 1934 ዓ.ም ሙሉ ሥራው ተጠናቅቆ የተመረቀው ይሕ ሐውልት የፋሽስቱን ግራዚያኒ አረመኔያዊና አውሬያዊ ድርጊት “ለዓለም እንዲናገር፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንዲያስቡት” ተብሎ የተሠራ ነው፡፡

በአውሬአዊነት ባሕርዩ “የሊቢያው ጅብ” የሚል ቅጽል ስምን ያተረፈው የፋሺስቱን ቫይስሮይ ሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ በየካቲት 12፣ 1929 ዓ.ም ዓም ላይ ተደረገ። በዕለቱ የጣሊያዋ ኔፕልስ መሥፍን ሴት ልጅ ስለተወለደችለት ፌሽታ በማድረግ ድኆችንና ነዳያንን የገንዘብና የሌሎችም ዕርዳታ ስለሚደረግ፣ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ እንዲገኝ ተጠርቶ ነበር። ሕጻናትንና ልጆችንም ይዘው እንዲገኙ ነበር የተደረገው።

ገና የዕርዳታ ዕደላው ሳይጀመር፣ አጋጣሚውን በመጠቀም፣ የግድያ ሤራውን አሢረው ሲዘጋጁ የነበሩት ወጣቶች፣ የያዟቸውን ቦንቦች በመወርወር፣ ግራዝያኒና በወቅቱ አብረው ከከነበሩት ጥቂት ሰዎች ቆሰሉ። (የከተማይቱ ከንቲባ የነበረውና የሜትሮፖሊታኑ ጳጳስ ነበሩ።)

ይሕን ሙከራ ተከትሎ ለሦስት ቀናት ያህል የቆየ የጅምላ ጭፍጨፋና አፈሳ ዘመቻን ዐወጀ፡፡ በዚህም ከከተማዋ ነዋሪዎች አንድ-አምስተኛው ያሕል በተገኘው መሣርያና መግደያ ተገደለ። አረጋውያንን፣ ሕፃናትን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ፣ በአካፋና በዶማ፣ በጠመንጃዎች ና በሽጉጦች፣ በካሚዮኖች በመጎተትና በላያቸው ላይ በመንዳት፣ ወ.ዘ.ተ ተገደሉ። ሸሽተው ቤታቸው መግባት የቻሉትና ከቤታቸው ያልወጡትን በላያቸው ላይ በመዝጋት እሳት ለኮሱባቸው።

የሀውልቱ መታሰቢያ

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በይፋ ማክበር የተጀመረው በ1934 ዓ.ም ነው። በዚያን ጊዜ የነበረውም ሃውልት፣ ይህ ዛሬ ትከሻውን አሳብጦ፣ ደረቱን ገልብጦ ቆሞ የምናው ሃውልት አልነበረም የተተከለው። ያኛው ሃውልት እስከ 21ኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ማለትም፣ እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ ለመታሰቢያነት ሲያገለግል ቆየ በኋላ፣ በ22ተኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ይኼኛው የመታሰቢያ ሃውልት በዩጎዝላቪያ መንግሥት ርዳታ በ1951 ዓ.ም በይፋ ተመረቀ። በዚህም መሠረት የሥነ-ሃውልትና የቅርጻ-ቅርጽ ባለሙያዎች ከዩጎዝላቪያ መጥተው ይህ ዛሬ የምናየው ሃውልት በመጀመሪያው ሃውልት ስፍራ ላይ ተተካ።

በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው ይሕን ዘግናኝ የሽብርና የጭፍጨፋ ድርጊት፣ 28 ሜትር በሚረዝመው፣ ባለሦስት ጎኑ የሰማዕታት ሐውልት ዙሪያ በሚታዩት ልጥፍ ቅርፆች እንዲተረኩ ተደርጓል። ሾጤ ሐውልቱ ሽቅብ ረዝሞ እየሾለ ይወጣል። ወደ ሰማይ ይጠቁማል። የጠፋው ነፍስ፣ የፈሰሰው ደምና ዋይታውና ለቅሶው በሰማያት ከመላእክቱ ከተማ ድረስ እንደወጣ ያመለክታል።

ከቅርጾቹ በተጨማሪ ከሐውልቱ ዙሪያ ወደ አጥሩ ተጠግቶ በአራቱ አቅጣጫዎች በጽሑፍ የኾነውን ኹሉ የሚተረኩ፣ በአትሮንስ ላይ በተዘረጉ መጻሕፍት ቅርፅ፣ በነሐስ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች ነበሩት። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአራቱም አቅጣጫ የነበሩት ጽሑፎች ተነቅለው ተወስደዋል። ማን እንደወሰዳቸው አይታወቅም።ሐውልቱና ልጥፍ ቅርጾቹ ጠቅላላ የተሠሩት በኹለት ዩጎዝላቪያውያን አርክቴክቶች ነው። ያሠሩት ደግሞ ግርማዊው ቀዳማዊው ኃይለሥላሴ ነበሩ። ደብዳቤዎች ዛሬ ባልታወቀ አካላት ተወስደዋል ፡፡

የካሳ እና ይቅርታ ዘመቻ ወደ ቫቲካን ሰዎች

የ2002 ዓመተ ምህረቱ የሰማዕታት ቀን ማግስት አዲስ ነገርን በተመለከተ በአያሌው ዕድለኛ ሳይሆን አልቀረም፡፡ አዲስ አበባ ጀግኖችን አሞግሳ፤ ለሰማዕታት የነፍስ ይማር ጸሎት አድርሳ በተመለሰች ማግስት፣ የካቲት 29-2002 ዓ.ም፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› የተሰኘ ተቋም በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትብብር የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ይፋ አደረገ።

የዘመቻውን ይዘት ከሚያብራራው ጥራዝ ላይ ትንሽ እንቆንጥር፣

“በ1935-41(እኤአ) ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርራ ባደረሰችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል፣ የቫቲካን መንግስት እጅ ከጓንት ሆና ተባባሪ ስለነበረች፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጽዕኖ እንዲደረግባት፣ ለዓለማቀፋዊው ህብረተሰብ፣ በዓለም ላሉ መንግስታት ሁሉ ፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣….ለሌሎች ለሚመለከታቸው ድርጅቶችና ለእውነት ለቆሙ ህዝቦች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ አቤቱታችንን በታላቅ ትህትና እናቀርባለን፡፡”

የዘመቻው ተጽዕኖ ውጤታማ ይሆን ዘንድ፣ 100ሺ ሰዎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተቋሙ በወቅቱ ጠይቋል። ዐሥራ ሁለት ዓመታት አለፉ፣ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር 10 ሺህ አልሞላም፣ ቫቲካንም ይቅርታ አልጠየቀችም።ምንጭ፡- ዓምደ ተዋሕዶ፣ ልሣነ አርት እና ቢቢሲ አማርኛ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...