ሩሲያ ለዛሬ ሰኞ አጥቢያ ከ160 በላይ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማውደሟን አስታወቀች። እንደ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሩሲያ ገለፃ የአየር መከላከያ ኃይሏ 162 የዩክሬን ድሮኖችን መትቶ አውድሟል።
አብዛኛዎቹ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተመተው የከሸፉት በሁለቱ ሃገራት የድንበር አካባቢዎች ነው። 57 በኩርስክ ክልል እና ሌሎች 31 በቤልጎሮድ ክልል መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቃል።
ሰው አልባ ጥቃቱ የተፈፀመው ከሩሲያ እና ከዩክሬን የተውጣጡ ልዑካን ዛሬ በቱርክ ሊያደርጉት ከታቀደው ስብሰባ ሰዓታት በፊት ነው። የስብሰባው አላማ ከሦስት ዓመታት በላይ በዘለቀው የዩክሬን ግጭት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመደራደር ነው።
ልኡካኗን ወደ ኢስታምቡል እንደምትልክ ያስታወቀችው ዩክሬን ትናንት የስለላ መሥሪያ ቤቷ በአራት የሩሲያ ወታደራዊ የአየር ማረፊያ ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች ከ40 በላይ የሩሲያ የጦር እና የስለላ አውሮፕላኖች ማውደሙን ይፋ አድርጋ ነበር። ሁለቱ ሃገራት ከድርድሩ በፊት በየፊናቸው የወሰዱት ጠንካራ ውጊያ በድርድሩ ላይ የሚኖረውት ሚና እየተጠበቀ ነው።
ፎቶ፤ በኢስታንቡል ሩሲያ እና ዩክሬን የሚደረደሩበት የቺራጋን ቤተ መንግሥት
