አርቲስት ዳዊት ፍሬው ኃይሉ ከአባታቸው አርቲስት ፍሬው ኃይሉ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዘነበች ተሰማ በአዲስ አበባ ከተማ ደጃች ውቤ ሠፈር በውቤ በረሀ መስከረም 07 ቀን 1969 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ እድሚያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከ1-8ኛ ክፍል በራስ አበበ አረጋይ ትምህርት ቤት እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ተፈሪ መኮንን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን ለአባቱ አርቲስት ፍሬው ኃይሉ ሙያ ከልጅነት ጀምሮ በነበረው ፍቅር በ1989 ዓ.ም ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን ተቀላቅሏል፡፡
በ1992 ዓ.ም በዋና መሳርያ (major) በክላርኔት በማይነር ኪቦርድ እንዲሁም በባህላዊ ሙዚቃ ማሲንቆን ጨምሮ ተመሮ ተመርቋል፡፡ በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው የታላላቅ የክላርኔት standared concerto’ዎች ተጫውቷል፡፡
ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደወጣ በኢትዮጽያ ብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥ በክላርኔትና አልቶሳክስ ተጨዋችነት ለአመታት አገልግሏል፡፡ በቴትትር ቤቱ ቆይታው በግሉ የመጀመሪያውን ኢኒስትሩመንታል አልበም ለአባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ‘’ፍሬው’’ በሚል ርዕስ በፈለቀ ሀይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል፡፡ ይህም ስራው ከሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ እውቅናን ያሰጠው የጥበብ ስራ ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠልም ህይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ተከታታይ ሦስት ተጨማሪ አልበሞችን በግሉ ስርቶ ለሙዚቃ አፍቃሪያን አቅርቧል። በመጨረሻም የሠራው አራተኛው አልበም ሀገሩ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለመስራት በጀመረችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የነበረውን ደስታ እና ድጋፍ መግለጫ ይሆን ዘንድ መታሰቢያ በማድረግ የሰራው አልበም ነበር ፡፡ ይህም በተለያዩ የቴሌሺዥን ጣቢያዎች ግድቡን በተመለከተ ስሜቱን ያንጸባረቀበት የጥበብ ስራዎች ሆኖ በታሪክ ሲዘከር ይኖራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በግሉ ከሰራቸው 4 አልበሞች ባሻገር ከ2000-2004 ዓ.ም ድረስ በሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የአዲስ አኮስቲክ ባንድ ጋር አልበም የማሳተም እና በበርካታ ሀገራት ኮንሰርት የማቅረብ እድልን አግኝቷል፡፡ እንዲሁም በአለም አቀፍ የሙዚቃ ፌስቲቫል (womex) በዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ጅቡቲ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያዊ ቅላጼ በተዋበው ድንቅ የክላርኔት አጨዋወቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በተደነቁት ‘the guardian’ እና ‘independent’ ጋዜጦች ላይ ሰፊ የአድናቆት የዘገባ ሽፋን አግኝቷል፡፡
በ2006 ዓ.ም ላይ በመምህር ፈለቀ ሀይሉ በተቋቋመው ’Retrieve Ethio Big Band’ በአልቶ ሳክስፎን ተጨዋችነት እጅግ የተደነቁ ታላላቅ መድረኮች ላይ ተጫውቷል፡፡
እንዲሁም ኮቪድ 19 በተከሰተበት ወቅት ወጣቱ ሙዚቀኛ እዩኤል መንግስቱ በልዩ ሁኔታ ባቀናበረው “ቅኔ ነው ሀገር’’ በተሰኘው ወጣት እና አንጋፋ ሙዚቀኞችን ባሳተፈው የኦርኬስትራ እና ካየር ቅንብር የሙዚቃ ስራ ላይ በክላርኔት ተጨዋችነት ተሳትፋል፡፡
ዳዊት ከአለም ታላላቅ ክላርኔቲስቶች ጋር በመድረክ የመጫወት እድልም ነበረው፡፡ ለአብነት ያህል በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሴ የሙዚቃ ፌስቲቫል መድረክ ላይ ከ ‘’Ether orchestra’’ አባላት ጋር ተጫውቷል፡፡
ከአለም እጅግ ገናና ስም ካላቸው ክላርኔቲስቶች አንዱ ከሆነው ከፓኩዌቶ ዴሪቬራ ጋር በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መድረክ ላይ ተጫውቷል፡፡
እንዲሁም በድምጽ ያባቱን የአርቲስት ፍሬው ሀይሉ የሆኑ ሙዚቃዎችን ሰርቶ ከመጫወት ባሻገር ለተለያዩ አርቲስቶች የሰጣቸው ግጥም እና ዜማ ድርሰቶች ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ‘’ማለባበስ ይቅር’’ በሚል የተለቀቀው በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ተዘጋጀ አልበም እንዲሁም የአርቲስት ፀጋዬ እሸቱ የሠርግ ዜማዎችም ከሰራቸው የጥበብ ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ለወደፊትም የሚወጡ በተለያዩ አርቲስቶች እጅ ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን ለአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን አበርክቷል፡፡
ክላርኔትን አትዮጵያዊ አንደበት ከሰጧት አትዮጵያዊ ሙዚቀኞች መካከል የዘመናችን እንቁ ሙዚቀኛ ሆኖ በመድረክም በአልበምም የታየው ዳዊት ፍሬው ኃይሉ ብዙ ሊሰራ ባቀደበት፣ ብዙ ውጥኖችንም ባደራጀበት በዚህ ወቅት ለእረፍት እና ለስራ በተጓዘበት በጣሊያን ሀገር ሮም ከተማ በተወለደ በ46 አመቱ በድንገተኛ ሁኔታ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ የክላርኔት የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቹ አርቲስት ዳዊት ፍሬው የቀብር ሥነ-ሥርዓትም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈጽሟል። በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአርቲስቱ አድናቂዎች እና ዘመድ ወዳጆቹ ተገኝተዋል።
የሙዚቃ ባለሙያው ሠርፀ ፍሬስብሐት ስለ ዳዊት ፍሬው
ይህንን አስደንጋጭ መርዶ ለማመን ሰዓታት ፈጅቶብኛል። ዳዊት ፍሬው ወደ ጣሊያን ለመጓዝ ዝግጅት ላይ እያለ፣ ለጣሊያን ኤምባሲ የድጋፍ ደብዳቤ እንድጽፍለት ሊጠይቀኝ ያለሁበት ድረስ መጣ። በጣም ግሩም በኾነ የተነቃቃ ስሜት ጣሊያን የሚኖሩትን የኮንሠርት መድረኮች ዘረዘረልኝ። ጣሊያን ሀገር ነዋሪ የኾኑ የኢትዮጵያ ‘ኮምዩኒቲ’ አባላት በምን ዓይነት ጉጉት እየጠበቁት እንደኾነም ነገረኝ።
የዳዊትን ጨዋታ ዐዋቂነት የምታውቁት የምትመሰክሩት ነው። ሙዚቃዊ ቀልዶቹን እያከታተለ ነግሮኝ በጣም አሳቀኝ። ደብዳቤውን ጽፌ ሠጠሁት። ከዚያ በኋላ የደወለልኝ ለጉዞው አንድ ቀን ሲቀረው ነበር። ሞቅ ባለ ስሜት እና በመድረክ ጉጉት ስሜት ተሰናበተኝ።
ከዚያች ዕለት በኋላ እጠብቅ የነበረው፣ የመድረክ ቪዲዮዎቹን ነበር። ከቶውንም ያላሰብኩትን የድንገተኛ ኅልፈቱን ዜና ሰማሁ።
***
ዳዊት ፍሬው ኃይሉ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱ ‘ሜጀር’ ያደረጋትን ክላሪኔትን የምር የሙጥኝ ያለ ድንቅ ሙዚቀኛ ነበር። አልቶ ሳክስፎን እና ክራር የሚጫወት ቢኾንም፣ ለክላሪኔት የነበረው ፍቅር፣ ከጋሽ ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ነፍስ ኄር) እና ከጋሽ መርዓዊ ሥጦት ጋር የሚያመሣሰለው ነበር።
በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው፣ የታላላቅ ኮምፖዘሮችን የክላርኔት standard concerto’ዎች’ ተጫውቷል። መምህሩ ፈለቀ ኃይሉ የሚያደንቀው እና የሚያበረታታው ተማሪው ነበር።
ከተማሪ ቤት እንደወጣ፣ኢትዮጵያብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥ በክላሪኔት እና አልቶ ሳክስ ተጫዋችነት ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሏል። በቴአትር ቤት ቆይታው፣ በግሉ፥ የመጀመሪያውን “ኢንስትሩሜንታል” አልበም፣ በፈለቀ ኃይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል።
ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ፣ በግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የ”ዐዲስ አኩዊስቲክስ” ባንድ ጋር አልበም እና በበርካታ ሀገራት ኮንሰርት የማቅረብ ዕድል አገኘ። በኢትዮጵያዊ ቅላፄ በተዋበው የክላሪኔት አጨዋወቱ የተደነቁ ጋዜጠኞች “The Guardian” እና “Independent” ጋዜጦች ሰፊ የአድናቆት ዘገባ ጽፈውለታል።
ከ2004 እስከ 2014 ዓ.ም. በተከታታይ ሦስት የመሣሪያ ቅንብር ሥራዎችን በአልበም አሳትሟል። 2006 ዓ.ም. ላይ፣ በታላቁ ሙዚቀኛ እና መምህር በተቋቋመው “Retrieve Ethio Big Band” ላይ በአልቶ ሳክስፎን ተጫዋችነት የተደነቁ ታላላቅ መድረኮች ላይ ተጫውቷል።
ኮቪድ 19 በተከሰተበት ወቅት፣ ወጣቱ ሙዚቀኛ ኢዩኤል መንግሥቱ በልዩ ኹኔታ ባቀናበረው “ቅኔ ነው ሀገር” በተሰኘው የኦርኬስትራ እና ኳየር ቅንብር የሙዚቃ ሥራ ላይ በክላሪኔት ተጫዋችነት ተሳትፏል።
ዳዊት ከዓለም ታላላቅ ክላርኔቲስቶች ጋር በመድረክ የመጫወት ዕድልም ነበረው። ለአብነት ያህል፥ በአሊያን ኢትዮ ፍራኔሲስ የሙዚቃ ፌስቲቫል መድረክ ላይ፣ ከ”Ether Orchestra” አባላት ጋር ተጫውቷል።(የኔ ሐሳብ የተሰኘችው የግርማ ነጋሽን ሙዚቃ የመድረክ ሥራ ያስታውሷል)፣ በዓለም እጅግ ገናና ስም ካላቸው ክላርኔቲስቶች አንዱ ከኾነው ከፓኩዊቶ ዴሪቬራ ጋር በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መድረክ ላይ፣ “አምባሰልን” ተጫውቷል።
ክላሪኔትን ኢትዮጵያዊ ዐንደበት ከሠጧት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል፣ የዘመናችን ዕንቁ ሙዚቀኛ ኾኖ በመድረክም በአልበምም የታየው ዳዊት ፍሬው ኃይሉ፣ ብዙ ሊሠራ ባቀደበት፣ ብዙ ውጥኖቹንም ባደራጀበት በዚህ ወቅት፣ በ44 ዓመት ዕድሜው ይህችን ዓለም በሞት መለየቱ ከልብ ያሳዝነኛል። ልብ የሚሰብር ኀዘን ነው የተሰማኝ።
ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለሙያ አጋር ጓደኞቹ እና የአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ። ነፍስ ኄር
