ዳግም የተቀሰቀሰው የቻይና እና የታይዋን ፍጥጫ

Date:

ከሰሞኑን የታይዋን ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሌይ በአሜሪካ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኒውዮርክ እና ሳንፍራንሲስኮ ያደረጉት ጉብኝት ታዲያ ቻይናን አስቆጥቷል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የዊሊያም ሌይ ጉብኝት የሀገሪቱን ሉአላዊነት የተዳፈረ ነው ብሏል። ሌይ ታይፒን ከቤጂንግ የመገንጠል እሳቤን የሚያቀነቅኑ እና “ሁሌም ችግር ፈጣሪ” ሲልም ገልጿቸዋል። በታይዋን በቀጣይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋነኛው እጩ ተፎካካሪ ዊሊያም ሌይ በቻይና ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ትችት ይሰነዘርባቸዋል። በምርጫ ቅስቀሳቸውም ለታይዋን ነጻነት እንደሚሰሩ ሲናገሩ መደመጣቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ፓራጓይ ሲያመሩ ሁለት ጊዜ በአሜሪካ የማረፋቸውን ጉዳይ በቀላሉ አንመለከተውም ያለው መግለጫው፥ ሌይ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ምን እንደተነጋገሩ እየተከታተልን ነው ብሏል። ቻይና እንደ አንድ ሉአላዊ ግዛቷ የምትመለከታት ታይዋን ከቅርብ አመታት ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርታለች። የዛሬው ጥንቅራችንም ቻይና በ2027 ታይዋንን ለመውረር ጥብቅ ምሥጢራዊ ዕቅድ አስልታ እደረገች ያለውን ዘመናዊ የጦር ሰራዊት ግንባታን ይመለከታል፡፡

ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ፣ በ2022 በተካሔደው ሃያኛው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በአፋጣኝ ሕዝባዊ ነጻ አውጪው ጦራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የጦር ኃይል ኾኖ እንዲገኝ ሥራዎችን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ዋናው ግባችን ዘመናዊና ተመራጭ የጦር ኃይል ያላት ሶሻሊስት ሀገር የመገንባት ስትራቴጂያዊ ተልዕኮአችንን ለማሳካት ፓርቲያችን የሚሰጠውን ተልዕኮ ፈጻሚ የኾነ፣ ጠንካራ የፓርቲ ዲሲፕሊን ኖሮት ለሚሰጠው ግዳጅ ሁልጊዜም ዝግጁ የኾነን ሰራዊት መገንባት ነው›› ሲሉ መመሪያ መሳይ ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ በዚሁ ኮንግረስ ላይ ‹‹በተጠናከርን ቁጥር ጥንካሬያችንን የሚፈትኑ መሰናክሎችና የተለያዩ ውጫዊ ጫናዎች ይገጥሙናል፡፡ እነዚህ የውጪ ኃይሎች ጫናዎች አደገኛ ቢኾኑም፣ ቻይና ይኽንን ፈተና በማለፍ ነው ጥንካሬዋን የምታረጋግጠው፡፡ እናም የሚያጋጥመንን ማዕበል እና ወጀብ ለማለፍ መዘጋጀት አለብን›› ሲሉ ግዙፉ የሕዝባዊት ቻይና ጦር በመጪው ጊዜያት ለሚጠብቀው ግዳጅ ዝግጁ እንዲኾን መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በርግጥም የቻይና ባሕር ኃይል በጦር መርከቦች እንዲሁም በአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ብዛት በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው ደረጃን ለመያዝ መብቃቱ በስፋት ይነገራል፡፡ ለዚህም ይመሥላል ‹‹ሰራዊቱ የሚሰጠውን ተልእኮ ለመወጣትና በውጪ ኃይሎች የሚሰነዘር ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት፣ ብሎም ታይዋንን ነጻ ለማውጣት የሚንቀሰቀሱ ተገንጣይ ኃይሎች ሙከራን ለመግታት ብሎም ለሀገራችን ሉዓላዊነት የሕይወት መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የኾነ አስተማማኝ አቅም ያለው የጦር ኃይልም ገንብተናል›› የሚለውን የቻይና ባለሥልጣናት የሚሰጡትን መግለጫ ተከትሎ በርካታ ወገኖች ‹‹ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት ወደ ጦርነት አልገባንም ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ፍጹም አውዳሚ ጦርነት እያመራን ነው›› ሲሉ ፍርሐታቸውን በመግለጽ ላይ የሚገኙት፡፡

እንደ ብዙዎች ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተሉ ወገኖች አስተያየት ታዲያ ይኽ የአያሌዎች የፍርሐት ሥጋት ከእውነት ያልራቀ፣ ይልቁንም ታይዋን በምትገኝበት የደቡብ ቻይና ባሕረ ሰላጤ ያለው ሁኔታ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ ለዚህም ይመሥላል የሕዝባዊት ቻይና ጦር ኃይል በጥድፊያ ላይ የሚገኘው፡፡ ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግም ሀገራቸው የሚጠብቃትን አደገኛ ማዕበል ለመቋቋም እና በአሸናፊነት ለመወጣት የጦር ኃይላቸውን ግዳጁን በወጉ መወጣት በሚችልበት ጉዳይ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡

የዚህ ግዳጅ ዓቢይ ተልዕኮ ደግሞ፣ ሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ የተመሠረተችበት አንድ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል በሚከበርበት 2027 ታይዋንን በመውረር ከቻይና ጋር እንድትዋሐድ የማድረግ ግዳጅ ነው፡፡ ለዚህም እየተዘጋጀ ስለመኾኑ አፈትላኪ መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡

በስፋት እንደሚታወቀው ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም፣ ቻይና ግን እንደ አንድ አፈንጋጭ ግዛቷ ከመመልከት የተሻገረ እስካሁን በታይዋን ላይ ያላትን ዐቋም ለድርድር አቅርባው አታውቅም፡፡ እ.አ.አ በ1895 በሺሞኖስኪ ስምምነት መሠረት በጃፓን ቅኝ አገዛዝ ስር ከቆየች በኋላ፣ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጃፓን ተሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ‹‹ራስ ገዝ እንጂ ዳግም የቻይና አካል አልሆንም›› በማለት ከቻይና ኮሚኒስት መንግሥት ጋር የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እስከመግባት ደርሳም ነበር፡፡ ኾኖም የቻይና አቋም ዝንፍ የማይል መኾኑን ተከትሎ አሜሪካ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እያጠናከረች መሔዷ፣ ነገሩ ሔዶ ሔዶ የታይዋንን ሉአላዊነት ማወጅ እና የቀጠናውን ቁጥጥር አሳልፎ ለዋሽንግተን መስጠት መሆኑን በመረዳት ቻይና ነገሩን በሚቀጥሉት ዓመታት አንዳች እልባት ለመሥጠት ያለመች ይመሥላል፡፡

በቅርብ ጊዜ እንኳን ቤጂንግ ወደ ታይዋን አየር ክልል ተዋጊ ጄቶቿን በመላክ የታይዋን ዕጣ ፈንታ በእርሷ መዳፍ ላይ መኾኑን አንዳች ወታደራዊ መልዕክት ለማስተላለፍ ሞክራለች፡፡ በርግጥም ለእነዚህ ጄቶች ከታይዋን መንግሥት የተሰጠ የአፀፋ ምላሽ ባይኖርም አሜሪካ የቻይናን ልዕለ ኃያልነት ለመገዳደር ወሣኝ ካርድ አድርጋ ታይዋንን የመመልከቷን እውነታ በተለያየ መንገድ ከማሳየት ግን አልተቆጠበችም፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ከወራት በፊት  የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ማስጠንቀቂያ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ታይዋንን ጎብኝተው መመለሳቸው ነው፡፡ 

ከቀናት በፊትም እንዲሁ የታይዋን ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሌይ ወደ አሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይና ያሰማችው ቁጣ፣ ነገሩ እንዲህ ቀላል ተደርጎ ላለመታየቱ የቅርብ  ማስረጃ ነው፡፡ በርግጥም ታይዋን፣ ከዋሽንግተን በቢሊየን ዶላር የምትሸምተው የጦር መሳሪያ እያደገ መሄድና የቤጂንግ ጦር ልምምድ የታይዋን ሰርጥን ውጥረት እያባባሰው መሔድ ነገሩ የሚያሳስባቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ ታይዋን ከቤጂንግ ጋር ያላት ወታደራዊ ንጽጽር ከተስተዋለ፣ የታይዋን ጉዳይ ልክ እንደ ዘሌንስኪ የባይደንን ውሃ የበላውን ‹‹አይዞህ አለሁልህ›› ሽንገላ ተማምኖ ላትን ውጭ ከማሳደር የዘለለ ረብ እንደማይኖረው የምድር ጦር፣ የባሕር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ ስትራቴጂክ ሚሳኤሎች፣ ስትራጂክ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች እና ሌሎች ወታደራዊ ኃይሎችን ዝርዝር ዳታ በእማኝነት አስደግፈው የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡

ይኽም ኾኖ ሌሎች ተንታኞች ግን የቻይና መጠነ ሰፊ ዘመናዊ ወታደራዊ መሰናዶ እንዲህ ተብሎ ‹‹የተለየ ግብ ለማሳካት የተሰጠ ግዳጅ የለም፣ ሁሉም ነገር ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ፣ ዘመናዊ አቅም ያለው ጦር ኃይል መገንባትና ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ የማድረግ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው›› በሚለው ሐሳብ የሚስማሙ ናቸው፡፡

ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ በበኩላቸው ‹‹ሰራዊቱ በአፋጣኝ ዘመናዊና ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይኾን ማሸነፍ የሚችል ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኃይል መኾን አለበት›› ይላሉ፡፡ ሺ የሀገራቸው መንግሥትና ሕዝብ ለዚህ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነትም በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የግሎባል ኮንፍሊክት ኤንድ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የኾኑት፣ ፕሮፌሰር ታሚንግ ቻንግ፣ ‹‹ቻይና የጦር ኃይሏን ለማዘመንና ግዳጁን በብቃት መወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ እየሰራች ያለችው፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ነው፡፡ ይኽ እንቅስቃሴዋ በዋናነት ከአሜሪካና ሸሪኮቿ በተለያዩ መንገዶች የሚደርስባትን ትንኮሳና ጫና ለመቋቋም የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር ነው፡፡ ይኽንን ዕቅዷን ለማሳካት ደግሞ በሚሳኤል ቴክኖሎጂ፣ በኒውክለር ጦር መሣርያ ክምችት፣ በሕዋ ሳይንስ እና በሳተላይት መረጃ አሰባሰብ ዘርፍ እያካሔደችው ያለው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኃይል ሚዛን ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወደ መኾን እንድትሸጋገር አድርጓታል›› ብለዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...