
የጃፓን የፀሐይ ኃይል አምራች ኩባንያ የሆነው ቶዮ ሶላር፤ በኢትዮጵያ ያለውን ዓመታዊ የሶላር ሃይል የማምረት አቅሙን ከ 2 ጊጋዋት ወደ 4 ጊጋዋት በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ።
ኩባንያው በየካቲት ወር የሙከራ ምርቱን በጀመረበት እና ፋብሪካው በሚገኝበት የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሁለተኛ የማምረቻ ፋብሪካውን ለመከራየት ማሰቡን አመልክቷል።
የአዲሱ ፋብሪካ ግንባታ በሚያዝያ ወር ይጀመራል የተባለ ሲሆን ሥራውን በነሐሴ ወር በይፋ እንደሚጀምር ተመላክቷል።
የመጀመሪያው ፋብሪካ ኢንቨስትመንት 60 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ለሁለተኛው ፋብሪካ 47 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።
ኩባንያው ምርት ከጀመረበት ከጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2023 ጀምሮ 1.3 ጊጋዋት የሶላር ሴሎችን ወደ ውጭ መላኩ ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የተመረቱት ሴሎቹ በአሜሪካ ወደሚገኘው ሞጁል ማምረቻ ፋብሪካ የሚላኩ ሲሆን፣ እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2026 መጀመሪያ ድረስ በአሜሪካ የተለየ “የሶላር ሴል ማምረቻ ፋብሪካ” ለመገንባትም አቅዷል።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ጁንሴይ ሪዩ “የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁ በፊት ለሶላር ሴል ምርቶቻችን ያገኘነው ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት እና ትዕዛዞች የስትራቴጂካዊ ራዕይ ጥንካሬን ያረጋግጣሉ” ብለዋል።
አክለውም “ዓለም አቀፋዊ ፍላጎትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ተጨማሪ አቅም ለማሳደግ ወስነናል” ሲሉ ተናግረዋል።