‹‹ጉዳዩ በጎችን የመበተን ጉዳይ በመኾኑ ሰማዕትነትን ይጠይቃል››

Date:

መምህር ንጉሤ ግርማ

(የወልዳ ዳንዲ አቦቲ ሰብሳቢ)

ያለንበት ወቅት አንጋፋዋ እና ታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕልውናዋን የሚፈታተን ዐዲስ መልክ ያለው አደጋን እያስተናገደች የሚገኝበት ነው፡፡ ይኽንን ተከትሎም ከሃይማኖቱ አባቶች አንስቶ መላው ምዕመን ያጋጠመው ችግር የቤተክርስቲያኒቱን ሕላዌ እንዳያጠፋ በጾም እና ጸሎት እንዲተጉ ጥሪ እየተላለፈ ነው፡፡ መንግሥትም የቤተክርስቲያንን ሕጋዊ ሰውነት እንዲያከብር እና እንዲያስከብርም የተለያዩ የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማኅበራት እየጠየቁ ነው፡፡ ከእነዚህ በቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ዕውቅና ካላቸው መንፈሳዊ ማኅበራት መካከል ደግሞ ትኩረቱን በኦሮሚያ ክልል ባለው የአገልግሎት ችግር ላይ አድርጎ የተቋቋመው ወልዳ ዳንዲ አቦቲ (ማኅበረ ፍኖተ አበው) ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ለመኾኑ ማኅበሩ በክልሉ ‹‹አሉ›› ብሎ የተቋቋመባቸው ችግሮች ምን ምን ናቸው? ችግሮቹንስ ለመፍታት የተከተለው መንገድ እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቋንቋ አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ ቤተክህነት ከማቋቋም ‹‹ጵጵስና እስከመሾም›› የደረሰው አካሔድ እንዴት ይታያል? በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ የሚነሳው ጥያቄስ ምን ያህል እውነትነት ያለው ነው? ስንል ከማኅበሩ ሰብሳቢ መምህር ንጉሤ ግርማ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!    

ግዮን፡- ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?

መምህር ንጉሤ፡- መምህር ንጉሤ ግርማ እባላሁ፡፡ የወልዳ ዳንዲ አቦቲ ሰብሳቢ ነኝ፡፡

ግዮን፡- ወልዳ ዳንዲ አቦቲ መቼ ተመሠረተ?

መምህር ንጉሤ፡- የተመሠረተው በ2012 ዓ.ም ነው፡፡ የተመሠረተበት ምክንያት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት ክፍተት ለመሙላት ነው፡፡ በክልሉ ስላለው የአገልግሎት ጥናት ተጠንቶ የመፍትሔ ሐሳቡም ቀርቦ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡

ግዮን፡- አሁን ያለውን ችግር ማኅበራችሁ እንዴት ይመለከተዋል?

መምህር ንጉሤ፡- አሁን ያለው ችግር መታየት ያለበት የእምነት ጉዳይ ስለኾነ በመንፈሳዊ ዓይን ነው፡፡ በጥናቱ ወቅት ረጅም ጊዜ የወሰደብንም የችግሩን ተጨባጭነት ለይተን፣ መፍትሔው ላይ ፍኖተ ካርታ ስናዘጋጅ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኦሮሚያ በርካታ ሀገረ ስብከት የሚገኝበትና ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥበት ክልል ነው፡፡ እውነታውን መሠረት አድርጎ ችገሩን በደምብ ማግኘት ስለሚገባ ጥናታችን ረጅም ጊዜ ወስዶብናል፡፡ በዚህም በክልሉ በየቦታው ያለው ችግር ተመሳሳይ መፍትሔ የሚፈታው እንዳልኾነ አረጋግጠናል፡፡ የችግሩ መልክ ቢመሳሰል እንኳን ጥልቀቱ ይለያያል፡፡ ይህ በመኾኑም ለእያንዳንዱ አካባቢ የተለያየ ስትራቴጂ ያስፈልገው ነበር፡፡ በዚያ ደረጃ ችግሮቹን በመተንተን ለሦስት ዞን ከፍለን ስትራቴጂዎችን አስቀምጠን ወደሥራ ገብተናል፡፡ ይህ ሥራ የሚሠራው በመዋቀር በመኾኑ ወልዳ ዳንዲ አቦቲ በመዋቀሩ የሚሠራውን ሥራ ያከናውናል፡፡ መዋቅሩ ያቀደውን ወልደ ዲንዲ አቦቲ ያከናውናል፡፡ እያንዳንዱ ፍኖተ ካርታ በመዋቅሩ ከጸደቀ በኋላ ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ወደ ቋሚ ሲኖዶሱ በመምራት ቋሚ ሲኖዶሱ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መርቶት ከታየ በኋላ አሁን እየሠራንበት ነው፡፡

ሥራው የሚከናወነው በታችኛው መዋቅር ስለኾነ ሀገረ ስብከቶች ፍኖተ ካርታው ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ለሰባት ሀገረ ስብከቶች ልከን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይም ለመሄድ ሞክረናል፡፡ እነዚህ ሀገረ ስብከቶች ፍኖተ ካርታውን በማኔጅመንታቸው ገምግመው አፅድቅው መልሰውልናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከቶች ተጠቃሶች ናቸው፡፡ እንደ ሀገረ ስብከቶቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ “በሚቀጥሉትን 25 ዓመታት በሁሉም ሀገረ ስብከቶች መድረስ አለበት” የሚል አካሄድ ስላለው ከሌላው የሰው ኃይልና አቋም አንፃር “ይደርሳል ወይስ አይደርስም” የሚለውን እንዲያረጋግጡ አድርገናል፡፡

ግዮን፡- ፍኖተ ካርታችሁ የ25 ዓመት እቅድ ነው?

መምህር ንጉሤ፡- አዎ ፍኖተ ካርታችን የ25 ዓመት እቅድ ነው፡፡ ለዚህ ምላሽ የሚኾን በሦስት ፕሮጀክቶች የተከፈለ ሙሉ ዶክመንት አለ፡፡ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት ትምህርት እና ሥልጠና የተከፈለ ነው፡፡ ስለዚህ የተቋም ግንባታዎች አሉ፡፡ ግንባታው እስከ ትምህርትና ምርምር ግንባታ ድረስ የሚሄድ ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ጳጳሳት ባሉበት ቀርቦ የተገመገመ ጥልቀት ያለው ፍኖተ ካርታ ነው፡፡

ግዮን፡- ይህን ሥራ ስታከናውኑ አንድ ወቅት የአባ ሳዊሮስ ሀገረ ስብከት ከልክሏችሁ እንደነበር ይነገራል፡፡ ለምን ነበር?

መምህር ንጉሤ፡- ወልዳ ዳንዲ አቦቲ ከውስጥና ከውጪ ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተክርቲያን ችግር ሲጠና ብዙ ፈተናዎች አሉት፡፡ ቢዝነስም ኾነ ፖለቲካ መሥራት አይቻልም፡፡ ችግሮቹ በቀላል የሚፈቱ ሳይኾኑ የሚደራረቡ ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለው ችግር በፖለቲካው ዓለም የሚታየው ነው፡፡ የኾነው ኾኖ በአቡነ ሳዊሮስ ሀገረ ስብከትም ጥናቱ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ወደዚያ ለመሄድ ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ በእርግጥ ከዚህ ሥራ ጎን ለጎን ሌሎች ሥራዎችም ተጀምረዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳሱ ናቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አይሠራም ካሉ ምንም ዐይነት ነገር ማከናወን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ወሊሶ አካባቢ የተለያዩ ጉባኤያትና ሥልጠናዎችን ለማከናወን እያጠያየቅን ነበር፡፡ በፕሮጀክቱ ውስጥ ሰላምና አንድነት የሚባል አለ፡፡ ይህ ፕሮጀክት ቤተክርስቲያኒቱ በሠላምና አንድነት ዙሪያ የምትሠራበትን ሂደት የሚያከናውን በጀት ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ ይኼ ከሚሠራባቸው ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ደግሞ አንዱ ወሊሶ ነበር፡፡ ነገር ግን መሥራት አልተቻለም፡፡

ግዮን፡- ለምንድን ነው እንዳትሠሩ የተከለከላችሁት?

መምህር ንጉሤ፡- የተከለከልነው በመጀመሪያ ደረጃ ውክልና ላለመስጠት ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በሀገረ ስብከቱ ቅስቀሳ እያደረግን ነበር፡፡ በቅርቡ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም በዚህ ዙሪያ እየመከርን ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት ላይ እያለን ይህ ችግር ተፈጠረ፡፡ እኛ ግን አብረን ለመሥራት በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ሸዋ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ሞክረን ነበር፡፡ ይኼ የሚሠራው በየሀገረ ስብከቱ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት አምነውበት ሥሩ ስላሉን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ መሥራት አይቻልም፡፡

ግዮን፡- እነዚህን ፕሮጀክቶች ስትሠሩ የገቢ ምንጫችሁ ምንድነው?

መምህር ንጉሤ፡- ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል በመጀመሪያ 6000 መምህራን መሠልጠን አለባቸው የሚል እቅድ አለን፡፡ ይህን ዕቅድ 30 በመቶው በጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃ የሚሠራ ነው፡፡ ልክ እንደ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ቤተክህነትም ከሥሩ ላሉት በጀት ይሰጣል የሚል እምነት አለን፡፡ ቀሪውን ሰባ በመቶ ደግሞ ሀገረ ስብከቶቹ ይችላሉ፡፡ የወልዳ ዳንዲ አቦቲ ሚና ሁለቱን ማገናኘት ነው፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ፕላት ፎርሙን ከማመቻቸት ተግባር ቀጥሎ ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጥያቄውን ከተቀበለ ከእርሱ ጋር ሀብት ማፈላለግ ላይ እንሠራለን፡፡ ሀገረ ስብከቱ ላይ ያሉ የእኛ ጽሕፈት ቤቶች ለሚሠራው 30 በመቶ ሁኔታዎች ያመቻቻል፡፡ በማዕከላዊነት ደረጃ ወደ 196 ሠልጣኞች ለማሠልጠን ሀገረ ስብከቱ እንዲሸፍን ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ ይህንንም በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ተግባራዊ እያደረግን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን የሚባለው አካል የመዋቅሩን ሥራ በፋይናንስ ማገዝ አለበት፡፡ አሥራት በኩራት ከሚሰጠው በተጨማሪ ለዚህ ሥራ እርዳታ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህን በተመለከተ ለምሳሌ ሻሸመኔ ላይ ካርድ ተዘጋጅቶ ለእያንዳንዱን ምዕመን እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡ የሚፈለገው ብር ወደ 115 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በየዓመቱ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ በእንደዚህ ዐይነት መልኩ ከማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን በመሰብሰብ የቤተክርስቲያኒቱን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም እየተሠራ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ በማኅበራት በኩል ለመሥራት ነው የታሰበው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኤንጂኦ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶችን እንደሚወስደው ሁሉ በተመሳሳይ በቤተክርስቲያነቱ ዙሪያ እንዲሠሩ ይፈለጋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወረዳ የሚንቀሳቀስ ማኅበር “የዚያን ወረዳ መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል” በሚል ለባለ ድርሻ አካላት ፕላት ፎርም አሳትመናል፡፡ ሌላው የምንሠራቸው ሥራዎች ደግሞ ከውጪ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሠሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሰላምና አንድነቱን ሥራ ከመንግሥታትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ነው የምንሠራው፡፡ አሁን እየሠራነው ያለ ሥራም አለ፡፡ እርሱም የማኅበረሰቡን እሴት ማበልፀግ ነው፡፡ በቀጣይ የማኅበረሰብ ሰላምና የሕዝቡን አንድነት ማረጋገጥ በሚል እየተሠራ ያለ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ መንግሥታዊም ይሁን መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን እንደ አንድ የገቢ ምንጭ እንጠቀማቸዋለን፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ በማኅበራችን ውስጥ ያለን አባላት ለአንዳንድ ነገር የሚኾን አስተዋፅኦ እናደርጋለን፡፡

እነዚህ ሲሰበሰቡ የትምህርት እና የምርምር ተቋም፣ ሌሎች መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የሕግ ማዕቀፍ አላቸው ፤ የፖሊሲ፣ የደንቦች እና የውሳኔ ችግር የለም፡፡ ሥራውን ለመሥራት የሰው ኃይል እጥረትም የለም፡፡ ወንጌልን በየቤተክርስቲያኑ ለማድረስ ይቸግር ይኾናል እንጂ መፍትሔውን ለመሥራት የሰው ኃይል ችግር የለም፡፡ አሁን ያለው የሰው ኃይል መምህራን ማሠልጠን ይችላል፡፡ ጉባኤ ማዘጋጀት ይችላል፤ አሁን የያዝናቸውን ፕሮጀክቶንም መሥራት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ማኅበሩ በኦሮሚያ ውስጥ ወደ 20ሺህ የሚጠጋ የሰው ኃይል አለው፡፡ ስለዚህ ሥራ ሠርቶ ተጨማሪ አገልጋዮችን ማፍራት ይችላል፡፡ ምዕመኑንም መጠበቅ ይቻላል፡፡ በመኾኑም ሥራውን ለማከናወን የሰው ኃይል፣ የእውቀት፣ የሀብት ችግር የለበትም፡፡

ግዮን፡- ከሁለት ዓመት በፊት ‹‹የኦሮሚያ ቤተክህነት›› ለማቋቋም የተንቀሳቀሱ አካላት ነበሩ፡፡ ተቺዎቻቸው እነዚህን አካላት ጥያቄዎቻቸውን የሥልጣን እንጂ የቤተክርስቲያን አይደለም ይላሉ፡፡ እናንተ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት የሄዳችሁበት አቅጣጫ ምን የተለየ መልክ አለው?

መምህር ንጉሤ፡- በመሠረቱ እኛ ችግሮችን የምናይበት መንገድ ሦስት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከሕግ አንፃር ነው፡፡ አንድ ችግር ‹‹ችግር›› ተብሎ ሲነሳ “የሕግ ማዕቀፍ አለው የለውም” የሚለውን እንለያለን፡፡ ለምሳሌ ቋንቋ እንደችግር ሲነሳ “የቋንቋ አገልግሎት ሕግ ምን ይላል?” የሚለው ላይ ማሕቀፍ እንሠራለን፡፡ የሲኖዶሱ ውሳኔ፣ ሕገ ደንቦቹ ምን ይላሉ? የሚለውን እናያለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ችግሩን ለመመለስ ግብዓቶቹ ምንድን ናቸው? የሚለውን እንመረምራለን፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሕዝብ ግንኙነት ሥራውን እንፈትሻለን፡፡ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ገንዘብ ያመጣሉ፤ ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጥያቄ በመጣ ጊዜ ይዞት የተነሳው ጥያቄ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የሚመለስ የሕግ ማሕቀፍ የሚፈልግ ነገር አለ ወይ የሚለውን አየን፡፡ ይህን ስናይ እንደ ችግር የተቀመጠው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ምላሽ የተሰጠበት ነው፡፡ በምልዓተ ጉባዔው አቅጣጫ የተቀመጠበት ነው፡፡

ለምሳሌ በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀፅ አምስት ላይ የአካባቢ ቋንቋ ከግዕዝ ጋር ከትምህርት አልፎ የሥርዓት አምልኮ እንዲኾን አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ እነዚህን ችግሮች የሕግ እውቅና ያገኙና የተመለሱ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ጥያቄው የሕግ፣ የሀብት አስተዳደርም ክፍተት የለበትም፡፡ የመሠረተ በልማት ጥያቄዎችንም ስናይ በአግባቡ የተመለሱ ናቸው፡፡ በየሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛዎች አሉ፡፡ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱም ለዘመናት የዘረጋችውን መዋቅር እነዚህን ችግሮች በተመለከተ መመለስ የሚያስችል አቅም አላት፡፡ ስለዚህ ችግሩ መሠረተ ልማቱን ማስቀጠል ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አደረሰን፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የደረስንበት የሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ስናይ ለምሳሌ አገልጋይ የለም፡፡ ነገር ግን አገልጋይ ማፍራት የሚያስችል አገልጋይ አለ፡፡ በቋንቋችን ሰባኪ ማፍራት የሚያስችሉን መምህራን አሉ፡፡ ስለዚህ ችግሩን ከመቅረፍ አንፃር የሚያስኬድ ነው፡፡ በእነዚህ ዐይነት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ሂደት ስንገመግም ያገኘነው ክፍተት የአተገባበር ኾኖ አገኘነው፡፡

ግዮን፡- ታዲያ በቅርቡ በእነ አባ ሳዊሮስ በኩል የተደረገው የቀኖና ጥሰት ምንጩ ምንድነው ይላሉ?

መምህር ንጉሤ፡- አሁን ያለው መሠረታዊ ችግር ሕግ፣ መሠረተ ልማትና የሰው ኃይል ተጠቅሞ ችግሮች መፍታት አለመቻል ነው፡፡ ስለዚህ በየሀገረ ስብከቱ ክፍተቶቹን ለመሙላት ጳጳሳት መሥራት ይችላሉ፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ እንደ አዳዲ ማርያም ያሉ ቤተክርስቲያኖች ከእነቅዱስ ላሊበላ በፊት የተሠሩ ናቸው፡፡ አዳዲ ማርያም ሁለት መቶ እና ሦስት መቶ አገልጋይ መኖር ነበረበት፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ አለ ለሚባል ችግር መልስ መስጠት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወደ አምስት መቶ እና ስድስት መቶ የሚጠጉ ኦሮምኛ ብቻ የሚችሉ ተማሪዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት እንዲህ ዐይነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ኃላፊነትን መሸሽ ትክክል አይደለም፡፡ ይኼን እኔ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ተብሎ የተደረገ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡

ግዮን፡- በተፈጠረው ኹነት አንዳንድ የሌሎች ቤተእምነቶች ተከታዮች ሕገወጡን ስብስብ የመደገፍ ነገር አለ፡፡ እንዴት ይታያል?

መምህር ንጉሤ፡- የቤተ እምነት ኃላፊዎች ‹‹በእግዚአብሔር ሥም እንለምናችኋለን›› ብለው ጣልቃ እንዳይገቡ መልዕክት አስተላፈዋል፡፡ መሬት ላይ ግን ማኅበራዊ ሚዲያውና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ስናይ የኦርቶዶክስ መከፋፈልን ለመደገፍ ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ በየሚዲያው ፓስተሮችም ይህን ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ቀድመው ነግረውናል፡፡ ትክክለኛ ነብይነታቸውንም አስመስክረውበታል፡፡ ይህ ደግሞ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በትክክል የተጠና መኾኑን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡

ግዮን፡- “ትንቢት ተናጋሪ ፓስተሮችና የተወገዘው ሲኖዶስ በጋራ ይሠሩ ነበር፡፡ ፓስተሮቹ ቀድሞም መረጃ ነበራቸው” የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ሐሳቡን ይጋራሉ?

መምህር ንጉሤ፡-እኔ ግለ ምልከታዬን  ነው የምናገረው፡፡ ያም ሆኖ ቀድሞ አብረው ቁጭ ብለው ሠርተዋል ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን ራዕዩን ያየው አካል በዚህ ዐይነት መልኩ ራዕይ ማየት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ባለራዕዩ ቀደም ሲል ጣዖት አምልኮ ብሎ ያስተማረው ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ “ይህን ጣዖት የተሸከመ ለሁለት እንደሚከፈልና እንደበሚበተን አየሁ” ሲል ሲኖዶሱን ማለቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በእኛ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ያስቀመጥናቸው “ማመቻቸት፣ መሰብሰብና ማሸነፍ” የሚሉ ሐሳቦች አሉ፡፡ ጠላት ከፍ ሲል ባየነው መንገድ በመጀመሪያ ያመቻቻል፤ በመቀጠል ወደ አንድ ጉድጓድ ያሰባስባል፤ በመጨረሻ የማሸነፊያ ቀይ ካርዱን ይመዛል፡፡ ይሄ በተጨባጭ መሬት ላይ የታየ ነገር ነው፡

እኔ እንኳን በቤተ እምነቴ ይቅርና በሥጋ ወራቴ እንኳን ለመውቀስ እና ለመተቸት የሚያስችል ሞራል የለኝም፡፡ እዚህ ሀገር ውስጥ ምንም አስተዋፅዖ ሳላደርግ አንተ አላደረግክም ብዬ መውቀስ አልችልም፡፡ እኔ ያበረከትኩትን አስተዋጽኦ አላውቅም፡፡ ምናልባትም አሉታዊም ሊኾን ይችላል አበርክቶዬ፡፡ ጉዳዩን ወደ ቤተክርስቲያን ስናመጣውም ሕጉ ቢመዘን አንድ መስፈርት እንኳን ማሟላት አንችልም፡፡ ይልቅ ንስሐ ገብተን ለፖለቲካው ዓለም ሚዛን መኾን ነበረብን፡፡ እኛ ግን ሚዛናችን ፖለቲካ እየኾነ መጣ፡፡ መኾን የነበረበት “ኦርቶዶክሳውያን ምን ይላሉ” የሚለው ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በጎችን የመበተን ጉዳይ በመኾኑ ሰማዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ እኛ የሰላም ጥሪ አድርገናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱም በውሳኔ አንድና ሦስት ላይ በይቅርታ እንዲዘጋና በሰላም እንዲጠናቀቅ ወስኗል፡፡ ይህ ካልኾነ እራሱን የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከፍሎት ይሄዳል፡፡ ጉዳዩ ሄዶ ሄዶ የኾነ ቦታ ላይ ይቆማል፡፡ ነገር ግን ማብቂያውን የሚያገኘው የኦሮሞን ማኅበረሰብ ለሁለት በመክፈል ነው፡፡

ግዮን፡- የክልሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ምዕመናኑን የተወገዘውን ሲኖዶስ እንዲቀበል ግፊት ሲያደርጉበት ይታያል፡፡ እናንተ ይኽን እንዴት ተመለከታችሁት?

መምህር ንጉሤ፡-የተለያዩ መረጃዎች ይደርሱናል፡፡ “ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው፤ እየተባልን ነው” የሚሉ የምዕመናን መልዕክቶች ይደርሱናል፡፡ ይሄ ደግሞ በግልፅ የመንግሥት እንቅስቃሴ ያለበት ነው፡፡ ሀገራችን ያልተረጋጋች ሀገር ናት፡፡ ከዚህ አንፃር እንደዚህ ዐይነት ነገሮችን ከላይ እንደተገለጸው አመቻችቶና አዘጋጅቶ ለመጠቀም የሚፈልግ ኃይል ሊኖር ይችላል፡፡ የተለያዩ ዛቻዎችንም እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ያለውን አለመረጋጋት መጠቀም የፈለገ ኃይል ሊኖር ይችላል፡፡ መንግሥትም እጁን አስገብቶ ሊኾን ይችላል፡፡ በመኾኑም ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ቢኾን የራሱን መዋቅር በትክክል አያምነውም፡፡ ለጊዜው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርና ክቡር ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እኛ የእነርሱ ትዕዛዝ ወርዶ በትክክል እየተደረገ መኾኑን አናውቅም፡፡ ነገር ግን በመዋቅሮቻችን ላይ ጫና እየተደረገና መዋቅሮች በጉልበት እየፈረሱ ስለኾነ ጉዳዩ በአፋጣኝ እንዲቆም ብለን በሚዲያም ጥሪ አድርገናል ፤ በኢሜልም ልከናል፡፡

ግዮን፡- እስካሁን ያገኛችሁት መልስ አለ?

መምህር ንጉሤ፡- እስካሁን ያገኘነው መልስ የለም፡፡ ከቀናት በፊት ግን ክቡር ጠ/ሚኒስትር ለሚኒስትሮች በሰጡት ማብራሪያ ላይ በገደምዳሜ እጃቸው እንደሌለበትና ወደፊትም እንደማይኖርበት ተናግረዋል፡፡ እኔ መናገር የምፈልገው ለኦርቶዶክሳውያን ጉዳዩን እንዲተውልን ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያን አባገዳዎች አሉ፡፡ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚፈቱ ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከሕግና ከሕግ ውጭ ያሉ ነገሮችን ማስቆም አለበት፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ እየተመራችበት ያለውና በፍትሐብሔር የፀደቀ ሕግ አለ፡፡ ይህ ሕግ እውቅና የተሰጠው ሕግ ስለኾነ በዚያ ሕግ እየተጠቀምን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያለውን ደግሞ የሚመለከተው አካል እንዲፈታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ዕምነቶቻችንና የእኛን ጉዳይ እኛ እራሳችን መፍታት እንችላለን፡፡ መፍታት አለባቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ከጸጥታ ውጭ ያለውን ነገር በገለልተኝነት ማየት ይኖርበታል፡፡

እኛኮ ከዚህ ሂደት ውስጥ ንቁ ምዕመናንና ኦርቶዶክሳዊ አባቶች ይመጣሉ ብለን ነው የምናስበው፡፡ አሉታዊ ጎን ብቻ አይደለም የምናየው፤ በዚህ ጠባብ ቀዳዳ ውስጥ ንጹህ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ንጹህ ኦርቶዶክሳዊ አባት ይወጣሉ ብለን ነው የምናስበው፡፡ ውግዘት ሲደረግም ከይቅርታ አንፃር ነው፡፡ በይቅርታ አንድ እንድንኾን ይፈለጋል የተዘጋ ነገር የለም፡፡ ጉዳዩን በይቅርታ ጨርሶ ከሕግ የተያያዙትን ከሕግ አንፃር ማየት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ምክንያቱም በዚያ ወገን ያሉት ሦስቱም አባቶች ከዚህ ካሉት አባቶች ጋር አንድ ኾነው የሠሩት ሕግ ነው፡፡ ስለዚህ የራሳቸውን ሕግ ራሳቸው ያስኬዳሉ፡፡ በመንግሥት በኩል የሚመጣ የለም፡፡ የቤተክርስቲያኒቷ ሕግ ካልተከበረ የምዕመናን አገልግሎት አይኖርም፡፡ የምንሰብከው ሕግ እንድናከብር ነው፤ ሕግ የሚከበረው ደግሞ በር በመዝጋት ሳይኾን ሕግን አክብሮ በማስከበር ነው፡፡

ግዮን፡- ለክልሉ ሀገረ ስብከቶች የሚመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ አይውልም ይባላል፡፡ እናንተ በዚህ ዙሪያ የደረሳችሁበት ነገር አለ?

መምህር ንጉሤ፡-የቤተክርስቲያን በጀት ከሦስት ምንጭ የሚነሳ ነው፡፡ የመጀመሪያው በጀት በየአንዳንዱ አጥቢያ የሚሰበሰበው 80% ነው፡፡ 20% ግን ወደ ሀገረ ስከት የሚላክ ነው፡፡ ይኽ ከምዕመን በተለያየ መልኩ የሚሰበሰብ ነው፡፡ ሀገረ ስብከት ደግሞ ከየአጥቢያው ከሰበሰበው 20% ላይ 35%ቱን ወደየወረዳው ልኮ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት 35%ቱን ይልካል፡፡ ይህን ሲያደርግ ለመደበኛ አገልግሎትና ለአብነት ትምህርት ለየብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነትም ከየሀገረ ስብከቱ ከሚሰበሰበው ፐርሰንት በአጠቃላይ በየሀገረ ስብከቱ ከሚሰበሰበው ፐርሰንትና በአጠቃላይ በየሀገረ ስከቱ ከሚተዳደሩ የልማት አውታሮች ከሚያገኘው ገቢ ለየሀገረ ስብከቱ ድጎማ ያወጣል፡፡ ይህን የሚያደርገው ለቅዱስ ሲኖዶሱ እያሳወቀ ነው፡፡

ስለዚህ የጥያቄው የመጀመሪያ መልስ አጥቢያ ላይ ነው ያለው፡፡ “አጥቢያ 80 በመቶውን ገቢ ምን እያደረገው ነው?” የሚለው ነው መጠየቅ የነበረበት፡፡ በየትኛው አጥቢያ ስብከተ ወንጌል ተስፋፋ? የሚለውን ነው መጠየቅ! እንዲህ ዐይነት ጥያቄ ሲነሳ ዛሬ አየሩን የተቆጣጠሩ ሰዎች ቀንደኛ ተከራካሪ ይኾናሉ፡፡ ምክንያቱም እነርሱን ስለሚመለከታቸው ነው፡፡ እኛ እዚያ እንዳንደርስ ደብዳቤ ጽፈውብናል፡፡ ከሠራናቸው ትንተናዎች አንዱ ይሄ ስለኾነ እኛ ላይ ጥሩ ምልከታ የላቸውም፡፡ ወረዳዎች ደግሞ እዚያ ላይ በተቀመጠው ልክ አጥቢያዎችን መምራት አለባቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በሁለት ዓይነት መልኩ ተጠያቂው የወረዳ ቤተክህነት ነው፡፡ ከዚያ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ሀገረ ስብከት ደግሞ ባለው መዋቅር ወረዳ ቤተክህነቶችን ማስተዳደር አለበት፡፡ ይህ እንዲኾን ሂሳባችን ወደ ፋይል እንዲገባ፣ በባለሙያ እንዲመራ በተለያየ ጊዜ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር የሦስቱም ጳጳሳት ሀገረ ስብከት መታየት አለበት፡፡

ጠቅላላ ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ያደርጋሉ? እቅድ አለ? ስንት የኦሮሚያ ሰባኪ ሰብኳል? ስንት ዲያቆናትስ ፈርቷል? የአብነት ትምህርት ቤት አሉ? አንዳንዶች እኮ የካህናት ማሠልጠኛን ዘግተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የሀገረ ስብከቱ ቁልፍ ተከፍቶ የማያውቅበትም ቦታ አለኮ፡፡ ይህን እኛ እናውቃለን፡፡ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ወደላይ መናገር አስቸጋሪ ቢኾንብኝም ሰው ራሱ ዓይን ውስጥ ያለበትን ጉድፍ በደንብ ማየት አለበት፡፡ ሌላው ቢቀር ይኼ በፖለቲከኞች መመዘን የለበትም፡፡ ፖለቲከኞች ናቸው በእኛ መመዘን ያለባቸው፡፡

አሁን እነርሱ በእኛ ተቸግረዋል፡፡ እኔ የሚታየኝ ይኽ ነው፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ጉዳዩ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ በጎች መበተን የለባቸውም፡፡ ለዚህ ነው ከፍ ሲል ሰማዕትነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ያልኩት፡፡ ሰማዕትነትን ከፍሎ በጎችን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያኑ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ የሕይወት፣ የሥነልቦና፣ የንብረት ዋጋ ከፍሏል፣ ይበቃዋል፡፡ ስለዚህ ቢቻል የኾነውን አቅልሎ በወንጌል እንዲታነጽ ማድረግ ነው እኛ የምንችለው፡፡ ከተጠያቂነት ማናችንም የማናመልጥ በመኾኑ የተከፈተውን የይቅርታ በር ተጠቅመን ጉዳዩን በሰላም ቋጭተን ችግሮቻችንን በኃላፊነት እንፍታ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ቤተክርስቲያን ሕግ ያላት ተቋም ስለኾነች በኋላ መውጫ በሩ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ግዮ፡- በክልሉ ይህ ሲመት ከተፈጸመ በኋላ በምዕመኑና አባቶች ላይ የተለያዩ ወከባና እንግልት እንዲሁም አፈና እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህን ችግር ለማስቆም ያደረጋችሁት ነገር አለ?

መምህር ንጉሤ፡- ከምንሰማቸው መረጃዎች በመነሳት ችግሩ እንዲቆም ጠይቀናል፡፡ ለምሳሌ ነቀምት ላይ ይህን ነገር በጉልህ ሰምተናል፡፡ ጅማ፣ ሐረርና ሌሎች ቦታዎች ላይም ተመሳሳይ ነገር ሰምተናል፡፡ ነገር ግን አይጠቅምም፡፡ መንገዱ አያስኬድም፡፡ ጉዳዩ  ወደግጭት እንዳያመራ ጥንቃቄ ማድረግና መደማመጥ ይፈልጋል፡፡ እኛ ባለፉት ዓመታት ስንሠራ ምቹ ሁኔታ አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ የኤጲስ ቆጶሳቱ ሹመት ትክክል አይደለም የምንለው ከሕግ አንፃር ነው፡፡

ሲመቱ ሕገ ቤተክርስቲያን የምትቀበለው አይደለም፡፡ ስለዚህ መታየትና መዳኘት ያለበት ከሕግ አንፃር ብቻ ነው፡፡ ወደ መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ነገሮች ቢከሠቱ ሕገመንግሥት በጉልበት ለመናድ እየተባለ እርምጃ ሲወስድ አይተናል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጣም መታየት ያለበት በዚህ አግባብ ነው፡፡ ትግላችን አሁንም ሕግ ይከበር የሚል ነው፡፡ ቃል ዓዋዲው “ሰው በሚገባው ቋንቋ አስተምር” ይላል፡፡ ጥያቄው መኾን ያለበት “በሚገባን ቋንቋ አስተምረኝ” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ማስተማር እንዳልተፈቀደና እንደተከለከለ አድርጎ በማቅረብ ቤተክርስቲያኒቱን ከማኅበረሰቡ ጭንቅላት ለማውጣት የሚደረገው ጥረት አይጠቅምም፡፡

የምንሰብከውም መንግሥተ እግዚአብሔርን ከኾነ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ ማንነቷን የሚገልጹ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይኖርብናል፡፡ እኛ ሊቃነ ጳጳሳት ሁለት ሦስት መኪና እንደሚነዱ የት ነው የምናውቀው? ችግር ሲመጣ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን መስማት የለብንም፡፡ ይሄ ለኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ጥሩ ስሜት አይሰጥም፡፡ የሌላው እምነት ደስ ሊለው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከዚህ አኳያ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየቶች ሳነብ “ኦርቶዶክሳዊ ያልኾኑ ሁሉ ነጠላ ለብሰው አይቻቸዋለሁ፡፡” የሚል አይቻለሁ፡፡ ይኼ ለኦርቶዶክሳዊያን  ጥሩ ስሜት አይሰጥም፡፡ ለየትኛው መንግሥት ሰውን ማጨት እንዳለብን ማወቅ ያሻል፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በነቀፋ፣ በውሸት፣ በማስፈራራት፣ በስም ማጥፋት የሚኾን አይደለም፡፡ እውነትን እስከሰማዕትነት መጋፈጥ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ቆብ ውስጥ ያለ ሰማዕትነትን እንፈልገዋለን፡፡ በጎች እንደዚያ ነው የሚጠበቁት፡፡

ግዮን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?

መምህር ንጉሤ፡-  የመጀመሪያ መንግሥት ሕግ ማስከበር አለበት የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ይኽ መንግሥት የኛም መንግሥት ነው ብለን ከመረጡት መካከል ነን፡፡ ስለዚህ ቆፍጠን ብሎ ሕግ ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ጉዳይ ለሌላ አጀንዳ መዋል የለበትም፡፡ በመሠረቱ መንግሥትም ይመዘንበታል፡፡ ጉዳዩ መሬት የነካ በመኾኑም ማስተባበል አያሻውም፡፡ መንግሥት ብዙ መረጃዎች አሉት፡፡ ስለዚህ የሚመራውን ሕዝብ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ እኛ ለወሬና ለይስሙላ አይደለም ጥሪ ያቀረብነው፡፡ ወደ ይቅርታ ከመጡ ጉዳዩ በሰላም መፈታት ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን አለመግባባት ስለ ጉዳዩ ባለበት መቆም ይኖርበታል፡፡ ሕግ ስላለ በሕግ መታየት ይኖርበታል፡፡ ሌላ ምንም ማድረግ ባይቻል እንኳን ታዝበንበትና መማሪያ ኾኖ ያልፋል፡፡ ለእግዚአብሔር ተሰጥቶት የሚተው ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ መሐል ላይ እምባ እና የመገፋት ስሜት ሊኖር ይችል ይኾናል፡፡ ለእግዚአብሔር የሚነገሩ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡

ሁለተኛው ጉዳዩ እነረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የቀድሞ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሽማግሌዎች እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ በጸሎት ሰዓት “የበደሉንን ይቅር እንደምንል ይቅር በለን” ብለን ስለኾነ እነዚህ አባቶች መጀመሪያው ያልነገሩን መንግሥተ ሰማያት እስከሌለች ድረስ በመጽሐፍ የምናውቃት መንግሥተ ሰማያት የምትወረሰው በገላትያ 5፡22 ‹‹የመንፈስ ፍሬ›› የሚለው ያን ስለኾነ መንግሥተ ሰማያት በሌላ ሳይኾን በይቅርታ ትወረሳለችና ወደ ይቅርታው እንሂድ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ያደረግንላቸውን ጥሪ ተቀብለው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖስም አስፈላጊውን ሁኔታ በማመቻቸት ማገዝ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼ በደስታ የሚጨበጨብለት ጉዳይ አይደለም፡፡

ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በሐሳብ ካነሱት ጉዳይ ውስጥም አንዱ ይኼ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መርከቢቷ ስትናወጥ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምዕመናን ሚናቸው ሊኾን የሚገባው መጽናት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ቤተክርስቲያን እረፍት ያገኘችበት ጊዜ የለም፡፡ የሚታየው ፈተና ብቻ ነው፡፡ ይህም በእኛ ዘመን የመጣ በዓይነቱ የመጀመሪያ ፈተና በመኾኑ ሊከብደንና ግራ ሊያጋባን ይችል ይኾናል እንጂ ረጅም ጊዜም ላይዘልቅ ይችላል፤ ያልፋል፡፡ ነገር ግን ይዞን እንዳያልፍ በቤታችን፣ በቤተክርስቲያን፣ በእምነታችን፣ በጸሎት፣ በፆም፣ ልንፀና ይገባል፡፡ ምናልባትም በደላችን በዝቶ እግዚአብሔር ሊያስተምረን ያመጣው ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ ማኅበረ ካህናትን ምዕመናን ቤተክርስቲያናቸውን መጠበቅ፣ ሕገ ቤተክርስቲያንን ማክበር፣ በእምነት መጽናት አለባቸው፡፡ አካባቢያቸው ካለው የመንግሥት መዋቅር ጋር በመወያየት መሥራት አለባቸው፡፡ የጋራ ሀገር የግል ሃይማኖት አለን፡፡

በግል ሃይማኖት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ ሀገር አለን፡፡ በግል ሃይማኖት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ ሀገር ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ስለዚህ እንደሀገርም እንደቤተክርስቲያንም  ብዙ ሥራ አለን፡፡ ቅድሚያ እንድንሰጥ ይህን ጉዳይ ወዳልተፈለገ መንገድ ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት ማክሸፍ አለብን፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም ፤ የብሔር ጉዳይም አይደለም፡፡ ጉዳዩ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የብሔርና የፖለቲካ መልክ ለማስያዝ 24 ሰዓት የሚሠሩ ትላንት ኦርቶዶክስ የሕይወት ዋጋ ሲከፍል ድምጻቸውን ያላሰሙ ወገኖች ዛሬ ተቆርቋሪ ኾነው እያራገቡ ነው፡፡ እንደውም ጉዳዩ ያለው አክቲቪስቱና ዩቱዩበሮች ጋር ነው፡፡ ይህን ማክሸፍ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ለኦሮሞ ኦርቶዶክስ በጣም ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ይህን ጊዜ በጥበብ መሻገር አለብን፡፡ አለዚያ ትቶ የሚሄደው ጠባሳ አደገኛ ጠባሳ ነው፡፡ በተለይ ለኦሮሞ ኦርቶዶክስ፡፡

በጥንቃቄ አባቶቻችን ካስረከቡን ቅድስት ቤተክርስቲያን አንፃር ጉዳዩን እያየን ማለፍ ይኖርብናል፡፡ እኛ ብዙ ጥያቄ አለን፡፡ የእውነት ጥያቄያችን ግን ይኼ አይደለም፡፡ በደንብ አልተሰበክንም፤ ንስሐ አባት አላገኘንም፣… እነዚህን ጥያቄዎች መልሱልን ብለን ያስቀመጥነበት መንገድ አለ፡፡ ስለዚህ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ መሰጠት ይኖርብናል፡፡ የቤተክርስቲያናንን ድምጽ መሰማት በጣም ያስፈልጋል፡፡

ከሰሙኝና እግዚአብሔር ልባቸውን ካራራው ደግሞ የሌሎች ቤተ እምነቶችና ሚዲያዎች ይህቺ ቤተክርስቲያን ተመሳሳይ ፈተና ብዙ ጊዜ ስለገጠማት ይኸንንም እንደታሪኮቿ እንደምታልፈው በማመን ከእውነት ጎን ሊቆሙ ይገባል፡፡ እኔ የመካነ እየሱስ አባት ትላንት ያስተላለፉትን መልዕክት ሰምቼ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ የሚያመልኩት አምላክ ለኦርቶዶክስ አንድነት ይረዳል ብለው ካሰቡ በጸሎት ያግዙን፡፡ እንደዚያም ካልሆነ ዝም ማለት ትልቅ እገዛ ስለሆነ ብዙ ባይሞግቱን ጥሩ ነው፡፡ እውን የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ተጠናክሮ መንግሥተ ሰማያት እንዲገባ ይፈልጋሉ? እንደዚያ ከሆነ ለምን ኦርቶዶክስ ሆነው የእግዚአብሔርን መንግሥት አብረን አንወርስም ታዲያ?

የኦርቶዶክስ መጠናከርና የወንጌል በኦሮምኛ መስበክ በዚህን ያህል ካንገበገባቸው የያዙት እምነት ትክክል አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ መጥቶ ተጠምቆ ወንጌል በኦሮምኛ እንዲሰበክ አብሮ መታገል ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ እኔ የምረዳው እንደዚያ ነው፡፡ እምነትን በፖለቲካ ዐይን መመዘን ተገቢ አይደለም፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሉ በሌላ እምነት ሆነው ይህን የሚያደርጉ አካላት ለእኛ አንድ ነገር እየነገሩን ነው፡፡ ይኽውም እምነታቸው ትክክል እንዳልኾነ ነው፡፡

ሌላው መልዕክቴ ለሚዲያዎች ሲኾን ሚዛናዊ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ወንጌልን በኦሮምኛ ስበኩኝ አለ እንጂ ወንጌል በሕገወጦች ይሰበክ አላለም፡፡ ማኅበረሰቡ የራሱ እሴት፣ ባህልና መገለጫ አለው፡፡ ፊት ለፊት ያለን ሰዎች ማኅበረሰቡን መነገጃ አድርገነው እንጂ ማኅበረሰቡ የሚያስፈልገው ሰንበት ሲመጣ የሚያሳርፈውን የእግዚአብሔርን ቃለ ወንጌል መሰበክ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን መጥቶ ነላ እንዲቋጭ ማድረግ ሳይኾን በቋንቋው ወንጌልን መማር ነው ማኅበረሰቡ የሚፈልገው፡፡

 ፓትሪያርክ ምንድነው ሊል ይችላል ማህበረሰቡ፡፡ እኛ ለምንፈልገው የሚያግዘንን ነገር እየመረጥን ማኅበረሰቡን መጠቀም ትክክል አይደለም፡፡ ለማህበረሰቡ አክብሮት መሰጠት ያስፈልጋል፡፡ ሥርዓት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ግበረ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ ኦርቶዶክስ ጸንታ እንድትኖር የመጀመሪያ ጳጳስ ያበረከተ ማኅበረሰብ ነው የኦሮሞ ማህበረሰብ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ እነ አቡነ አኖሬዎስን ያፈራ እና 1600 ዓመት ታሪክ ያለው ቤተክርስቲያን ያለበት ክልል ነው ኦሮሚያ፡፡ ይኼን አቻችሎ የኖረን ማኅበረሰብ አጋጣሚውን ተጠቅመን ማኅበረሰቡን ከፍ ዝቅ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያየ ቦታ ያሉ የእኛ አባላት ከቤተክርስቲያን ጎን ብቻ መቆም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጊዜ ያልፋል፤ የቤተክርስቲያን ችግር በቤተክርስቲያን እንዲፈታ እናድርግ፡፡ በጸሎት እና በንስሐ እንበርታ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቀለ !

በእንግሊዝ ኤፌ ካፕ አምስተኛ ዙር መርሐግብር አርሰናል ማንስፊልድን 2ለ1...

ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ሊያልፍ የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ መምታቷን አስታወቀች

አብዮታዊ ዘቡ በቴሌግራም ቻናሉ ባወጣው መረጃ፤ "ፕሪማ" የሚል ስያሜ...

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት በ8 ሀገራት በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ አዘጋጀ

ከነገ ጀምሮ ወደ ካይሮ፣ ጅቡቲ፣ ናይሮቢ፣ ፍራንክፈርት፣ አክራ፣...

ከቄራ ወደ ሜክሲኮ የሚወስደው መንገድ ከሰኞ ጀምሮ በከፊል ለትራፊክ ዝግ ይሆናል

ለፈጣን አውቶቢስ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ከቄራ ወደ ሜክሲኮ...