ጠንካራ የቤተክርስቲያን መዋቅር እንዴት ይኑረን?

Date:

ኢንጂነር መርጋ ረጋሳ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሦስት ሺ ዘመናት በላይ እግዚአብሔርን ስታመልክ፣ ላለፉት ሁለት ሺ ዘመናት ወንጌለ ክርስቶስን ስትሰብክ የኖረች ሃይማኖትን ከምግባር ያስተባበሩ ብዙ ሊቃውንትን ያፈራች በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፣ በሐዋርያት፣  በሐዋርያውያን አበውና በሊቃውንት የተስፋፋች፣ በሰማዕታት ደም ያጌጠች ስንዱ እመቤት መሆኗ የተረዳ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም ዘመን ጉዞዋ ይህንን ሰማያዊ ትምህርት እና የአምልኮ ስርአት በአገር ዉስጥ እና በአካባቢ ላሉ ማህበረሰብ ለማድረስ በነበራት የአገልግሎት ቁርጠኝነት በአከባቢዉ ማህበረሰብ ያላትን ተደራሽነት ከማስፋት ባሻገር፤ በርቀት የሚኖሩ ህዝቦችን በክርስትና ለመማረክ የቻለች ናት፡፡

ይሁን እንጂ በእነዚህ ዘመናት ሁሉ ወንጌልን ስትሰብክ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውላት በተመቻቸ ሁኔታ ላለመሆኑ በዮዲት ጉዲት ጥፋት፣ በግራኝ አህመድ ወረራ፣ በካቶሊክ ሚሲዮናውያን ቅሰጣ፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በየዘመናቱ ከውጪ የተቃጡ ጦርነቶች፣ እግዚአብሔር  የለም በሚል ርእዮተ ዓለም፣ በፕሮቴስታንቲዝም፣ በምዕራባዊነት፣ በአክራሪ እስልምና እንዲሁም በተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴዎች የደረሰባትን ፈተናዎች እና ፈተናዎቹን ያለፈችበት ጥበብና ትጋት አለማንሳት የማይቻል ነው፡፡

በዘመናችንም ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ቀጥለውና ተባብሰው ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመኖቿን ለተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች እያጋለጠ በመምጣቱ፤ ምእመናን በቀሳጥያን እና አህዛብ እምነት እየተወሰዱ ቅጥርዋን እየፈተኑና ሕልውናዋን እስከ መፈታተን የደረሱ በመሆናቸው የልጆችዋን፣ የካህናቱንና የምዕመናኑን ትጋትና ህብረት ግድ የሚል በመሆኑ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ እርሱ ባወቀ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የማይተዋወቁ የቤተክርስትያን ልጆች ከአዲስ አበባና በዙርያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ተገናኝተው እንዲመክሩ እድል በማግኘታቸው ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ቤተክርስቲያንን ያናወጣትን ወጀብ በጥናት በመለየት በጥናት የተለዩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ የቤተክርስትያኒቱን መዋቅር ማገዝ ጊዜው የሚጠይቀው ዋነኛ መፍትሔ መሆኑ እና ቃለ-አዋዲን መሠረት አድርጎ የካህናትና የምዕመናንን ሕብረት ማጠናከር እንደሚገባ ታምኖበት ሕገ ቤተክርስትያንን መሠረት ያደረጉ እና የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዲጠናከር ያግዛሉ ተብለው የቀረቡትንና እንዲተገበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ታምኖባቸው ውሳኔ የተሰጠባቸውን አገልግሎቶች አፈጻጸም እንዲደግፍና እንዲፈጽም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አገልግሎቱን እንዲደግፍ ኃላፊነት እውቅናና መመርያ የተሰጠው መሆኑ እና በአገልግሎት ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

  • ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖችን እንዲጠቁ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶች እና ወደፊት የትኩረት አቅጣጫ
  • ከረጅም ጊዜ ወዲህ የውስጥ ሰላምና አንድነት እየላላ መምጣቱ እና የፖለቲካው ጫና

ምክንያቶቹ ከውስጥና ከውጪ የሆነ ከረጅም አመታት ወዲህ የውስጥ ሰላምና አንድነት እየላላ ከመምጣቱም ባሻገር በአንዳንድ ቦታዎች እና ጊዜያት ኦርቶዶክሳዊያን ጎራ ለይተው ሲሟገቱ ይስተዋላል፡፡ በተቋም ደረጃ የሰላምና እርቅ ኮሚሽን በየደረጃው ያሉት አለመግባባቶች በወቅቱ እንዲፈቱ መዋቅራዊ ጥበቃው እንዲጠናከር እና ከውስጥና ከውጪ ጥቃት እንዲጠበቅ፣ ከግለሰቦችና ከቡድኖች የሚነሱትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ከጥቃቅን እስከ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች በአንድም በሌላ ምክንያት ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ እየተገፉ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያትን በውጥረት እንዲያሳልፍ ምክንያት ከመሆናቸውም በላይ ለጠላት ሙሉ አቅሙ ተጠቅሞ አለመግባባቶችን ለጉዳዩ ማስፈጻሚያነት ምቹ እድል ፈጥሮለታል፡፡ በሌላ በኩል በሀገር ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ቤተ ክርስቲያን ከነበራት ሚና እንድትገለልና በውስጥ ጉዳዮቿ እንድትወጠር እንደስልት የውስጥ ሰላምና አንድነትን ማናጋት ይጠቀሙበታል፡፡

  • የቤተ ክርስቲናችን መዋቅር ሁለተናዊ በሆነ መልኩ በየጊዜው አለመልማት

እንደሚታወቀው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር አሁን ባለንበት ሁኔታ በትክክል አቢያተ ክርስያናት ባሉበት ሁሉ በሕገ ቤተ ክርስያንና በቃለ አዋዲ ላይ በተቀመጠው ልክ አለመተግበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአገልግሎት ስፋት እና ከዘመኑ አንጻር በየደረጃው ያለው መዋቅራችን በመሰረተ ልማት (መንገድ፣ ትራንስፖርት፣ ኔትዎርክ፣ ቢሮና በመሳሰሉት) አለመደራጀት፣ በየደረጃ ያሉት የአመራር አካላት በቂ የአመራር እና የሙያ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደፊት እንዲራመዱ የማድረግ ስራዎች ውስንነት፣ የአጋዥ ተቋማት ማለትም የቁጥጥርና ምርመራ መምሪያ፣ የሥነ-ሥርዓትና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን፣ የቋንቋዎች  እና ሥነ-ጽሑፍ፣  የሕዝብ ግንኙነት እና ሌሎችም ተደራጅተው የሚሰሩት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ዝቅተኛ መሆኑ የሕጎችና ደንቦች እንዲሁም ውሳኔዎች አፈጻጸም ፈተና የበዛበት በመሆኑ መዋቅሩ እራስን የመከላከል አቅሙን እያዳከሙ እና ከውስጥና ከውጪ ባሉት ኃይሎች እንዲጠቃ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ከውስጥና ከውጪ ኃይሎች ተወጥሮ ወደፊት እንዳይራመድ በመደረጉ ምክንያት ለውጥን ለመምራት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በመግባቱ አክራሪዎች በቀላሉ ጫና እንዲያሳድሩ ዕድል ፈጽሯል፡፡

  • የባለድርሻ አካላት ተኮር ተግዳሮት

በግልም ይሁን በቡድን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማገዝ የሚንቀሳቀሱ አካላት አብሮ ማቀድና መስራት፣ መዋቅሩን የመደገፍ ሂደቶቹ ውስን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለመዋቅሩ ፈተናና ለውጪ ጠላትም ጭምር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መጠቀሚያ መሆንና በባለድርሻ አካላት አለመግባባትና አብሮ አለመስራት ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ የቤት ስራ ሆኖ የውጪ ጥቃት እንዳይከላከል አቅሙን አዳክመውታል፡፡

  • የተልዕኮ አገልግሎት ተኮር ተግዳሮት

የቤተ ክርስቲያን የትምህርት፣ ስልጠና፣ ስብከትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎቶች በመደበኛው መዋቅር ብቻ ተደራሽ የሚሆን አይደለም፡፡ ሌሎች አጋዦችም ያስፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ ተልእኮ ከቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ አንጻር ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት ጠላት ይህን ቀዳዳ በመጠቀም በተለይ ልጆችን በመለያየት፣ ወደ ዘውጋዊነት እንዲሄድ ማድረግ እና በዘርፉ የሚደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን የማደናቀፍ ስራዎችን በመስራት በተለይ የውስጥ አንድነቷን ለአደጋ እንዲጋለጥ አደረጉ፡፡ በሌላ በኩል በቤቱ ያለውን የማጽናት፣ በአንድም በሌላ ምክንያት የውጡትን ለመመለስ፣ ያላመኑትን ለማሳመን እንዲሁም ተተኪ አገልጋዮችን የማፍራት ስራዎች በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት አለመሄዱ ለጠላት መልካም አጋጣሚ እንዲሆነው አድርጓል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች (ሊሰሩ የሚገቡ ሥራዎች)

  1. የሰላምና እርቅ ኮሚሽን ማቋቋም፡- ለአክራር እስልምና መጠናከር ምክንያቱ ጠንካራ የውስጥ ሰላምና አንድነት አለመኖሩ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን አለም አቀፋዊ የሰላምና እርቅ ኮሚሽን አቋቁማ እስከ ምእመናን ድረስ ጠንካራ አንድነትና ሰላም እንዲኖር በቂ ጊዜ፣ የሰው ኃይልና በጀት መድባ መስራት፣ የመረጃና ደኅንነት ስራዎች ማጠናከር፣ የቅሬታና አቤቱና አስተነጋገድ አሰራርን በመዘርጋት በሁሉም ደረጃ የውስጥ ሰላምና አንድነት አከባቢ ያሉትን ችግሮች መሰረታዊ በሆነ መንገድ መፍታት፡፡ በሰላምና እርቅ ኮሚሽን በኩል የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ከውስጥ እና ከውጪ ጥቃት በቂ እና አስተማማኝ ጥበቃ እንዲደረግለት እና በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ዙሪያ ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸውና እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል፡፡ በሁሉም ደረጃ ቤተ ክርስቲያናዊ መግባባትን መፍጠር፡፡
  • የሀገር ውስጥና የውጪ ሕዝብ ግንኙነት እና የብሮድካስት ባለስልጣንን ማጠናከር፡- በውስጥ ይሁን በውጪ ያሉት እና በተለያየ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሱ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች (ሞት፣ ተገዶ መስለም፣ ተገዶ መደፈር፣ መፈናቀል፣ የአቢያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የክርስቲያኖች ንብረት መውደም…) የፖለቲካ እና የብሔር ብቻ አድርጎ ከመሳል በተለያየ አቅጣጫ በመመልከት ፍላጎቱ ረጅምና አስከፊም ጭምር እንደሆነ በየደረጃው ያለው የቤተ ክርስቲያን የአመራር አካላትና ምእመናን ተገንዝበው በዛ ልክ ግዴታቸውን እዲወጡ ማድረግ በሚያስችል ደረጃ የብሮድካስት ባለስልጣንን፣ የሀገር ውስጥና የውጪ ሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር፡፡
  • ጽ/ቤቶችን ማጠናከር፡- የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ለማስፈጸም የቅዱስ ፓትርያርክ ጽ/ቤት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና የዋና ሥራ አስኪጅ ጽ/ቤት ቁልፍና ቀዳሚ ሚና ያላቸው ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችም የሚፈጸሙት በእነዚሁ ጽ/ቤቶች አማካኝነት ነው፡፡ በመሆኑም ጽ/ቤቶቹን በበቂ መሰረተ ልማት ማለትም በጀት፣ ቴክኖሎጂ (በተለይ በቂ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ማግኘት በሚያስችል)፣ በስልት (ሶስቱ ጽ/ቤቶች ስትራቴጅክ በሆነ መንገድ ማገናኘት፣ አለም አቀፋዊ ይዘት…) ባለው ማጠናከር ትልቁና ግንባር ቀደም ስራ አድርጎ መስራት፡፡
  • የቁጥጥርና ምርመራ መምሪያን ማጠናከር፡- ኦርቶዶክሳዊ ካባ ለብሰው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሰሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ተከታትሎ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ፣ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር አተገባበርና አጠባበቅን ለማጠናከር፣ ጠንካራ የሕጎችና ደንቦችና ውሳኔዎች አፈጻጸምን ለመፍጠር፣ የሀብት አስተዳደርን በማጠናከር የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ በበቂ ሁኔታ ለማስፈጸም በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 22 ላይ በተቀመጠው መሰረት በቁጥጥርና ምርመራ መምሪያን ሁለተናዊ በሆነ መንገድ በማጠናከር አገልግሎቱን ከመፈጸም እኩል ከውስጥና ከውጪ ፈተናዎች እራሱን መከላከል በሚችል ደረጃ ማደራጀትና ማጠናከር፡፡
  • የሥነ-ሥርዓትና ሥነ-ምግባር ኮሚሽንን፡- የሕጎች፣ ደንቦችና ውሳኔዎች አለመፈጸም እና አለመከበር እንዲሁም መጣስ ውጪ ላለው አክራሪ አካላት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረና በተቃራኒው ግን መዋቅርን እያዳከመና የጠላት መጠቀሚያ እያደረገ እንዳለ ታስቦ ትኩረት በመስጠት ማስተካከል፡፡ በሌላ በኩል ከአሰራር ውጪ እና ከቤተ ክርስቲያኒቷ አስተምሮ ውጪ የሚደረጉ አካሄዶች ለማንኛውም ጥቃት የማጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑ ታውቆ አፋጣኝ ማስተካከያ ማድረግ፡፡ መዋቅሩን የመበተን፣ ሲኖዶስን የመክፈል እና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የመበተን አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ታስቦ ከሥነ-ሥርዓትና ሥነ-ምግባር ጉዳዮች ጋር የሚገናኙትን ክፍተቶች እንዲስተካከል ማድረግ፡፡ 
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ፕሮጀክት፡  የትምህርትና ስልጠና አገልግሎት፣ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት፣ የትርጉምና ሕትመት አገልግሎት፣  የሕግና ምክር አገልግሎት፣ የአቅም ግንባታ አገልግሎት፣ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙት አገልግሎትና ተያያዥነት ያላቸውን አገልግሎቶች የሚደግፍ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በዋና ሥራ አስኪያጅ ደረጃ ተከፍቶ ከመደበኛ አገልግሎት ውጪ በመደበኛው መዋቅርና አሰራር የሚሰሩትን ስራዎች ለማገዝ የሚያስችል ሐብት (ጥሬ ገንዘብና በዓይነት) በማሰባሰብ በመላ አለም በመደበኛ መዋቅሩ ተደራሽ መሆኑ ያልቻሉትን ማገዝ እና በቂ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ያለውን የሰው ኃይል ማብቃት፣ ያሉትን ማጽናት፣ የሄዱትን መመለስ እንዲሁም ያላመኑትን ለማሳመን መስራት የሚያስችልና በዋና መዋቅሩ በየደረጃው የሚሰሩትን ስራዎች በማዕከላዊነት (በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ) ለመደገፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአቢያተ ክርስቲያናት የተቀናጀ የልማት መርሐግብር  በተሰራው ሰነድ መሰረትመጀመር እንዲፈቀድልንና ለዚህም የመነሻ በጀት እንዲመደብልን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና አከናወነ

ኩባንያችን ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመተባበር...

የኔታንያሁ ድንገተኛ ማስጠንቀቂያ እና የቢሊዮን ዶላር የጋዝ ሚስጥር!

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከታሪካዊቷ የግብፅ ምድር የሚሰማው...

ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከግዛቷ እንድታስወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች

የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና...

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች ቁጥሩ ከ5.46 ሚሊየን በላይ መድረሱን ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2018 አ.ም የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን...