ሁለት የኢሕአፓ ፖለቲከኞች እና የተቃዋሚዎች ጠበቃ ታሰሩ

Date:

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞቹ አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ለቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንደአ ጠበቃ የሆኑት አበራ ንጉስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ተናገሩ።

ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው “በፌደራል ፖሊስ” አባላት የተያዙት ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ በተለያየ ሰዓት እንደሆነ የቤተሰብ ምንጮች፣ ጠበቃ እና የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

በቅድሚያ የተያዙት ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጠበቃ በመሆኑ የሚታወቁት አበራ ንጉስ ናቸው። የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የፌደራል መንግሥት ባቋቋመው በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አበራ፤ ሲታሰሩ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በ2016 ዓ.ም. “ጦርነት ይብቃ” በሚል ሊካሄድ ታቅዶ ከነበረው ሠልፍ ጋር በተያያዘም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

“የፌደራል ፖሊስ” አባላት ወደ ጠበቃ አበራ ቤት የመጡት ሰኛ ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የቤተሰብ ምንጭ ተናግረዋል።

በሰዓቱ አበራ ወደ ሥራ ለመሄድ ዝግጅት ላይ እንደነበሩ የሚናገሩት ምንጩ፤ “በድንገት ነው የመጡት፤ እሱም ለራሱ ተደናግጦ ነበር” ብለዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላቱ አበራ “ለምርመራ እንደሚፈለጉ” መናገራቸውንም አስታውሰዋል። እንደ ምንጩ ገለጻ፣ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ግን ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አበራ የት እንደሚገኝ እስካሁን በትክክል አለመታወቁንም አክለዋል። ማክሰኞ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ለብርበራ ወደ ቤት መጥቶ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።

የጠበቃ አበራን መታሰር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቅድሚያ ካጋሩ ሰዎች አንዱ የኢሕአፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ይሳቅ ወልዳይ ናቸው።

ይሳቅ፤ ግንቦት ላይ በተካሄደው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ኢሕአፓን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት ከቀረቡ በኋላ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ይታወሳል። ይሳቅም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

የጠበቃው አበራ ወዳጅ የሆኑት ይሳቅ ቀን 8 ሰዓት ተኩል በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት በላይ ተናግረዋል። ይሳቅም የተያዙት በፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሆነ የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

አንድ ያነጋገርናቸው ምንጭ፤ ሰኛ ከሰዓት ይሳቅ ከፖሊስ መኪና ወርደው ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሲገቡ መመልከታቸውን አስረድተዋል።

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም እንደሚናገሩት በአንድ ቀን የታሰሩ ሦስተኛ ሰው የሆኑት የፓርቲው አባል ታዋቂው ፖለቲከኛ አበባ አካሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ የነበሩት አበበ አካሉ ሐምሌ 2016 ዓ.ም. አንስቶ ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኢሕአፓን ተቀላቅለዋል።

አበበ “ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ” በሆነ ስፍራ የተያዙት ምሸት ላይ መሆኑን የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ተናግረዋል። ፖለቲከኛው ከሰኛ ምሽት እስከ ማክሰኞ ጠዋት ድረስ ያሉበት ሳይታወቅ መቆየት ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል።

“እስከ ጠዋት ድረስ ቤተሰቡ ከፍተኛ ስጋት ላይ ነበር፤ አሁን ነው በቅርብ [ሰዓት] ወደ ሜክሲኮ ታስሮ እንዳለ ማረጋገጥ የተቻለው” ሲሉ ስደስት ሰዓት ገደማ ላይ ተናግረዋል። አበበ ያሉበት ቢታወቅም እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳልተገናኙ አክለዋል።

ጠበቃ አበራም ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘታቸውን አንድ ምንጭ ተናግረዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ሌላ ምንጭ ገልጸዋል።

የሦስቱን ግለሰቦች እስር በተመለከተ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ጥረት አልተሳካም። የፌደራል ፖሊስ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዲ በአሁኑ ሰዓት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

BBC

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በዓለም የምግብ ምርምር ድርጅት ሹመት ተሰጣቸው

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ (AGRA) የቦርድ ሰብሳቢ...

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በካናዳ ሀገር ሊሸለሙ ነው

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በንግዱ...

በምክክሩ ወቅት በሀሳብ ልዩነት “አድማ የመቱ” ነበሩ

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ22ኛው ቀን ውሎው በስልታዊ ቡድን ደረጃ...

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለዉ ግጭት እንዳሳሰበው የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን ገለፀ

የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን  በኢትዮጵያ ፌደራላዊ  መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ...