የጠ/ሚኒስትሩ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ምን አስገኙ?

Date:

ኢትዮጵያ ጠንካራ የሃገረ መንግሥት ምሥረታ ካካሔዱ ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡ ይኽ ግን በአንዳንድ የግራ ዘመም የፖለቲካ ኀልዮትን በሚያራምዱ ወገኖች ዘንድ የትችት መርግ ሲወርድበት የቆየ እውነታ መኾኑ አይታበልም፡፡ ያለፈው ኀምሳ ዓመት ዘውግ ተኮር ፖለቲካ በዚህ ልክ የሀገሩ ሕላዌ ጠንቅ እና ጸር መኾኑም እስከዛሬ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ጎራው ግን ከጠየቀው በላይ እያገኘ፣ ከሻተው በላይ እያጋበሰም በዚህ አፍራሽ አቋሙ ጸንቶ ቀጥሏል፡፡ ይኽ ኃይል ድኅረ 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሕግና የአስተዳደር መዋቅሮችን ተቆጣጥሮ ለሩብ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ልዩነትን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካን የሀገሩ መበየኛ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ነገሩ በዚህ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ሕልውና እና የሕዝቦቿ አብሮ የመቀጠል ዕጣ አደጋ ላይ መውደቁን ቀድመው የተረዱ ወገኖችም ነገሮች ከቁጥጥር ከመውጣታቸው በፊት አንዳች መፍትሔ ይበጅ ዘንድ በብዙ መክረዋል፤ ብዙ ተናግረዋል፤ ብዙም ጽፈዋል፡፡

እነኚህ ጩኸቶች ከ2008 ዓ.ም በኋላ የተፈጠሩትን ሕዝባዊ አመጾች ተከትሎ በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ውጥረት ከአምስት ዓመት በፊት ሰላማዊ በኾነ መንገድ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ አመራርነት የሚመጡበትን መንገድ ጠርጓል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ምኒልክ ዙፋን በመጡ በወራት ውስጥ በርካታ ጆሮ ገብ ንግግሮችን በማድረግ በርግጥም የሚሊዮኖች ፍርሓት የነበረውን የሀገር ፍርሰት ጉዳይ እርሳቸውም ቁብ እንደሰጡትና ኢትዮጵያም በብዙ መልኩ ከራሷ እውነት ጋር ካልታረቀች ፈውስ እንደማይኖራት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ሁነኛ አባሪ የሚኾነን በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተደረገላቸው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ያስተላለፉትን መልዕክት ዳግም መመልከት ነው፡፡ በዚህ የዐደባባይ መልዕክታቸው ነጻነትን፣ ዴሞክራሲን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክተው ያስተላለፏቸው ቁም ነገሮች ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከደረሰችበት ሁለንተናዊ ቁመና ተቃራኒ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡

ለምን? ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ከመጡ ድፍን አምስት ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን የሕልማቸው እና የንግግራቸው አልፋ እና ኦሜጋ በማድረጋቸው መላው ኢትዮጵያዊ ፍቅሩንና ድጋፉን በአደባባይ ገልጦላቸዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ግን የኦሮሚያ እና ኦሮሚያ ክልል ብቻ አጀንዳ አስፈጻሚ እስኪመስሉ ድረስ ማኅበራዊ መሠረታቸው ወደ አንድ አካባቢ ወርዷል፡፡ ይኽ በዓለማችን ካጋጠሙ ፈጣን የፖለቲካ ቁልቁለቶች ዋነኛው ነው ቢባል ስህተት አይኖረውም፡፡ እንዲህ ላለው ከባድ የማኅበረ ፖለቲካዊ ውድቀት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ጀምሮ በተግባር ባለፉት ዓመታት በዜጎች ሕላዌ ላይ የወሰዷቸው ዘግናኝ አቋሞች ምክንያት ኾነው ሊጠቀሱ ይችላል፡፡

ከምንም በላይ ግን ንቁ በሚባለው የፖለቲካ ማኅበረሰብ ዘንድ የድጋፍ መሠረታቸው በዚህ ልክ አቅጣጫውን የቀየረው ከትናንት 27 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ፍርሰት የሚያጠዳድፉ ግልጽ ምልክቶች ፈጥጠው እየታዩ ጠ/ሚኒስትሩ ይኼ ነው የሚባል የኢትዮጵያን ሃገረ መንግሥት ሕልውና ለማስቀጠል የሚረዱ የሕግና የመዋቅር ለውጦችን ከማድረግ ይልቅ አጠናክረው መቀጠላቸውና አዳዲስና አደገኛ ችግሮችንም በመፍጠራቸው ነው፡፡

ዐዲስ አበባን ‹‹ኦሮሞ ጠል ነዋሪዎች ያሉባት›› ከሚለው ንግግራቸው  አንስቶ ‹‹እኛ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን አናፈርስም›› እስከሚለው ዲስኩራቸው ድረስ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ኢትዮጵያ›› እና ‹‹ኢትዮጵያዊነት››ን ማዕከል ካደረገው ፖለቲካቸው ተፋትተው የአንድ ዘውግና ቡድን ጥቅም አስጠባቂ የመሠሉባቸውን ንግግሮች የመጨረሻ በሚባለው የሥልጣን አካል (የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት) ማስተጋባታቸው በማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይኼን ጊዜ የጠ/ሚኒስትሩ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ምን አስገኙ? የሚለው ጥያቄ ተላላ መልክ ይዞ ሲመጣ፣ ምላሹ ከ‹‹ተዋቡ ፓርኮች እና ከአረንጓዴ አሻራዎች›› የተለየ እንደሚኾን ሳይታለም የተፈታ ይኾናል፡፡    

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...