ሰሙነ ሕማማት

Date:

ሕማማት የሚለው ቃል ሐመመ ወይም ሐመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ሲበዛ በብዙ ቁጥር ሲነገር ሕማማት ይሆናል መከራ ስቃይ ማለት ነው ፡፡ ሰሙነ ሕማማት ማለት የሕማማት ሳምንት ማለት ነው፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለበትን ሳምንት ሰሞነ ሕማማት በጾምና በጸሎት ማሰብ እንደሚገባ ያስተማሩትና ጾመው እንድንጾም አርአያ የሆኑን ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው ፡፡

ዛሬ እኛ እንደምንጾመው ከዐብይ ጾም ጋር ተያይዞ አልነበረም ሐዋርያት የጾሙት ሰሞነ ሕማማትን ከመጾማቸው ቀደም ብለው ዐብይ ጾምን ይጾሙ ነበር ፡፡ ከዐብይ ጾም ጋር ተያይዞ መጾም እና ሌሎችም ሥርዓቶች መፈጸም የጀመሩት ከዛሬ 600 ዓመታት ገደማ የግበረ ሕማማት መጽሐፍ ከግብፅ መናንያን ከአረብኛ ወደ ግእዝ ከተተረጎመ በኋላ ነው ፡፡ ጾሙ ግን ከዛ በፊት ሐዋርያት ይጾሙት ነበር ፡፡

በተለይ ከዐብይ ጾም ጋር ተጠጋግቶ እንዲቀመጥ የተደረገው በ3ኛ መ/ክ/ዘ በተነሳው በዲሜጥሮስ ጻድቅ አማካኝነት ነው ፡፡ ቅዱስ ዲሜጥሮስ ትንሣኤ ሰኞ ማክሰኞ ሲከበር ደስ አላለውም ነበርና ምን አለ ትንሣኤ እሑድን ባይለቅ ስቅለት ዓርብን ባይለቅ እያለ ከመመኘት አልፎ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ይለምን ነበር ፡፡

እግዚአብሔርም ጥሩ ባህረ ሐሳብ ወይም ቀመር ሰጠው ፡፡ በዚህም ቀመር መሠረት ትንሣኤ መቼም መች እሑድን እንዳይለቅ ሆነ፡፡

ሰሞነ ሕማማት በሚታሰብባቸው 6 ቀናት ከደስታ ከጨዋታ ተለይቶ ሕማሙንና ሞቱን የሚናገሩ መጻሕፍትን ሲያነቡ ሲሰሙ መዝሙረ ዳዊትን ውዳሴ ማርያም ከሰጊድ ጋር ሊያደርሱ ይገባል፡፡

የቻለ ሁለት ሁለት ቀን ያልቻለ እስከ ዕርበተ ፀሐይ (ፀሐይ እስክትገባ / 1 ሰዓት /) ሊጾም ይገባል፡፡ ምግቡ ሕብስት በጨው መጠጡ ጥሩ ውኃ ነው፡፡ በእኒህ ዕለታት ጮማ የሚቆርጥ ወይን ጠጅ የሚያንቆሮቁር ቢኖር ዕድል ፈንታው ጽዋ ተርታው ጌታን በመስቀል በመግደል ደስ ከተሰኙ ከአይሁድ ጋር ነው፡፡

የታመመ ከሆነ ግን ከበዓለ ሐምሳ በኋላ ተክቶ ሊጾም ይገባል ይልቁንም ከሴት የደረሰ ሰውነቱን ያረከሰ ዕዳው ፍዳው ይጸናበታል፡፡ ዳግመኛ ይህ ሰሙነ ሕማማት ውስጥ ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ እንደመሆናቸው ወደ ሲዖል የወረዱ የሰው ልጆች ስቃይ ይታሰብበታል፡፡ ኤፌ 2፡1 ቆላ 2፡13

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች የጌታን መከራ ስቃይ የምናስበው በሰሞነ ሕማማት ብቻ አይደለም ፡፡

ለምሳሌ፦
✝️ የረቡዕ እና ዓርብ ጾም፡- ረቡዕ ሊሰቅሉት የመከሩበትን ዓርብ የሰቀሉበትን የምናስብበት ነው


✝️ መዝሙር ስንዘምር ማሸብሸብና ማጨብጨብ ከበሮ መምታታችንም የጌታን መንገላታትና በጥፊ መመታቱን እያሰብን ነው። ወረቡም ከአምላካችን መከራ ጋር የተያያዘ ነው ፡፡


✝️ ንዋየ ቅድሳቱ ከበሮ ራሱ በአሠራሩ እላዩ ላይ ያለው ጨርቅ ያለበሱትን ቀይ ከለሜዳ ጨርቅ፣በላዩ ላይ ያለው ጠፈር ደግሞ ሲገርፉት በሰውነቱ ላይ የወጣው ሰንበር ምሳሌ ነው


✝️ የአንገታችን ማዕተብ ክርም ጌታ የታሰረበትን ገመድ ለማሰብ ነው


✝️ ካህናት ለአገልግሎት ሲሰየሙ የሚለብሱት ልብስ ከፊትና ከኋላ ያለው መርገፍ ጌታችን እንዴት እንደታሠረ እንዴት እንደተጎተተ ያሳያል ፡፡


✝️ አንድ ክርስቲያን በቀን እንዲጸልይባቸው የታዘዙት ሰባቱ ጊዜያት (12 ሰዓት፤ 3 ሰዓት፤ 6 ሰዓት፤ 9 ሰዓት፤ 11 ሰዓት፤ ምሽት 3 ሰዓት፤ ምሽት 6 ሰዓት) ሁሉም ከጌታ በእለተ ዓርብ ከተፈጸመበት ግፍ ጋር የተያያዘ ነው ፡፡

በአጠቃላይ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከጠዋት እስከ ማታ የጌታን ሕማምና መከራ ስቃይ እንድናስብ በሥርዓት ስላብናለች ነገርግን ሰሙነ ሕማማት የጎላው ዋናው መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ስለዚህ በሰሙነ ሕማማት ከስራም ከምንም ያለችንን ጊዜ እየቀነስን ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ መሰገድ ቅዱሳት መጻሕፍት ማንበብ እና መስማት ይገባል ፡፡

ሁኔታው የተመቻቸላቸውና ያሰቡበት ያለውንም በረከት የተረዱ የዓመት እረፍት በመውሰድ ሳምንቱን በቤተክርስቲያን የሚያሳልፉ አሉ ፡፡ በተጨማሪም ወጣ ወደአለ ገዳም በዓት ገብተው ይህንን ሥርዓት የሚፈጽሙ የጌታን ሕማምና መከራ የሚያስቡ አሉ ፡፡ እነዚህ የታደሉ ናቸው ፡፡ ነገርግን በምንችለው አቅም ሕማማተ ክርስቶስን በሚገባ ልንዘክር ያስፈልጋል ፡፡

በምንም ዓይነት ምክንያቶች ሊያመልጠን ግን አይገባም። ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ከሆነ ማለትም የሰሞነ ሕማማት የሚውልበት ቋሚ ስላልሆነ ከሀገር ብንርቅና ከሰው ባንገናኝ ሰሞነ ሕማማት ሳናስበው ቢያልፈን እና ከአቅም በላይ በሆነ ሕመም ደዌ በሰሞነ ሕማማት ሥርዓት በጾም በመስገድ መሳተፍ ባንችል በዓለ ሃምሳ ሲወጣ የሰሞነ ሕማማት ጾም በግል ከንስሐ አባታችን ጋር በመነጋገር መጾም ስግደቱንም መስገድ ይገባል ፡፡

የሰኞ በረከት በማክሰኞ አይገኝም የማክሰኞ በረቡዕ አይገኝም የጠዋቱ በማታ አይገኝም ስለዚህ እያንዳንዱ ራሱን የቻለ በረከትና ምሥጢር እንዲሁም ሥርዓት ስላለው ሊያልፈን አይገባም ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ብቻ ከ12ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ

በሱዳን የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ...

ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ሊወያዩ እንደሚችሉ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት...

የኢራን ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ የዓለም ምጣኔ ኃብት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አይኤምኤፍ አስጠነቀቀ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው የኢራን...

የመምህር ዘላለም ወንድሙ (ወልደ ሰማዕት) የ፵ ቀን መታሰቢያ ጥሪ

​"የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው!" (ምሳሌ ፲፥፯)​በሕይወትና በቃል ትምህርታቸው ብዙዎችን...