Home ባሕር ማዶ የግፍ ሰለባ የሆነችው አጊቱ ጉደታ

የግፍ ሰለባ የሆነችው አጊቱ ጉደታ

አጊቱ ጉደታ ትውልዷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፣ በፖለቲካ ስደት ጣሊያን ከገባች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በፈረንጆቹ ዘመን መለወጫ ቀን በ1978 አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደችው አጊቱ፣ በግብርና ከሚተዳደሩ ወላጆቿ የግብርና እውቀት እንዳገኘች ትናገራለች፡፡ በወቅቱ ገጠር አካባቢ ከሚኖሩት ወላጆቿ በነፃ ያገኘችው ዕውቀት ህይወቷን የቀየረላት ነበር፡፡ ጣሊያን ሀገር ከሚገኘው ትሬንቶ ዩኒቨርስቲ በሶጂዮሎጂ ዲግሪዋን ያገኘችው አጊቱ ጉደታ፣ ትምህርቷን ተጠቅማ ሀገሯን ለመጥቀም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር፡፡

አርሶ አደሩን በዘላቂነት በሚጠቅሙ የግብርና መስኮች ላይ በማተኮር አደራጅታ ህይወታቸውን ለማሻሻል ጥራለች፡፡ የአርሶ አደሩንም ልፋት ለመቀነስ ከስልጠና ጀምሮ መሠረታዊ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ፣ እንዲሁም ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ገቢያቸውን ከፍ እንዲደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመምራት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ በዚህ ተግባሯ የተነሳ ወደ ፖለቲካው ያደላችው አጊቱ፣ መንግስት መሬትን ከገበሬ እየወሰደ ለባለሀብቶች ማከፋፈሉ አስቆጥቷት ተቃውሟውን ስታሰማ እንደነበር የሚያውቋት ጭምር ይናገራሉ፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ህግን ያልተከተለ ኢንዱስትራላይዜሽንን በመቃወም በትልልቅ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ስም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያካሂደው የመሬት ነጠቃ ተገቢ አይደለም ስትል በመቃወሟ የመንግስት ጥርስ ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ በዚህ ተግባሯ ሰላሟን ያጣችው አጊቱ የትውልድ ሀገሯን በመተው በፈረንጆቹ 2010 ላይ ወደ ጣሊያን ለመሰደድ ተገዳለች፡፡ በ32 አመቷ ጣሊያን የገባችው ይህች ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዝነኛ የስራ ፈጣሪ፣ ህይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በግብርና መስክ ዝነኛ ለመሆን በቅታ ነበር፡፡

በአልፕስ ተራሮች አካባቢ የሚገኝ የእርሻ ቦታን በመጠቀም ብዛት ያላቸውና ልዩ ዝርያ ያላቸውን ፍየሎች በማርባት ታዋቂ መሆን ችላለች፡፡ ከፍየሎቹ ከምታገኘው ወተት ቺዝ/አይብ/ በማምረት ለገበያ በማቅረብ ምርቷ በአጭር ጊዜ ተወዳጅነትን አትርፎላት ነበር፡፡ ከወተት ተዋጽኦ የውበት መጠበቂያዎችን በማምረት ጭምር ምርቷን ራሷ ለገበያ በማቅረብ ከአካባቢው ነዋሪዎች አልፋ በመላው ጣሊያን ለመታወቅ በቅታ ነበር፡፡ ከስራዋ ባሻገር በንግዱ ላይ በቂ ዕውቀት በማዳበሯ ዝናዋን ሰምተው በርካታ ሚዲያዎችና አለምአቀፍ ተቋሞች ስራዋን አስተዋውቀውላት ነበር፡፡

ከጣሊያኖች ጋር ተቀላቅሎ በመኖር የስደተኞች ምርጥ ምሳሌ ናት በሚልም ህይወቷን ሌሎች እንዲያውቁት ተደርጎም ነበር፡፡ ዘረኝነትን ከመታገል ጀምሮ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ መድሎዎችንና ተጽዕኖዎችን በመታገል የምትታወቀው አጊቱ፣ ለብዙ መሰል ስደተኞች ምሳሌ መሆን ችላ ነበር፡፡ በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ከባዶ ተነስታ ከፍተኛ የሆነ ቦታ ላይ ከዝና ጋር መድረስ የቻለችው ይህች ድንቅ ሴት፣ ያሰበችውን ጨርሳ ሳታከናውን ህይወቷን በግፍ ተነጥቃለች፡፡

በርካታ ሠራተኞችን እየቀጠረች ስራዎቿን ታከናውን የነበረችው ይህች ትጉህ ሴት፣ በአንድ ክፉ ቀን በተቀጣሪዋ ጋናዊ እጅ ውስጥ ትወድቃለች፡፡ “ገንዘብ ጨምሪልኝ” በሚል አምባጓሮ ያነሳው ይህ ነፍሰ ገዳይ የምትኖርበት አፓርታማ ድረስ ሄዶ፣ አስገድዶ ደፍሮ በሚዘገንን ሁኔታ ጭንቅላቷን በመዶሻ ቀጥቅጦ ገድሏታል፡፡ በእለቱ የነበራት የንግድ ቀጠሮ ላይ ባለመገኘቷ በስልክም መልስ አልመልስ ስላለች ጎረቤቶቿ ሲፈልጓት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገላ አግኝተዋቷል፡፡ የመገደሏ ዜናም ከሚያውቋት አልፎ በመላው አለም በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል፡፡ ከአገዳደሏ አሠቃቂነት በተጨማሪ፣ የህይወት ውጣ ውረዷና ስኬቷ በተደጋጋሚ በይፋ ተዘግቦ ስለነበር ሀዘኑ ይበልጥ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

“ፒዜታ ሞኬና” የተሰኙ ልዩ የፍየል ዝርያዎችን ቫሌ ዲ ሞሾኒ በተባለ አካባቢ ማርባት የጀመረችው አጊቱ፣ ስለቺዝ አሠራር ፈረንሳይ ሄዳ ከተማረች በኋላ ነበር “ላካፕራ ፊሊስ” ወይም “ደስተኞቹ ፍየሎች” የተሠኘውን ድርጅቷን የመሠረተችው፡፡ 15 ፍየሎችን በመግዛት ባለቤት አልባ የነበረን 11 ሄክታር መሬት ተጠቅማ እርባታውን በመጀመር ከ2 አመት በፊት 180 ደርሰውላት ነበር፡፡ በወቅቱ በዶቼ ቬሌ ዶክመንተሪ ላይ ህይወቷ እንደተዘገበው” ወተትና ከወተት ተዋጽኦ አይብ ብቻ ሳይሆን፣ የውበት መጠበቂያ ምርቶችንም ለገበያ ታቀርብ ነበር፡፡

ከግሏ የእርሻ ተግባር በተጨማሪ፣ በአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞችና ቅስቀሳዎች ላይ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራት አጊቱ፣ ከስደተኝነት ተነስታ ከጣሊያናውያኑ ጋር በመቀላቀል ባበረከተችው አስተዋጽኦ በሀገሪቱ ፖለቲከኖች ጭምር ስሟ ተነስቶ እስከመመስገን ደርሳ ነበር፡፡ ከአመታት በፊትም በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች በሚሰጥ ሽልማት ላይም ዕጩ ሆና ቀርባ ነበር፡፡ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ከስሟ በተጨማሪ “የደስተኞቹ ፍየሎች ንግስት” በሚል ቅጽል ስም ያሞካሹዋት ነበር፡፡ አጊቱ የደረሰችበት ዝና በአጋጣሚ አልጋ ባልጋ ሆኖላት የተገኘ አልነበረም፣ ጣሊያን እንደገባች በርካታ የዘረኞች ጥቃት እረፍት ይነሳት የነበረ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም ዝነኛ እየሆነች ስትመጣ እንደቀነሰ ትናገር ነበር፡፡

አጊቱ እንደ አብዛኞቹ ሠራተኞች በስደተኝነቱ ቀጥራው በነበረው የ32 አመቱ ጋናዊው አዳምስ ሱሊማኒ መገደሏን ተከትሎ በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዘነቡ ታደሰ ወደ ትሬንቲኖ በመጓዝ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር ስለጉዳዩ አብረው ለመስራት መነጋገራቸው ተዘግቦ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽነርም የተሰማቸውን ሀዘን በመጥቀስ፣ አንድ ስደተኛ ተቀባዩን ሀገር እንዴት መርዳት እንደሚችል ያመለከተች ድንቅ ሴት ነበረች በማለት ስደተኛን አንቀበልም ለሚሉ ሀገራት ማስተማሪያ እንደምትሆን ጠቁመዋል፡፡ ለሌሎች ስደተኞችም አርአያ ትሆናለች ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ስደተኞች ተስፋ እንዳይቆርጡና ከህዝቡ ተቀላቅለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ማሳያ ለመሆኗ ለሁላችንም ማስታወሻ ናት ብለዋል፡፡ የአጊቱ ጉደታን ግድያ ተከትሎ፣ አሟሟቷን ጭምር የሰሙ ኢትዮጵያኖችን ሀዘናቸው በተለየ መንገድ ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡ ከፍየሎችዋ ጋር የተነሳቻቸው ፎቶዎች በማህበራዊ ትስስር ድህረ ገጾች ለቀናት ሲዘዋወሩ የቆዩ ሲሆን፣ በርካታ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም ተቀባብለው ዘግበውታል፡፡ በወተትና ቺዝ ምርቶቿ ዝነኛ የነበረችው አጊቱ፣ ሀብትና ዝና ማትረፍ አላማዋ እንዳልነበር በተለያየ ጊዜ ቃለ መጠይቅ ላደረጉላት ተናግራ ነበር፡፡ ያለምንም ዘመናዊ መሣሪያ አካባቢን ከብክለት የሚጠብቁ ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሣየት እፈልጋለሁ ትል ነበር፡፡ ዘረኝነት እየተባባሰ በመጣበት አለም ስደተኛ ምን ማድረግ እንደሚችል ለማሳየትም ከፍተኛ ፍላጎት የነበራት ይህች ታታሪ ሴት፣ በተደጋጋሚ በዘሯ ምክንያት የግድያ ዛቻ እየደረሰባት ለፖሊስ ታሳውቅ ነበር፡፡ ከአንድ ጀርመናዊ ደራሲ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የነበራት አጊቱ፣ ከወራት በኋላ አብረው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለትውልድ ሀገሯ አስተዋጽኦ የማድረግ ህልም እንደነበራት ወዳጇ ተናግራለች፡፡ እነዚህን ህልሞቿን ተግባራዊ ሳታደርግ፣ ስራው ህይወቱን ይቀይርለታል ብላ አዝናለት በቀጠረችው ጋናዊ ስደተኛ እጅ በአሠቃቂ ሁኔታ መገደሏ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ ምርቶቿን ይወዱ የነበሩት ብቻ ሳይሆኑ፣ ታሪኳንም ሰምተው ያዘኑላት በመላው አለም የሚገኙ አድናቂዎቿ፣ ገንዘብ አሠባስበው ስራዋን ለማስቀጠልና ለማሳደግ አልመዋል፡፡ ስሟ እየተዘከረ እንዲቀጥል ውለታዋንም ለመመለስ በማሰብ ዘላቂ የሆነ ነገር መታሰቡንም ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡