ዳንኤል ገዛኸኝ ፤ ሞትን የተጋፈጠው ጋዜጠኛ! (ከ1967-2016 ዓ.ም)

Date:

ዳንኤል ገዛኽኝ ውልደቱ በ1967 ዓ.ም በሐረር ከተማ ነው። ትምህርቱን በደገሃቡር አውራጃ፤ በጅጅጋ ከተማ እና በሐረር ተከታትሏል። የሥነ-ጽሑፍ ሕይወቱ ጅማሮ የሚነሳው ከሐረሩ ብራና የኪነ-ጥበብ ማዕከል ሲሆን፣ በሐረር ሬድዮ ጣቢያ አጫጭር መሠረታዊ የዜና አቀራረብ እና አዘጋገብ ኮርስ እንዲሁም በሐረር ክልል 13 ባህል እና ማስታወቂያ ቢሮ የቴአትር ትወና እና አጻጻፍ ጥበብን የአንድ ዓመት ሥልጠና ተከታትሏል።

በሐረር ከተማ በ1985 ዓ.ም ‹‹እልቂት›› የተሰኘ የሙሉ ሰዓት ቴአትር ጽፎ ከሙያ ጓደኛዎቹ ጋር ለሕዝብ በማቅረብ ገቢው በወቅቱ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲውል አበርክቷል። ከዚያም የተለያዩ ነጻ ጋዜጦች ላይ በአምደኝነት እየሰራ በትፍላሜ እና በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ዓመት መሠረታዊ ጋዜጠኝነት ኮርስ ተከታትሏል።

በመቀጠል ‹‹ገመና›› በተሰኘው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩረው ነጻ ጋዜጣ ላይ ሕትመቱ እስከተቋረጠበትና በመንግሥት ኃይሎች እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ በዋና አዘጋጅነት ሲሰራ ቆይቷል። በኋላም በሞገድ ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ካገለገለ በኋላ በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና እና ጥቃት ሙያውን ለመተግበር እንደማይችልና ህይወቱ አደጋ ላይ እንደወደቀች ሲረዳ አገር ጥሎ መውጣት የግድ ኾኖበታል፡፡

ጋዜጠኛው ከሃገር በስደት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ እንደ በርካታ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ሁሉ ከመንግሥት ኃይሎች እሥራት፣ ወከባ፣ ድብደባና በቅልብ ውሻ የመነከስ ጥቃት ተሰንዝሮበታል። በስደት በየመን ለአራት ዓመታት ተኩል ሲቆይ የመንግሥት ደጋፊዎች የጥገኝነት መብቱን አስነጥቀው ወደ ሃገሩ የመመለስ ሙከራ ሲያደርጉበት፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ኢቲቪ›› በሃገር ውስጥ ነውጥ ቀስቃሽነት እና በሃገር ከጂነት ወንጅሎ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶበታል። ጋዜጠኛው በስደት ሃገር ያለፈበትን ጥልፍልፍ የስደት ጉዞ አስመልክቶ ‹‹ሲዋን›› በሚል ርዕስ የመጀመሪያ መጽሐፉን ለንባብ ያበቃም ሲኾን፣ የመን በነበረበት ወቅት በርካታ መከራዎች እና ፈተናዎች ቢገጥሙትም ለችግርና ለፈተና ሳይበገር በየመን፣ በሳዑዲ ዐረቢያ እና በሌሎችም የዐረብ ሀገራት እንግልት እና ስቃ ለደረሰባቸው፣ ለተጎሳቆሉና በዓረብ ሀገራት የጸጥታ ሰራተኞች በደል ይፈጸምባቸው ለነበሩ ብዙኃን የእናት ኢትዮጵያ ልጆች ዓለም አቀፍ ድምጽ ኾኖ አገልግሏል፡፡

ዳንኤል ይኽንን የስደት ሰቆቃውን አስመልክቶ ‹‹ሲዋን›› በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ የሚከተለውን ይላል፡-

‹‹…በሕይወት ለመቆየት የሰው ልጆች ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች ዋና ዋናዎቹ ተብሎ የተጠየቀ ሁሉ አስቀድሞ የሚመልሰው የታወቁትን መሰረታዊ ጉዳዮችን እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ምግብ እና ውሃ በሌለበት እንደ እኔ ለቀናት ፍዳውን ያየ፤ አበሳን የቆጠረ ደግሞ ከተስፋ በላይ ምንም የለም ቢል አይገርምም። በአንጻሩ በመንፈሳዊ አስተምህሮትስ ቢሆን ሰው በምግብ ብቻ እንደማይኖር ተመልከቶስ የለ። የኔው ግን የተለየ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ሊያስበው ይችላል ይሞክረው ብዬ ግን ሙግት አልይዝም፡፡ ምክንያቱም እኔ በዚያ መከራ አልፍ ዘንድ የግድ ነበር እና ነው በዚያ ሁኔታ ማለፌ እና መፈተኔ፡፡

‹‹ተስፋ የህይወት ስንቅ ነው›› ያለው ማን ነበር?… ዘነጋሁት። ግን አባባሉን ልዋሰው አዎ ተስፋ የህይወት ስንቅነቱ ግን የሚያከትመው ከውስጥዎ ቆርጠው የጣሉት ዕለት ብቻ ነው። እነሆም በህይወት ነገን ለማየት ስለነገው ለመኖር በተስፋ መጉዋዝ መጪውን ብሩህ ያደርገዋል፡፡

የዘመናት ህልሙን እውን ለማድረግ የበረሃ ላይ ነፍሳትን ምሳሌ በማድረግ ያቺን ቁንጽል አጋጣሚ እንደ ሕይወት መመሪያው በመውሰድ ለትልቅ ውጤት የበቃውን የአሜሪካውያንን ኩራት አብርሃም ሊንከልንን ማሰብ በቂ ነው ሰለተስፋ ዋጋ ለመረዳት እላለሁ እኔ በበኩሌ።

ስለዚህ ህይወትን ደግሞ አንድ ቦታ ብቻ ከተንጣለለው ውቅያኖስ መሃል መልህቅን ጥሎ በጨረቃ ዳቦ ጣይልኝ ስሌት አይኖሩዋትም፡፡ ምክንያቱም ባሉበት ረግጠው በተስፋ የሚቆዩባት አይደለችም እና ነው ህይወት። እኔም ከህይወት መመሪያ የምጋራ ህይወትን የተቁዋደስኩ አንዱ አካል እንደ መሆኔ ህይወት ብታዝም ባታዝም ለጊዜውም ቢሆን ጉልበተኞች በሚያዙባት አለም ያለሁ የጉልበተኞች ጉልበት መወጪያ፤ የፍርደ-ገምድሎች ሰለባ ሆንኩኝ።

ሃገሬን እየወደድኩኝ ተገድጄ ግን ደግሞ እስራትን መጋዝን፤ ያለ አግባብ መቁሰል፤ መድማትን ለአመታት ኖሬበት የአበሳው ገፈት ሲያንገሽግሽኝ ካሳለፍኩዋቸው የባሰ ወደ የሚመረው ስደት ለመግባት ተገደድኩኝ። ሰው እኮ የማይናገርን ያናግራል ራሱ በተረተው ተረት “ኑሮ ካሉት…” በሚለው ተረቱ ውስጥ “ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል “አለች ኮካ ኮላ” በማለት ከስቃይም በላይ ስቃይ ያለበት ህይወት… ህይወት ተብሎ በግድ ያለ ውድ እንደሚመረጥ ያመላክታል ሰው፡፡

ብታምኑም ባታምኑም እኔ ከሞት ጋር ተያይቻለሁ። ሞትን ተመልክቼዋለሁ፡፡ በርግጠኝነት ነው የምነግራችሁ ሞትን ፊትለፊት ተጋፍጨዋለሁ ግን ሞትን በይፋ አሸነፍኩት። አባባሌ ማንንም ግር ለማሰኘት ውይንም ደግሞ የሌለኝን መለኮታዊ ሃይል እንዳለኝ የማወራ ያልሆነውን የምቀባጥር ሃሳይ መሲህ እንዳልመስላችሁ። እራሴንም የመለኮታዊ ሃይልን የታደልሁ አድርጌ ያቀረብኩ አድርጋችሁም አትመልከቱኝ ያለሁት ከህሊናዬ ጋር ነው የምጽፈው የደረሰብኝን ነው።…››

ዳንኤል ገዛኸኝ በስደት ከኖረበት ሃገረ የመን ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ በዚያው በነበረው ቆይታ ‹‹ማዕዶት›› የተሰኘ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን (ዩ ቲ ዪብ) በማቋቋም የሃገሩን፣ የወገኖቹን አንገብጋቢና ወቅታዊ ጉዳዮች ለአንባቢዎቹና ለአድማጮቹ ያቀርብ ነበር።

በአሜሪካ ለአመታት የቆየው ከሰው ሰራሹም አገዛዝ አፈና እና ከተፈጥሮው ሕመምም ጋር ለአመታት በአይበገሬነት የታገለው ምግባረ ሰናይ ብርቱው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ፣ ከኩላሊት ሕመም ፈተናው ጋር ሆኖ ማዕዶት ሚዲያን እና በአሜሪካ ዳኮታ የኢትዮ ሱፎልስ ማህበረሰብ ቅርርብና ትብብር እንዲጎለብትና የላቁ ኢትዮጵያውያን ጎላ ብለው እንዲታዩ ብሎም ባለበት ግዛት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመራቂ ተማሪዎች ከብረው እንዲነሱ ሲያደርጋቸው የነበሩ ጉልህ የፊታውራሪነት ምግባረ ሰናይ ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀስ ሲኾን፣ ከዚህም ባሻገር በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚወለዱ ልጆችን አማርኛ እና ግዕዝ ያስተምር እና የኢትዮጵያን ባህልም እንዲያውቁ ሲለፋና በችግር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እርዳታ አንዲያገኙ ያስተባብር ነበር።

መከራ የተከተበለት ይመስል ሕይወቱ በወጀብ የተሞላና የዕረፍት ትንፋሽ ሳያገኝ የኖረው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ወንድሙ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኖርበት ሳውዝ ዳኮታ በአቬራ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ እስከወዲያኛው ከዚህ ዓለም ድካም በሞት ተለይቷል። የዚህ የነፃው ፕሬስ ባልደረባ እና ፋና ወጊ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ የቀብር ሥርዓትም ነሐሴ 9 ቀን  2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቤቴል ወይራ ሠፈር በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘመዶቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹ እና ወዳጆቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡ ***

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...