ፈላስፋው እና አሰላሳዩ ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጀፈርሰን የፕሬስን አስፈላጊነት አስመልክቶ ከተናገራቸው ንግግሮች መሃል ታሪክ የሚከተለውን ኃይለ ቃል ከትቦልን አልፏል፡- ‹‹የሰው ልጅን አእምሮ ለማብራት ብሎም ምክንያታዊ፣ ሞራላዊ እና ማኅበራዊ ፍጡሩነቱን ለማጎልበት ምርጡ መሣሪያ ፕሬስ ነው››፡፡
በሀገራችን፣ ዘመናዊ ሥርዓተ መንግሥት እየተገነባ ከመጣባቸው ዓመታት አንስቶም፣ ሕብረተሰባዊ ሕይወት እና አኗኗራችን ተለውጦ ዓለም የደረሰበት የማሰብም ኾነ ሐሳብን (ፈጠራን) የማጎልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ መጻሕፍት፣ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ሲታተሙ ኖረዋል፡፡ የሺህ ዓመታት የፊደል እና የጽሑፍ ታሪክ ‹‹አለኝ›› ብሎ ለሚኩራራ ሀገር እና ሕዝብ እነዚህ የምናብ ልሕቀትን አስፍተው ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የሕትመት ውጤቶች ቁጥር ‹‹ምን ያህል የተራመዱ ነበሩ?›› የሚለው ጥያቄ ግን ደረት የሚያስነፋ እና ልብን የሚያኩራራ ኾኖ አይገኝም፡፡
መጽሔታችን ግዮንም ኾነች ከእርሷ በፊት ነጻ ፕሬስን የተቀላቀሉ አያሌ ጋዜጣ እና መጽሔቶች ዘርፉን የተቀላቀሉበት ዓላማም ቢጤን፣ ይኽንን ማኅበረሰባዊ ግዴታ ከመወጣት የዘለለ ሊኾን አይችልም፡፡ ኾኖም በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ይኽንን ለሀገርም ኾነ ለሕብረተሰብ መቀጠል ወሣኝ የኾነ ዘርፍ በጽናት ለማስቀጠል አያሌ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማነቆዎች ፈተና ሲኾኑ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ላይ ከ80 – 90 ሚሊዮን በላይ የተማረ ዜጋ እንዳላት የሚነገርላት ሀገራችን ያሏት የጋዜጣና መጽሔቶች ቁጥር ‹‹ምንም›› ወደሚባልበት ደረጃ ደርሷል ቢባል ማጋነን አይኾንም፡፡ ይኽ የሚያሸማቅቅና የሚያሳፍር ገመናችን ነው፡፡
መጽሔታችን ‹‹ግዮን›› ከየካቲት 2010 ዓ.ም አንስቶ በበርካታ ዘርፎች ፀሐፍት እና አሰላሳዮችን አሰባስባ የማኅበረሰባችንን ሁለንተናዊ ንቃት ለማዳበር የሚጠብቅባትን እያዋጣች፣ በበርካታ ጫናና እና ተግዳሮቶች ውስጥ አልፋ እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም ተጉዛ ነበር፡፡ ኾኖም ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሽ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የገጠማት አፈና፣ ያለፈውን አንድ ዓመት ከውድ አንባቢዎቿም ኾነ ከተነሳለችለት ዓላማዋ ተናጥባ ለመቆየት የሚያስገድድ ኾኗል፡፡ የሳሳውን የንባብ ፍቅርም ኾነ የአንባቢ ቁጥር በማሳደግ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የራሷን በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሕግን እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብራ ትንቀሳቀስ የነበረችው ግዮን፣ ባለፉት ዐሥራ ሁለት ወራት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበረው ዕትሟ እንዲለቀቅም ኾነ፣ ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ በተደጋጋሚ ታቀርባቸው ነበሩ ጥያቄዎች በቀላሉ መልስ ሊያገኙ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ መጽሔታችን ላለፈው አንድ ዓመት የገጠሟት ጫናዎች እና ፈተናዎች ጨርሶ ታሪክ ወደመኾን በተቃረበው የግል ፕሬሱ ላይ እስከወዲያኛው ተስፋ ለመቁረጥ የሚያስገድዱ ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡
ኾኖም ሀገርም ኾነ ሕብረተሰብ እንዲህ በቀላል ተስፋ ተቆርጦበት ‹‹ዞር›› የሚባልበት ባለመኾኑ ከአንድ ዓመት ትግል በኋላ ወደ እናንተ ወደ ተከበራችሁ አንባቢዎቿ ለመመለስ ችላለች፡፡ ‹‹የሰው ልጅን አእምሮ ለማብራት ብሎም ምክንያታዊ፣ ሞራላዊ እና ማኅበራዊ ፍጡሩነቱን ለማጎልበት ምርጡ መሣሪያ ፕሬስ ነው›› የሚለውን የታላቁን ሰው ቶማስ ጀፈርሰን ዕሣቤ በማንገብም ‹‹እጃችሁ ከምን›› ለሚለን አንባቢ ሽንቁር የበዛበት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችንን በጥልቀት የሚዳስሱ ሥራዎችን ይዘን እንደተለመደው ተከስተናል ለማለት እንወዳለን፡፡
መጽሔታችን፣ በሀገራችን ካለው የወረቀትም ኾነ የሕትመት ዋጋ ንረት ጋር እየታገለች ወደ ውድ አንባቢዎቿ ለመድረስ የያዘችውን ብርቱ ጥረት ግን ልዩ ልዩ ድርጅቶችም ኾኑ ተቋማት በማስታወቂያ እና ስፖንሰር እንዲደግፏት በእጅጉ ትሻለች፡፡ በርግጥም ሀገራችንም ኾነ ሕዝባችን ከምንም በላይ ሙያ እና ሥነ ምግባርን ወዳከበረ የሐሳብ ሜዳ ከመመለስ ውጪ ምርጫ አላቸው ብለን አናምንም፡፡ ቀለም ነጥፎ አፈሙዝ ያማዘዙት የሀገራችን መልከ ብዙ ችግሮችም ቢኾኑ ግዮንን ጨምሮ ዘመኑ ወደፈቀዳቸው ሥርዓታዊ እና ሙያዊ መገናኛ ብዙኃን መመለስ ይጠበቅባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ መጽሔታችንም በየዐሥራ አምስት ቀኑ ከእናንተ ከውድ አንባቢዎቿ ጋር ይኽንን በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል ኃላፊነቷን ለመወጣት የዐቅሟን ሚና እንደምትጫወት ከወዲሁ ቃል እንገባለን፡፡
ጅረትን ልብ ይሏል ፤ ግዮን አሁንም እየፈሰሰች ትቀጥላለች!
ግዮን ቅጽ 6 ቁጥር 215 መስከረም 2017 ዓ.ም
