ፈላስፋው አንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር)

Date:

ፈላስፋው አንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር)

(1940 – 2016 ዓ.ም)

‹‹…ሀገራችን ኢትዮጵያ የነጻነቷ እና የማንነቷ መለዮ ወይም ፊርማ፣ የጽሑፍ ባህሏ ነው። ኹላችንም ባንኖርና፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ጽሑፎቿ ብቻ ቢቀሩ፣ ማንነቷ እና ነጻነቷ ዕውቅና አያጣም ብዬ አምናለሁ።…››

(ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ)

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝዳት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። የእኚህን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና አካዳሚያዊ ታሪክ ውስጥ የራሳቸው ድርሻና አሻራ ያላቸው ምሁር ተከትሎም በርካቶች ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ተሰማ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መንበረ ገብረ ማርያም በ1940 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተወለዱ፡፡ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ  ትምህርት ቤት፣ ወደ አሜሪካ በመጓዝም በዊሊያምስ ኮሌጅ ፍልስፍና እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በመማር በመጨረሻም ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በአስተማሪነትም  በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በዩሲኤልኤ፣ በርክሌይና ፔንሲልቬንያ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ ሲሆን፣ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል።

ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ የቆዩት አንድርያስ ያረፉት ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲኾን ሥርዓተ ቀብራቸው ጳጉሜ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ የአንድ ልጅ አባት የሆኑት አንድርያስ፣ ሌሎች ሁለት ልጆችንም እንደ አባት ተንከባክበው ማሳደጋቸው በገጸ ታሪካቸው ተጠቁሟል።

ስለ ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ የተሰጡ ምሥክርነቶች እና አስተያየቶች

ስድስት ነገሮች ስለ እንድርያስ (ማዕረግ ጌታቸው)

አንድ፤ ሚስቱ እርሷ ነች!

ከታች የምታዩት የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ Mother Ethiopia የተሰኘ ሥራ ለእኔና ለእናንተ ተራ ስዕል ነው፡፡ ለእንድርያስ እሸቴ ግን የትዳር አጋሩ ምስል፡፡ አዎ! እንድርያስን የልጅ እናት ያደረገችው እሙዬ አስፋው ማለት ይች ናት፡፡ በእርግጥም  በውበቷ  መነጋገሪያ የነበረችው፤ ሎሬቱን ቡርሽ አስነስታ ከሰሌዳ ፊት የገተረችው በምስሉ ላይ ያለችው ውብ ሴት መነሻ የእንድርያስ እሸቴ ባለቤት ነበረች፡፡

ሁለት፤ ባለ ንስሃ አባቱ እንድርያስ

እንድርያስ የአገሩን ትውፊት የተጸየፈ አብዮተኛ ብቻ ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ ሦስት የፍልስፍና መጻሕፍ አንብበው የፈጣሪን ሕልውና ለሚጠራጠሩና ሐይማኖት ምን ሊፈይድ ለሚሉም ራሱን የቻለ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከክፈለ ዘመናችን መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፈላስፎች አንዱ የሆነው ሰው እንደ አገሩ ትውፊት የንስሃ አባት ነበረው ብልህ ታምናለህ ? ለእንድርያስ ትልቁ መሪ ምኒሊክ ነው፡፡ የሚወደው እንስሳ ደግሞ አህያ፤ ሁለቱም የቤቱ ድምቀቶች ነበሩ፡፡

ሦስት፤ ጸጸት

እንድርያስ የሔደበትን መንገድ ፍጹም የሚያደርግ ራሱን አምላኪ አልነበረም፡፡ በአንድ መድረክ  የእዉቁን የሥነ-ጽሁፍ ተማራማሪ ቴዎድሮስ ገብሬ(ተ/ፕ) ጥናት ካደመጠ በኋላ የተናገረው ነገር ይህን ያረጋግጣል፡፡ “እስክንድር በጎስያንና ስብሓት ገብረእግዛብሔር በአብዮቱ ዋዜማ ላይ የሁለት ሺህ ዓምት ታሪክ ያላት አገር አብዮት መሸከም ትችላለች ብላችሁ ታምናላችሁ ? ብለውን ነበር:: አልሰማናቸውም እንጂ” ብሎ መፀፀቱም ለዚህ ነው፡፡ እንድርያስ በቅርብ አመታት በተላለፈ የቴሌቪዥን ቃለ-መጠይቁ ላይም የእኛ ትውልድ ጥፋት ብዙ ነው ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡

አራት፤ ፊውዳሉ እንድርያስ

እንድርያስ የፊውዳል ልጅ ነው፡፡ ኋላ የንጉሱን ዙፋን በመገልበጥ በኩል አቀጣጣይ የነበረችው ሉሉ የተባለችውን ውሻ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወሰዷት ከእንድርያስ እጅ  ነው፡፡ ይገርማል ! ወቅት ጠብቆ እንደሚፈናዳ ቦንብ ሉሉ ዘግይተው እነ አንድርያስ ላፈነዱት አብዮት ማቀጣጣያ ሆነች።

ሌላም ላክል፡፡ የእንድርያስ እናት ከገጠር ካልመጣ አገልግል ውጭ ምግብ በአፌ አላዞርም የሚሉ ቀበጥ ፊውዳል ነበሩ፡፡ ታዲያ እነዚያ ጭሰኞች ምግብ ይዘው መምጣት በማይችሉ ቀን ወይዘሮ መንበረ አንድ መላ ነበራቸው፡፡ ምግብ አሰርተው በአገልግል አስቋጥረው ባሪያዎቻቸው ተሸክመው አዲስ አበባን ሲዞሩ እንዲውሉ ያደርጋሉ- ጣዕሙን ለማምጣት፡፡ ምን ልልህ ነው፤ እንድርያስ ያመፀው በፊውዳሉ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ትንሹ ልጅ  የተነሳው በእናቱ ላይ ነው፡፡

እንድርያስ ለአገሬ ይበጃል ያለውን አብዮት ያፈነዳው በወላጆቹ ላይ ነው፡፡ እናስ? እናማ ለአገርህ አይደለም ለራስህ የምትሆን ኩርማን የመብት ጥያቄ ለመጠየቅ የአለቃህን ፊት እያየህ ስለ እንድርያስ ሞራል ማውራት ስላቅ ነው፡፡  ልጨምርህ! እንድርያስ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወቱ ያለፈው ዘመድ ቸግሮት አይደለም:: ከኢትዮጲያ ለመለያየት ባለመፈለጉ እንጂ፡፡

አምስት፤ ጥቁር አብዮተኛውእንድርያስ

እንድርያስ በጥቁር አሜሪካዊያን የእኩልነት ንቅናቄ ትግል ውስጥ ብርቱ ትግል ያደረገ ታልቅ ሰው ነው፤ ማርቲን ሉተሪ ኪንግ I have a dream ብሎ ሲናገር በቦታው የነበረ የታሪክ  ምልክትም ነበር፡፡

ስድስት፤ ወንድማችነትን ናፋቂው እንድርያስ

የእንድርያስ  ቦታ በፍልስፍና ውስጥ ወንድማማችነት ይመስለኛል፡፡ ብዙ የፍልስፍና ሊቃውንት ስለነፃነት (liberty)  እልፍ ፅፈዋል፡፡ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት (equality) ሩቅ ሄደዋል፡፡ እንድርያስ ግን መልኩ ወንድማማችነት (fraternity) ይመስለኛል፡፡ በእሱ እምነት ነፃነትም ሆነ እኩልነት ፍሬ የሚያፈሩት በወንድማማችነት ነው፡፡ ይህ ምልከታው ለኢትዮጵያም እንደሚሰራ ያምናል፡፡ ለምን እንዴት የሚለውን ከጽሁፎቹ አግኙ፡፡

ስንብት

በመጨረሻም እንድርያስ ለወዳጆቹ ስልክ ሲደውል ራሱን በሚጠራበት ግጥም ልሰናበት!!

እንድርያስ እሸቴ

ማርና ወተቴ

ደህና ሁን! 

ምሁራዊ መኮፈስን የማያውቁ (ጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ)

ጥልቅ እውቀታቸውን በቀላል ቋንቋ፣ … ግድ ካልኾነባቸው በቀር ፈጽሞ እንግሊዝኛ ሳይቀላቅሉ፣ በጣም በትሁት አነጋገር ማካፈል የሚችሉ፤ …

በጠያቂያቸው ንግግር ውስጥ ያለ ስህተትን “እንዲህ ያልከው ትክክል አይደለም” ከማለት ይልቅ፣ “እንዲህ ስላልከው ነገር እኔ አላውቅም” ወይም “እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት በመተናነስ የሚያርሙ፣ …

ብዙ ሰዎች በየተራ በሚያወሩበት መድረክ ላይ፣ አንዳችም ቃል ሳይተነፍሱ ለብዙ ሰዓታት ተቀምጠው ማዳመጥ የማይሰለቻቸው፤ … ምሁራዊ መኮፈስን የማያውቁ፤ እጅግ በጣም ትሁት ሰው ነበሩ – ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ።

… ‘ምናለ አንድ ቀን መኖሪያ ቤታቸው ሄጄ፣ አውሮፓ ውስጥ በተካሄደ አንድ የኢሕአፓ ጉባዔ ላይ ከብርሃነ መስቀል ረዳ ጋር ስለተከራከሩበት ርዕሰ-ጉዳይ ይዘት በስፋት እንዲያወሩኝ ብጠይቃቸው?’ እያልሁ ስመኛቸው የኖርሁት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ … [በሸገር “የቅዳሜ ጨዋታ እንግዳ” ላይ ፕሮፌሰር አንድሪያስ፣ “ሁለታችን ብቻ ነበር የምንከራከረው” የሚለውን ንግግራቸውን መነሻ አድርጋ መዓዚ “የክርክራችሁ ነጥብ ምን ነበር?” ብላ አለመጠየቋ ቅር አሰኝቶኛል።] …

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሒልተን ሆቴል ውስጥ በተካሄደ አንድ የፓነል ውይይት፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ ንግግር ላይ ተመሥርተው ጣል ባደረጓት አንዲት ተረብ አዳራሽ ሙሉ ታዳሚ አስቀው የኤምባሲውን ተወካይ በንግግሩ እንዲሸማቀቅ ያደረጉት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ …

በ1860 በጄነራል ናፒየር የተመራው የብሪታንያ ጦር ከመቅደላ አምባ የዘረፋቸውን የሀገር ቅርሶች ለማስመለስ ከእነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር Association for the Return of Maqdala-Ethiopia Treasures (AfRoMET) የተሰኘ ማኅበር መሥርተው [ጥረታቸው ባይሳካም] ጥያቄው በመንግሥት ተደግፎ በይፋ ለብሪታንያ መንግሥት እንዲቀርብ በማድረግ ብዙ የለፉት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ …

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን በማርቀቅ ሂደት ላይ ከአቶ ክፍሌ ወዳጆ እና ከሌሎች ምሁራን ጋር የድርሻቸውን ምሁራዊ ሚና የተጫወቱት፣ [አንቀጽ 39 ላይ “እስከ መገንጠል” የምትለዋን ሐረግ ረቂቁ ላይ የጨመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው።] … ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ … ለዘመናት ያከማቹትን ሰፊ እና ጥልቅ እውቀት ይዘው ወደማይቀርበት ቀጠሮ ሄዱ። …

ፕሮፌሰር አንድርያስ ምናለ ከሰፊው እውቀታቸው ጨልፈው ጥቂት ጠቃሚ መጻሕፍትን በሀገር ቋንቋ ጽፈው ባስነበቡን እያልሁ ስመኝ ነው የኖርሁት። ኾኖም ግን፣ ይህን እየጻፍሁ ሳለሁ፣ “ለሀገራችን ‘ፖለቲካ’ እውቀት ምን ይፈይድለታል?!” የሚል ጨለምተኛ ድምጽ ይሰማኛል።

ለፕሮፌሰር አንድርያስ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸው። …

ለቤተሰቦቻቸውና ለቅርብ ወዳጆቻቸው ፈጣሪ መጽናናትን ይስጣቸው።ምንጮች፡- ሪፖርተርና ማኅበራዊ ሚዲያ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...