ይድረስ ለክቡር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Date:

ወርቁ ተስፋዬ

ይቅርታ ያድርጉልኝ እና ከመጠሪያ ሥምዎ በፊት ‹‹ዶ/ር›› የሚለውን ማዕረግ ያላስቀደምኩት አክብሮት ጎድሎኝ ሳይሆን የጤና፣ የእንሰሳት ወይም የሥነ ልቦና ሐኪም ላልሆነ ሰው ‹‹ዶ/ር›› የሚለውን ማዕረግ ከሥም በፊት መጠቀም አግባብ ስላልሆነ ነው፡፡

ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ በአሜሪካ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን የሕግ (Juris Doctorate) ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቢቀበሉም ‹‹ዶ/ር ኦባማ›› ተብለው ተጠርተው አያውቁም፡፡ ስለዚህ እርስዎንም የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ሆነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ 6 ኪሎ በምሰራበት ጊዜ አገልግሎት ከምሰጣቸው ተማሪዎች መካከል ጥሩ ሥነምግባር ያላቸውና አርቆ አስተዋይ፣ አንደበተ ርቱዕ የሆኑት የገዢው ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጉድፍ ጠራጊ የሕዝብ አንደበት፣ ዓይንና ጆሮ ለሆኑት ነፃ ፕሬሶች በማቀርባቸው መጣጥፎች ከብዙ የወከባ እና የማሳደድ ድርጊቶችና አደጋዎች ያዳኑኝ፣ የአሁኑ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ክቡር ወርቅነህ ገበየሁን እንዲሁም የውቢቱ የጣና ፈርጥ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ደረሰ ሳህለን ‹‹ዶ/ር›› ብዬ አልጠራም፡፡ በአንፃሩም የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰን የጤና ሐኪም ስለሆኑ ከሥማቸው በፊት ‹‹ዶ/ር›› ብዬ እጠራቸዋለሁ፡፡ ዶክትሬቱ ከሕክምና ውጪ ለምሳሌም የፍልስፍና፣ የቴክኒክ ከሆነም ግለሰቡን አንዴ ለማስተዋወቅ ከሥም በኋላ በቅንፍ ይቀመጣል እንጂ በሁሉም ቦታ ‹‹ዶ/ር›› እየተባለ አይጠቀስም፡፡ ማዕረጉን ከፈረንጆቹ መውሰዳችን ካልቀረ ልክ እነርሱ እንደሚገለገሉበት መገልገል ያለብን ይመስለኛል፡፡

ለማንኛውም ወደተነሳሁበት ቁም ነገር ልግባና ያኔ ሀገራችን ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሯት ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ በተመረጡበትና ሀገራችን እስከዛሬ ከመሯት መሪዎቻችን በተለየ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ አርባ ጊዜ እንደተጠቀሰችው ሁሉ በመሪ አንደበትዎ እንደዛ ተደጋግማ ስትወደስና ስትከበር እንደመስማት ያለ ፈውስ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር በተስፋ ያለመለመ ንግግር ከአደረጉበት ጊዜ አንስቶ በሄዱበት ሥፍራ ሁሉ ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳንመርጥ በፍቅር በደስታ ከጎንዎት ነን በሚል ስሜት ደግፈንዎታል፡፡ በተለይ በሙሉ ቀን ቀርቶ አምስት ደቂቃም በገንዘብ በሚተመንበት በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎሳንጀለስ፣ በሚኒስታ፣ ከመላው አውሮፓ የተውጣጡ በፍራንክፈርት በዚያ ብርድ ከሚኖሩ ዲያስፖራ ወገኖቻችንም ድጋፍ አልተነፈጉም፡፡

ይሁንና ሰኔ 16 ቀን በመስቀል አደባባይ በመገኘት ድጋፋቸውን በሰጡበት ጊዜ እኔም አዲስ አበባ በአካል ተገኝቼ ድጋፌን ለመሥጠት ባልታደልም ይዋል ይደር እንጂ እንደማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በነፃ ፕሬስ ‹‹አሃድ›› መጽሔት ላይ ‹‹ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር›› በሚል ርዕስ ከሙሉ ቁመና ምስልዎት ጋር አስደግፌ በሙስሊሙ ነብይ፣ በክርስቲያኑ ደግሞ በጨለማ ላይ የተገኘ ብርሃን፣ በፈርኦን ቤት ያደገ ሙሴ፣ በገደል ውስጥ የተገኘ ሜዳ፣ በአረንቋ ላይ የተገኘ ድልድይ የሚል መጣጥፍ በማቅረብ በእርስዎ የመልካም ንግግር ምክንያት ብቻ ለውጡንም ሆነ የብልፅግና ፓርቲዎን በሙሉ ልቤ ደግፌአለሁ፡፡

በመስቀል አደባባይ ድጋፋቸውን ለመግለጽ በታደሙበት ጊዜ በተሞከረብዎት የግድያ ሙከራ እጅግ አዝነናል፡፡ በተቃጣብዎት የግድያ ድግስ ሰፊው የአዲስ አበባ ወጣት ተረባርቦ በመቁሰል፣ በመድማት፣ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ታድገዎታል፡፡ ወዲያውኑም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውን በየሆስፒታሉ በመሄድ ከአጽናኑአቸው በኋላ ምሽቱን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ታሪካዊ ንግግር ካደረጉ በኋላ ‹‹…የኢትዮጵያ አምላክ፣ የኢትዮጵያ እናቶች በፀሎት ይጠብቁኛል›› እንዳላሉ ሁሉ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግና ደንብ ባፈነገጠ መንገድ በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት የተመራ የተለያዩ አባቶችን ኤጲስ ቆጶስነት በመሾማቸው እነዚህ የተሿሿሙትን የቤተክርስቲያን አፈንጋጭ አባቶችን ለማውገዝ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምህላ ላይ ‹‹…ባለፉት ዓመታት ያልተፈፀመ፣ ያልተደረገ፣ ያልሆነ፣ ያላየነው መከራ ምን አለ? ግን ምንም አላልንም፡፡ ዝም ነው ያልነው አሁን ግን ለገዥዎቻችን እንናገራለን፡፡ ስንከፋ መተከዥያ፣ ስንራብ ስንታረዝ መማጸኛ፣ ስታሳድዱን መሸሸጊያ፣ ስታፈናቅሉን መጠለያ፣ ስትገሉን መቀበሪያ ጥላችንን የሰላሙን ቦታ ተውልን፡፡ ቢያንስ ይህን ባለማድረግ ተባበሩን፡፡ እጃችሁን ከቤተክርስቲያናችን ላይ አንሱልን›› እያሉ ጥቁር ለብሰው ማቅ ሆነው በቤተክርስቲያን ደጃፍ ተንበርክክው የሚያለቅሱ እናቶችን ሲያዩ ምን ይሰማዎት ይሆን? ይፀልዩልኛል ያላቸው እናቶች የትኞቹ ይሆኑ?

አፈሩ ገለባ ያድርግላቸው እንጂ በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ በፋሲል ክ/ከተማ ቀበሌ 04 ነዋሪ የነበሩት እና መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩኝ የ90 ዓመት አዛውንት ወላጅ እናቴ እማማ የሻረግ ካሳ ረታ በፓርቲዎ ብልጽግና ሆነ በጣና ፎረም ስብሰባዎች ወደ ውቢቱ ባሕር ዳር ከተማ ብቅ ሲሉ ወደ መንበረ ሥልጣንዎ በሰላም እንዲደርሱ የሚመኙልዎት እንዲሁም ለሁለት የተከፈሉት የቤተክርስቲያናችን አባቶች አንድ በማድረግዎ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከነ ባለቤትዎ የወርቅ ወንጌል እና ካባ ስታለብስዎ የተሰማቸውን ደስታ በእንባ ታጅበው ያየሁትን ስሜት ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ምን ይሰማቸው ይሆን እላለሁ፡፡

ለዚህም ሀዘን የዳረጉን የትናንት የሃይማኖት አባቶች እስከዛሬ ድረስ ውግዘቱ ያልተነሳላቸው የዛሬ አባቶችን እርስዎ አይዟችሁ ባይሏቸው ከአዲስ አበባ ርቀው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሽፋን ተደርጎላቸው ሕገወጥ ስራ አይሰሩም ነበር፡፡ የካብኔ ሚኒስትሮችዎን በመሰብሰብ አንድም ሰው ጣልቃ እንዳይገባ የሚል ዛቻ አይሉት የማስፈራሪያ መመሪያ በማስተላለፍ ይበልጥ ደግሞ በእምነቶች መካከል ጊዜ ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ የጥላቻ ንግግር በማድረግዎ በዚህ የልብ ልብ የተሰማቸው ሕግ አስከባሪዎችም ጳጳሳት እንዳይንቀሳቀሱ፣ ካህን በዱላ ተቀጥቅጦ የሚገደልበት እና በጥፊ የሚመታበት ምዕመናኑም እየተሳደዱ የሚታሰሩበት በመሳሪያ የሚገደሉበት በአጠቃላይ የቤተክርስቲያናችን ክብር ዝቅ በሚያደርግ ድርጊት አይሰለፉም ነበር፡፡

እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጡንቻዎቻቸው ፈርጠም ፈርጠም ያሉ ወጠምሻዎች ካብኔ አቋቁመው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሾሙ ምን ያደርጋሉ? ያም ሆነ ይህ የአማራ ክልላዊ መንግስት ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ ‹‹አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትሪያርክ፣ አንድ መንበር›› በሚል መግለጫ በማውጣቱ የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማትም በእናት ቤተክርስቲያን ላይ የተፈፀመውን አሳዛኝ ድርጊት በማውገዛቸው የእምነት ተከታዮቻቸውም ግፍን እንታገላለን፣ ነውርን እንፀየፋለን፣ የቤተክርስቲያኗ ውርደት ውርደታችን ነው ክቡሯም ክብራችን ነው አጥሯ ተነቅሎ የኔ አጥር አይቆምም፣ ሁሌም ከተገፉት፣ ከተበደሉት ጎን ነን፡፡ እዘዙን እንታዘዛችኋለን፡፡ ክብር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እስከማለት ደረጃ በመድረሳቸው የእምነት ልጆቿ የሆኑ የሕግ ባለሙያዎችም ተሰባስበው ከቤተክርስቲያኗ ጎን በመቆም ለፍ/ቤት አቤት በማለት የመጀመሪያ የሕግ ድጋፍ በማግኘቷ እንዲሁም የካቲት 5 ቀን በጠራችው የተቃውሞ ስብሰባ አፈንጋጮችም በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ ቀን እና ቦታ የስብሰባ ጥሪ በማድረጋቸው ከዚህ እለት በፊት ባደረጉት የማግባባት ጥረት የበለጠ ደም ከማፍሰስ በማዳንዎት በእምነቴና በቤተክርስቲያኔ ስም ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይሁንና የማግባባት ጥረትዎት ደም ከፈሰሰ፣ ሰው ከሞተ በኋላ መሆን አልነበረበትም፡፡ እርስዎ ግን ደም ከፈሰሰ ሰው ከሞተ በኋላ ነው እንቅስቃሴ የሚያደርጉት፡፡ ለምን እንደሆነ ግን እስካሁን ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ምን አልባት ደም አቃብተው በማስታረቅ ከደሙ ንጹህ ነኝ ለማለት ፈልገው ይሆን?

ሌላውም ከለውጡ በፊት በዘሩ ተመርጦ የተወለደ ያለ ይመስል በኦሮሞ ተወላጅነታቸው ብቻ እየታደኑ የሚፈፀምባቸውን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት በማውገዝ ‹‹የኦሮሞ ደም የእኔም ደም ነው!!!›› በማለት የለውጡ መሐንዲስ በመሆን በ17 ቀናቱ ፍጥጫና ትንቅንቅ ላይ መሪ ተዋናይ በመሆን የተጎነጎኑ ሴራዎችን አክሽፎ ወሳኙን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በብልጠት በመወጣት ለእርስዎ ሆነ አሁን የኦሮሚያን ክልል ለሚመሩት የሥልጣን ወንበር ወደ ፊት የማምጣት ከፍተኛ ድጋፍ የአደረግነውን ከማንኛውም ኢትዮጵያውያን ጋር በአምቻ ጋብቻ ተሳስረን፣ ተዋልደን በአንድ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለነውን ማህበረሰብ ከእለት ወደ እለት ማንንም በሕግ ተጠያቂ በማያደርግ መልኩ ከኢትዮጵያዊነት ወደ አማራነት፣ ከአማራነትም ፈጥፍጠው ወደ ተራ ሰውነት አውርደው በሴራ መዶሻ ሊያጠፉን ከቤት ንብረታችን በማፈናቀል እንደጦስ ዶሮ እየታረደ፣ በጅምላ እየተረሸነ የዘር ማጥፋት ድርጊት እንዲፈፀምብን በሸገር ከተማ ምስረታ ላይ ቤታችን እየተመረጠ እንዲፈርስብን የመንግስታዊ አመራሮች እውቅናና ድጋፍ ያለበት ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡

አሁን ደግሞ በቅርብ ወራት በተመሳሳይ ሁኔታ በሕትመት ወረቀት ውድነት ምክንያት ከገበያ በጠፋችው ‹‹ሐበሻ ወግ›› መጽሄት ላይ የቀኝ ገዢዎችን ቅስም በአድዋ ጦርነት ድል የሰበረች፣ በዚህም በመላው ዓለም በባርነት ቀንበር ሲማቅቁ ለነበሩት መመኪያ የፓን አፍሪካኒዝም ታሪካዊ መገኛ፣ የአፍሪካውያን መንፈሳዊ መዲና፣ የኢትዮጵያዊያን መናገሻ ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባን እስከዛሬ ከመሯት የመጀመሪያዋ እንስት ከንቲባችን በሚል መጣጥፍ በማቅረብ እንዳላደነቅኳቸው ሁሉ ዛሬ የጠባብ ብሔርተኝነት አመለካከት ካላቸው ጋር ተናበው ያውም ዋና ከተማዋ የሁላችንም መሆኗ እየታወቀ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉባት ከተማ ይመስል ትላንት በሰሜኑ ሀገራችን በተፈጠረው ችግር ቀይ መስመር በሚል ብሔራዊ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው እንደ ፓርቲአቸው የብልጽግና አቋም (እስከ ዛሬ የማስተባበያ ሀሳብ አልተሰጠበትም) ‹‹እዚህ ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ችለናቸው ነው ያለነው፣ ወደ መጡበት ክልል መሄድ ይችላሉ›› የሚል አንደኛው ባለቤት ሌላው ባለቤት አልባ እንደሆነ የጅምላ ፍርድ መሥጠታቸው ይታወሳል፡፡

ዛሬ ደግሞ ‹‹አንዳንድ ክልሎች›› በሚል ስም ጠቅሰው በአኀዝ አስደግፈው መቀመጫ መቆሚያ ያጣውን የአማራ ተወላጆች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደ ከተማዋ በሚያደርጉት የመንቀሳቀስ መብት እንደ ፍልሰት በመቁጠር በምርጫ የተመረጠውን ሕጋዊ የመንግሥትን ስርዓት ለማውረድ ነው በሚል የመፈንቅለ መንግስት ቅንብር ስም ከነሱ የአመለካከት ፍላጎት ውጭ የሆኑትን ለማጥራት በሚያደርጉት ጥረት እና ውዝግብ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከወዲሁ አንድ መፍትሄ ካላፈላለጉ የአማራው ክልላዊ መንግስታችን በቤተክርስቲያናችን ላይ ተደቅኖ የነበረውን ችግር መሰረት ባደረገ በአወጣው መግለጫ ከማዕከላዊ መንግስቱ አቋም ጋር የሚቃረን የማይጣጣም የተሰጠ መግለጫ ነው ከሚሉ ከፌደራል መንግስቱ የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር በባህር ዳር ከተማ በተደረገው ዝግ ስብሰባ ላይ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንስተው እንደተወያዩት የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሐላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ‹‹ያመኑትን አሳምነን ያላመኑትን አደናግረን…›› ለሚሉት የቁጭት የበታችነትና የበቀል ስሜት ለተጠናወታቸው የታሪክ ምርኮኞች የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብ ‹‹… እኔ እንቅልፍ አጥቻለሁ፡፡ ትላንት አጥፍተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እንክሰዋለን ብለን ምህረት ያደረገልን ህዝብ በተለይ ደግሞ ለእኛ የአማራ ህዝብ አደራ ቢሰጠንም እኛ ግን እየዋለ እያደረ ይህንን ህዝብ ከጥቃት ለመታደግ አልቻልንም፡፡ ይህን ሁልጊዜ ሳስብ እኛ ስልጣን ላይ መኖራችን ጥቅሙ አልታየኝም አንዳንድ ጊዜ ይህ ህዝብ ምን አድርጋችሁልን ነው ቢለን ምን ልንመልስለት እንደምንችል ግራ ይገባኛል ስልጣን ኑሮኝ ስልጣን እንደሌለኝ ይሰማኛል›› የሚል አንጀት የሚነካ ልብን የሚያርስ ንግግር አድርገዋል፡፡

የክልል ፕሬዘዳንታችንም ‹‹…የአማራ ህዝብ ታጋሽነት በማሞገስ ይህ ሕዝብ ይለያል፡፡ ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰበት በተስፋ የሚኖር ድንቅ ህዝብ ነው፡፡ ይህን ህዝብ ከዚህ በላይ መበደል ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ይታሰብበት ይበቃል ! ይህን ሕዝብ ልንታደገው ይገባል›› የሚል የመጨረሻ የውሳኔ ሀሳብ  እንዳስተላለፉት በስተመጨረሻ ላይም ክልላዊ መንግስታችን እንዳወጣው ጠንካራ መግለጫ ሌሎችም ለምዕተ አመታት አቃፊ የሆነውን በተረኝነት የግዛት ማስፋፋት በማነሳሳት ከአማራ፣ ከሱማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከቢንሻንጉል፣ ከሲዳማ፣ ከጋሞ መሬት ይገባዋል በሚል ግልጽ ወረራ የተፈፀመባቸው ከፍተኛ ክልላዊ አመራሮች ድረስ በግልጽ፣ በስውር እና በህቡዕ በሚያደርጉት የመተባበር ድጋፍ ለብልጽግና ፓርቲዎ መሰነጣጠቅ ለስልጣንዎ ውድቀት ለሀገሪቱ መበታተን ብቻ ሳይሆን የዘር ማጥፋት ድርጊቶችም ሁሉ ተጠያቂ ያደርግዎታል፡፡ እንዲህም ስልዎት ኢትዮጵያን ሊቀብሯት ያሰቡትን የቀበረች ሀገር ናት የሚሉትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) አገላለጽ ትዝ አለኝ፡፡ እውነትም የኢትዮጵያ አምላክ አንድ ቀን ፍርዱን ይሰጣል፡፡                               

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...