ዳንኤል ገዛኸኝ ፤ ሞትን የተጋፈጠው ጋዜጠኛ!

Date:

ዳንኤል ገዛኽኝ ውልደቱ በ1967 ዓ.ም በሐረር ከተማ ነው። ትምህርቱን በደገሃቡር አውራጃ፤ በጅጅጋ ከተማ እና በሐረር ተከታትሏል። የሥነ-ጽሑፍ ሕይወቱ ጅማሮ የሚነሳው ከሐረሩ ብራና የኪነ-ጥበብ ማዕከል ሲሆን፣ በሐረር ሬድዮ ጣቢያ አጫጭር መሠረታዊ የዜና አቀራረብ እና አዘጋገብ ኮርስ እንዲሁም በሐረር ክልል 13 ባህል እና ማስታወቂያ ቢሮ የቴአትር ትወና እና አጻጻፍ ጥበብን የአንድ ዓመት ሥልጠና ተከታትሏል።

በሐረር ከተማ በ1985 ዓ.ም ‹‹እልቂት›› የተሰኘ የሙሉ ሰዓት ቴአትር ጽፎ ከሙያ ጓደኛዎቹ ጋር ለሕዝብ በማቅረብ ገቢው በወቅቱ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲውል አበርክቷል። ከዚያም የተለያዩ ነጻ ጋዜጦች ላይ በአምደኝነት እየሰራ በትፍላሜ እና በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ዓመት መሠረታዊ ጋዜጠኝነት ኮርስ ተከታትሏል።

በመቀጠል ‹‹ገመና›› በተሰኘው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩረው ነጻ ጋዜጣ ላይ ሕትመቱ እስከተቋረጠበትና በመንግሥት ኃይሎች እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ በዋና አዘጋጅነት ሲሰራ ቆይቷል። በኋላም በሞገድ ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ካገለገለ በኋላ በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና እና ጥቃት ሙያውን ለመተግበር እንደማይችልና ህይወቱ አደጋ ላይ እንደወደቀች ሲረዳ አገር ጥሎ መውጣት የግድ ኾኖበታል፡፡

ጋዜጠኛው ከሃገር በስደት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ እንደ በርካታ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ሁሉ ከመንግሥት ኃይሎች እሥራት፣ ወከባ፣ ድብደባና በቅልብ ውሻ የመነከስ ጥቃት ተሰንዝሮበታል። በስደት በየመን ለአራት ዓመታት ተኩል ሲቆይ የመንግሥት ደጋፊዎች የጥገኝነት መብቱን አስነጥቀው ወደ ሃገሩ የመመለስ ሙከራ ሲያደርጉበት፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ኢቲቪ›› በሃገር ውስጥ ነውጥ ቀስቃሽነት እና በሃገር ከጂነት ወንጅሎ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶበታል። ጋዜጠኛው በስደት ሃገር ያለፈበትን ጥልፍልፍ የስደት ጉዞ አስመልክቶ ‹‹ሲዋን›› በሚል ርዕስ የመጀመሪያ መጽሐፉን ለንባብ ያበቃም ሲኾን፣ የመን በነበረበት ወቅት በርካታ መከራዎች እና ፈተናዎች ቢገጥሙትም ለችግርና ለፈተና ሳይበገር በየመን፣ በሳዑዲ ዐረቢያ እና በሌሎችም የዐረብ ሀገራት እንግልት እና ስቃ ለደረሰባቸው፣ ለተጎሳቆሉና በዓረብ ሀገራት የጸጥታ ሰራተኞች በደል ይፈጸምባቸው ለነበሩ ብዙኃን የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ዓለም አቀፍ ድምጽ ኾኖ አገልግሏል፡፡ ዳንኤል ገዛኸኝ በስደት ከኖረበት ሃገረ የመን ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ በዚያው በነበረው ቆይታ ‹‹ማዕዶት›› የተሰኘ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን (ዩ ቲ ዪብ) በማቋቋም የሃገሩን፣ የወገኖቹን አንገብጋቢና ወቅታዊ ጉዳዮች ለአንባቢዎቹና ለአድማጮቹ ያቀርብ ነበር።

በአሜሪካ ለአመታት የቆየው ከሰው ሰራሹም አገዛዝ አፈና እና ከተፈጥሮው ሕመምም ጋር ለአመታት በአይበገሬነት የታገለው ምግባረ ሰናይ ብርቱው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ፣ ከኩላሊት ሕመም ፈተናው ጋር ሆኖ ማዕዶት ሚዲያን እና በአሜሪካ ዳኮታ የኢትዮ ሱፎልስ ማህበረሰብ ቅርርብና ትብብር እንዲጎለብትና የላቁ ኢትዮጵያውያን ጎላ ብለው እንዲታዩ ብሎም ባለበት ግዛት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመራቂ ተማሪዎች ከብረው እንዲነሱ ሲያደርጋቸው የነበሩ ጉልህ የፊታውራሪነት ምግባረ ሰናይ ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀስ ሲኾን፣ ከዚህም ባሻገር በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚወለዱ ልጆችን አማርኛ እና ግዕዝ ያስተምር እና የኢትዮጵያን ባህልም እንዲያውቁ ሲለፋና በችግር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እርዳታ አንዲያገኙ ያስተባብር ነበር።

መከራ የተከተበለት ይመስል ሕይወቱ በወጀብ የተሞላና የዕረፍት ትንፋሽ ሳያገኝ የኖረው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኖርበት ሳውዝ ዳኮታ በአቬራ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ እስከወዲያኛው ከዚህ ዓለም ድካም በሞት ተለይቷል። የዚህ የነፃው ፕሬስ ባልደረባ እና ፋና ወጊ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ የቀብር ሥርዓትም ነሐሴ 9 ቀን  2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቤቴል ወይራ ሠፈር በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘመዶቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹ እና ወዳጆቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡

***

ዳንኤል እና ሕይወት

(ከ‹‹ሲዋን›› መጽሐፉ የተቀነጨበ)

በሕይወት ለመቆየት የሰው ልጆች ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች ዋና ዋናዎቹ ተብሎ የተጠየቀ ሁሉ አስቀድሞ የሚመልሰው የታወቁትን መሰረታዊ ጉዳዮችን እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ምግብ እና ውሃ በሌለበት እንደ እኔ ለቀናት ፍዳውን ያየ፤ አበሳን የቆጠረ ደግሞ ከተስፋ በላይ ምንም የለም ቢል አይገርምም። በአንጻሩ በመንፈሳዊ አስተምህሮትስ ቢሆን ሰው በምግብ ብቻ እንደማይኖር ተመልከቶስ የለ። የኔው ግን የተለየ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ሊያስበው ይችላል ይሞክረው ብዬ ግን ሙግት አልይዝም፡፡ ምክንያቱም እኔ በዚያ መከራ አልፍ ዘንድ የግድ ነበር እና ነው በዚያ ሁኔታ ማለፌ እና መፈተኔ፡፡

‹‹ተስፋ የህይወት ስንቅ ነው›› ያለው ማን ነበር?… ዘነጋሁት። ግን አባባሉን ልዋሰው አዎ ተስፋ የህይወት ስንቅነቱ ግን የሚያከትመው ከውስጥዎ ቆርጠው የጣሉት ዕለት ብቻ ነው። እነሆም በህይወት ነገን ለማየት ስለነገው ለመኖር በተስፋ መጉዋዝ መጪውን ብሩህ ያደርገዋል፡፡

የዘመናት ህልሙን እውን ለማድረግ የበረሃ ላይ ነፍሳትን ምሳሌ በማድረግ ያቺን ቁንጽል አጋጣሚ እንደ ሕይወት መመሪያው በመውሰድ ለትልቅ ውጤት የበቃውን የአሜሪካውያንን ኩራት አብርሃም ሊንከልንን ማሰብ በቂ ነው ሰለተስፋ ዋጋ ለመረዳት እላለሁ እኔ በበኩሌ።

ስለዚህ ህይወትን ደግሞ አንድ ቦታ ብቻ ከተንጣለለው ውቅያኖስ መሃል መልህቅን ጥሎ በጨረቃ ዳቦ ጣይልኝ ስሌት አይኖሩዋትም፡፡ ምክንያቱም ባሉበት ረግጠው በተስፋ የሚቆዩባት አይደለችም እና ነው ህይወት። እኔም ከህይወት መመሪያ የምጋራ ህይወትን የተቁዋደስኩ አንዱ አካል እንደ መሆኔ ህይወት ብታዝም ባታዝም ለጊዜውም ቢሆን ጉልበተኞች በሚያዙባት አለም ያለሁ የጉልበተኞች ጉልበት መወጪያ፤ የፍርደ-ገምድሎች ሰለባ ሆንኩኝ።

ሃገሬን እየወደድኩኝ ተገድጄ ግን ደግሞ እስራትን መጋዝን፤ ያለ አግባብ መቁሰል፤ መድማትን ለአመታት ኖሬበት የአበሳው ገፈት ሲያንገሽግሽኝ ካሳለፍኩዋቸው የባሰ ወደ የሚመረው ስደት ለመግባት ተገደድኩኝ። ሰው እኮ የማይናገርን ያናግራል ራሱ በተረተው ተረት “ኑሮ ካሉት…” በሚለው ተረቱ ውስጥ “ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል “አለች ኮካ ኮላ” በማለት ከስቃይም በላይ ስቃይ ያለበት ህይወት… ህይወት ተብሎ በግድ ያለ ውድ እንደሚመረጥ ያመላክታል ሰው፡፡

ብታምኑም ባታምኑም እኔ ከሞት ጋር ተያይቻለሁ። ሞትን ተመልክቼዋለሁ፡፡ በርግጠኝነት ነው የምነግራችሁ ሞትን ፊትለፊት ተጋፍጨዋለሁ ግን ሞትን በይፋ አሸነፍኩት። አባባሌ ማንንም ግር ለማሰኘት ውይንም ደግሞ የሌለኝን መለኮታዊ ሃይል እንዳለኝ የማወራ ያልሆነውን የምቀባጥር ሃሳይ መሲህ እንዳልመስላችሁ። እራሴንም የመለኮታዊ ሃይልን የታደልሁ አድርጌ ያቀረብኩ አድርጋችሁም አትመልከቱኝ ያለሁት ከህሊናዬ ጋር ነው የምጽፈው የደረሰብኝን ነው።

እነሆ የዚህ መጽሃፍ መወለድ የአምባገነኖች ፍርደ-ገምድል የፍትህ ስርዓት ውጤት ነው፡፡ ከፋት ክፋትን ይወልዳል እንጂ የሰውልጆችን በሃይል በበትር ለማሳመን መሞከሩ ትርፉ የሚወልደው አመጽን፤ ሽሽትን፤ ስደትን ብቻ ነው። ዛሬ ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጲያ ሃገራቸው ላይ በተለያዩ አያሌ ምክንያቶች ሳቢያ መኖር አቅቶዋቸው ዜጎቻቸው ከሚሰደዱባቸው ሃገራት መሃል የአንበሳውን ድርሻ የምትይዝ በመሆን ረድፉን ትመራለች።

ቢሆንም ግን አምባገነኖች አልሆን ብሎዋቸው በድንበር ሃገር እየለቀቀ የሚሄደው ዜጋ ከቀን ቀን ቁጥሩ ሲያይል ከሰው ልጆች የመንቀሳቀስ ነጻነት ጋር ለማያያዝ ይሞከራሉ። በለስ ሲቀናቸው ደግሞ ባመቸው መስመር ከሃገሩ የሚሸሸውን እየያዙ ያሻቸውን ያደርጉታል። ወዲያውም የደሰኮሩለትን የመንቀሳቀስ መብቱን ይገድባሉ ማለት ነው፡፡

እንደ እኔ ነጻነቱን በሃገሩ ላይ ተነፍጎ በፖሊስ እንደ ክፉ ወሮበላ ሲታደን ማጣፊያው አጥሮት የስቃይ የስደት ህይወትን የመረጠው ዜጋ ህይወት አሳሳቢነት ሲወሳ አምባገነኖቹ እና ተከታዮቻቸው የተሻለ ናፋቂ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። ማንም ለሴኮንድ ያስበው ገቢው ምንም ይሁን ምንም፤ በሃገሩ ላይ የተከበረ ሞያ ያለው ሁሉ በአብዛኛው በሃገሩ ላይ በሞያው መስራትን ይሻል እንጂ የማንም የበታች አገልጋይ ለመሆን አይሰደድም፡፡ እናም ነጻነቱን ያጣ ዜጋ ግን በባዕድ ሃገር አሽከር አይደለም ሎሌ ቢሆንምን ይገርማል? ምንምአራት ነጥብ።

በህይወቴ ውስጥ የስደትን ውሳኔ እንድወስን ያደረገኝ ጦሱ ምርጫ 97 ነው። ምንም እንኩዋን በምርጫው ከተከሰስኩባቸው ጋር ተደምረው ሌሎቹንም ጨምሮ ከሞያዬ ጋር የተያያዙ ስድስት ክሶች ውስጥ በምርጫው ዋዜማ እና ማግስት ከተከሰስኩባቸው በሶስቱ በዋስትና የምከራከርበትን ይሁንታ ከ ፍርድ ቤት ባገኝም፤ ነገር ግን በ1993 ሚያዝያ ወር መደበኛ የከስ ፋይል ተከፍቶብኝ በወረዳ አስራ አራት ለአስራ አምስት ቀናት፤ እንዲሁም በዋናው ከርቸሌ እስር ቤት ለአንድ ወር ታሰርኩ።

ምክንያቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አልሳዕ፤ ሊቀ ዲያቆን ታደሰ እንግዳ፤ እና ዲያቆን ደሳለኝ ፈንቴ፤ የመዘበሩት የቡና ሽያጭ ከስ ጉዳይ ነው።

አቶ ታምራት ላይኔ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ዘመናቸው ከካህናቱ ጋር በመተባበር ሰለተፈጸመ የሙስና ተግባር ላይ የሚያጠነጥን በመረጃ የተደገፈ ሪፖርት ዘገባ ቀደም ሲል በዋና አዘጋጅነት እሰራበት በነበረው የገመና ጋዜጣ ታትሞ ወጣ። ጉዳዩ በዓመታት ልዩነት በክርከር ቆይቶ ለፍርድ ውሳኔ አንድ ቀን ሲቀረው የማላውቀው አዲስ ጉዳይ ደግሞ በሞባይል ሰልኬ ተደውሎ የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ፖሊሶች ሁሌም እንደሚያደርጉት ለጥያቄ እንደምፈለግ ይነግሩኛል፡፡

ወቅቱ ከቅንጅት ባለስልጣናት ጋር የተከሰሱ ጋዜጠኞች ወንጀል ምርመራ እስር ቤት የገቡበት በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ መርማሪዎች ሲጠሩኝ ለመሄድ ድፍረቱን አላገኘሁም። ምክንያቱም እስራቱ በዋስ ለመለቀቅ እድል የማይሰጥ እንደሆነ ስለተረዳሁ ማለት ነው።በነገራችን ላይ ለፍርድ ውሳኔ ያበቃኝን እና ሳይፈረድብኝ ያመለጥኩበት የቡና ምዝበራ ከስ የባልደረባዬ የገመና ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ እና አሳታሚ የጋዜጠኛ ግሩም ተከለሃይማኖት ምርጥ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጥረት የታከለበት የሪፖርት አስትዋፆ ያለው ሲሆን የጋራ ሰራችን በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በደፈናው ሁለታችንም በወረዳ 14 ፖሊስ ታስረን በቅልብ ውሻ እስከማስነከስ የደረስ የጭካኔ ተግባራቸውን የወረዳው ፖሊሶች ፈጽመውብናል። ሆኖም በፕሬስ ህጉ መሰረት ሃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ዋና አዘጋጁ ነው በሚለው አንቀጽ ጋዜጠኛ ግሩም ተከለሃይማኖት ከከሱ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

ስለዚህ ይህ ከስ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ውሳኔ ከሚሰጥበት ቀን ከመድረሱ በፊት በሁኔታው ዙሪያ ከህግ ባለሞያ ጋር የከሱን ዝርዝር ሃተታዎቹን በማቅረብ ለመመካከር በነበረችኝ አጭር ጊዜ ሙከራ ማድረጌ አልቀረም።

በዚሁ መሰረት የፍርዱ ሂደት እስከ አራት አመታት እኔን በጽኑ እስራት ሊያስቀጣኝ እንደሚችል ነበር ከህግ ባለሞያ ያገኘሁት ምክር የሚያስረዳው። የህግ ባለሞያው የሚሉት ታዲያ ከያዝኩት የመከራከሪያ ጭብጥ አንጻር ብዙ እኔን ነጻ የሚያወጡ መንገዶች ቢኖሩም ነገር ግን መንግስትም ሆነ ነጻ ስላለመሆኑ እማኝ የማይጠራበት የሃገራችን ፍርድ ቤቶች እና ጉዳዬ የሚታይበት የዳኛ ልዑል ዝማርያም አምስተኛ ችሎት የሚያስተላልፈው የፍርድ ውሳኔ ከላይ የተገለጸው ውሳኔን የሚበልጥ እንጂ ከሱ የሚያንስ እንደማይሆን ባለሞያው አስረዱኝ።

በሁዋላ ለውሳኔ ተቸግሬ ሳለ ነበር እንደገና ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የፖሊስ የትፈለጋለህ ጥሪ የቀረበልኝ። ስለዚህ የፖሊሶቹን ጉዳይ እንደሌላው ጊዜ ቸል የምልበት ምክንያት ስለሌለ ውሳኔ መወሰን ነበረብኝ። ውሳኔው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እሱም ከሆነ ስደቱን በሃገር ውስጥ መቀጠል ካልሆነም ድንበር በማቁዋረጥ ሃገር ለቆ መውጣት።

ምንጊዜም የአምባገነኖች ተግባር ንጹሃንን ሃገራቸውን ባንዲራቸውን መንጠቅ ነው፡፡ እኔም ለዓመታት ይህንን ሰጽፍ ኖሬያለሁ። ዛሬ ደግሞ በእኔ ላይ ደርሶዋል። ይህንን ስል ታዲያ ለበርካታ ጊዜዎች በሚደርሱባቸው ወከባዎች ሳቢያ ከሃገር ውስጥ ስደት አንስቶ ድንበርን አቁዋርጦ ከሰው ሃገር ግዞት ድረስ የተዳረጉትን የኢትዮጲያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኛዎች ሁሌም በጀግንነታቸው አስታውሳቸዋለሁ። ማንም የኢትዮጲያ ፕሬስ ቤተሰብ አይረሳቸውም። …

ግዮን ቅጽ 6 ቁጥር 215 መስከረም 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...