ነቢዩ ሲራክ
የብልጽግና ስህተት የታማኞች ሹመት…
የግል ሥራ ጉዳይ እግር ጥሎኝ ላለፉት ሁለት ወራት ወደ ሸገር ሱሉልታ ማዘጋጃ ቤት ደጋግሜ እየተመላለስኩ ነው። ጉዳየን ስከታተል በሩቅ የምሰማ በሩቅ የማየውን ደረቅ ሐቅና እጅግ አስከፊ የሆነውን የቢሮክራሲውን እንግልትን ቀምሻለሁ። እስከ ትናንት በዘለቀው የሸገር ሱሉልታ ጉዳዬ የተረዳሁት በዘር አገልግሎት አድልኦ ይሰጣል ከሚባለው ግልጋሎት ይልቅ ብልጽግና ፖርቲ ያለበቂ እውቀት እና ልምድ በታማኝነት የሚሾሙት ባለሥልጣናት የነዋሪውን ሰቆቃ ያከፉት ስለ መሆኑ ተረድቻለሁ።
እውነት ነው ባለ መብት እና ሕጋዊ ሆኜ እያለ በሸገር ሱሉልታ ማዘጋጃ ቤቱ ዙሪያ በተኮለኮሉት ጉዳይ ገዳዮች ጉዳየን አለማስፈጸሙ እንግልቴን አብዝቶታል። ከማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎችና ከበላይ ሰራተኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው ደላላ ወይም በአዲሱ አጠራር በጉዳይ ገዳዮች ጉዳየን አለማስጨረሴ ሥራየን ጎድቶታል። ግን ተጎድቼም በመብቴ ተጠቅሜ ጉዳየን በሕግ አግባብ ሕግን ተከትዬ ጉዳየን መጨረሱን መርጫለሁ …
የሱሉልታ ቢሮክራሲና የጉዳይ ገዳይ ግብግብ …
ያን ሰሞን ሱሉልታ ወደ ሸገር ስትጠቃለል ሥም መቀየሩ ለጀመርኩት ጉዳዬ መጓተት ምክንያት መሆኑ አልጠፋኝም። እኔም ጉዳይ ለማስፈጸም የቢሮክራሲው ጫናና ምልልሱ ታከተኝና “ወደ ሸገር ሥም መቀየሩን ስትጨርሱ አሳውቁኝ” ብየ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። ከትናንት በስቲያ ሌላ የቆየ ጉዳይና ተጨማሪ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ ሸገሯ ሱሉልታ መሬት አስተዳደር አመራሁ። ለፋይል ማስወጫ ግልጋሎት በባንክ 600 ክፈል ተብዬ ከፈልኩ። የከፈልኩበትን ደረሰኝ ይዥ ፋይሌ እንዲወጣ ታዘዘ። ዳሩ ግን “የመዝገብ ቤቱን ዳታ የያዘው ኮምፒውተር በኦሮምያ ፀረ ሙስና እየተመረመረ ነውና ጠብቅ” ተብየ ሙሉ ቀን ብጠብቅም ፋይሉን ማስወጣቱ አልተሳካልኝም። እንግልቱ ሲበዛብኝ ወደ አንድ ኃላፊ አመልክቼ ፋይሌ እንዲወጣ ቢታዘዝም የተሰጠኝ “ፋይልህ ጠፋ” ምንቴስ የሚል ስንኩል ምላሽ አስገርሞ አስደምሞኛል፡፡ ያም ሆኖ አሁንም ጉዳዬን ራሴ እጨርሳለሁ እንጅ ለጉዳይ ገዳይ ላለመስጠት እልህ ተናንቆኛል … በሸገር ሱሉልታ ጉዳይ ክትትሉን ተስፋ ባለ መቁረጥ እጄን ለጉዳይ ገዳይ ላለመስጠት ከራሴ ጋር ቃል ገብቻለሁ … ነገም ሌላ ቀን ነውና፡፡
“ሽሮ ፈሰስ” መንገድ ሥራ …
ሸገር ሱሉልታ በሚሠራው የአስተዳደር በደል ተበድየ ጉዳዬን ስጠባበቅ ለ12 ዓመት በተጓተተው የጎንደር ቸቸላ ሆስፒታል መንገድ በበልግ ዝናብ ጎርፍ የመጥለቅለቁ ምስል ደርሶኝ ተመለከትኩና አዘንኩ። ፊቴንና ሐሳቤን ከሸገር ነቅየ ወደ ሰሜን ጎንደር የቸቸላ ያላለቀ መንገድ ምስል ቀልቤ ተስቧል… በበልግ ዝናብ የፈራረሰው የቸቸላ መንገድ በመንግሥት ላለፉት 12 ዓመታት ተጀምሮ ያላለቀ አውራ መንገድ ነው። ቸቸላ በጎንደር ትልቁ ሆስፒታል መጠሪያ ነው። የተለያየ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት የሚመጡ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሚመላለሱበት አውራ መንገድ ግን በበጋ አቧራው፣ በበልግና በክረምት ጎርፍ ጭቃው የነዋሪውን ውሎ አዳር አክፎቶታል። ዛሬም የቸቸላ መንገድ በጅምር መቅረት በጎንደር እና በዙሪያው ላሉ ሁሉ ብቸኛ እና ትልቁ የመንግሥት ሆስፒታል በተገልጋዮች ላይ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ ነው። የድንገተኛ አምቡላንስ መኪኖች ጽኑ ታማሚዎችን ይዘው ወደ ቸቸላ ሆስፒታሉ ሲመጡ በመንገዱ መበለሻሸት የሚገጥማቸውን እንግልት ሊሰሙት እንኳ ያማል…
አዎ ሱሉልታ ሸገር ላይ እንደሆነው ብልጽግና ሀገር ሲመራ በእውቀታቸው ሳይሆን በታማኝነት በሚሾማቸው ሹሞቹ ሕዝብ በእጅጉ እየተበደለ ነው። ከትልቁ የጎንደር ከተማ የትንሿ የሱሉልታ ሸገር አስተዳደር የሚሻለው በወራት ቢበዛ በአንድ ዓመት የሚጠናቀቀው መንገድ ጎንደር ላይ 12 ዓመት ፈጅቶ አሁንም አለማለቁ ነው። ጎንደሬ ቢቸገር በጅምር የቀረውን የቸቸላ መንገድ ሲያሸሙረው “እንደ ቸቸላው መንገድ በጅምር ያስቀርህ” እያለ ሕመሙን ይተርትበት ይዟል። እናም ሸገር ላይ ተበድዬ የበደል ቀንበር ስለተጫነው ተገፊ ወገን ከቶ አለማሰብ እና አለማዘን አልተቻለኝም ፤ እንደ ዜጋ ይህን ዝም ብሎ ማለፍም የከበደ ሐጢያት ሆኖብኛል፡፡
ይህን ሁሉ ያስባለኝ “ሽሮ ፈሰስ” በሚል ነዋሪው ሥም የሰጠው የመንገድ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያልነካው የቸቸላው መንገድ በበልጉ ዝናብ እንዳልነበረ አድርጎት መመልከቴ ነው። የተበለሻሸውን መንገድ ምስል ስመለከት ትዝ ያለኝ ማለዳ በእንጦጦ ማርያም አድርጌ ወደ ሸገር ሱሉልታ የመጣሁበት ወለል ያለ ደረጃውን የጠበቀ አስፓልት ነው። ወገን በራሱ ልጆች ደጋግሞ መገፋቱ አመመኝና የሸገር ሱሉልታን የከፋ ቢሮክራሲ በደል ለጊዜው ተውኩት…
በጥቅምት ጥምቀት ሲመጣ
በደልና መከራው የተጫነው ወገን አዋቂ ልጆች ሞልው ተርፈዋል። ልጆቹ ግን ዛሬም እንደ ትናንቱ ከአፍንጫቸው ሥር የራሱ ልጆች በሆኑ ሹሞችና ባለስልጣናት እየተደቆሰ ሰቆቃው የከፋ ሆኗል። ለዚህ ማስታወሻ መነሻ ምክንያት የሆነኝ የበልግ ዝናብ ያጋለጠው የቸቸለና የአዘዞ መንገድ ነው። ጎንደር ላይ ስለ መሠረተ ልማት ስናወሳ መሰረታዊ የሆኑትን ትተን የከተማው ነዋሪ ፍላጎት ማሳካት የተቻለ አይደለም። ከቸቸላ አዘዞ 12 ዓመት የተንቀረፈፈውን “በሽሮ ፈሰስ” መንገድ ሥራ ጀምረን፣ የአንገረብና መገጭን የውሃ ግድብ እና የከተማውን ነዋሪ ፍላጎት ለማሟላት የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች በየፈርጁ ብንቃኝ በአብዛኛው ጅምር እንጅ የተጠናቀቀ መሰረተ ልማት ብዙ አናገኝም።
መስከረም አልፎ በጥቅምት ጥምቀት ሲመጣ ከዋዜማው በፊት ባሉት ሳምንታት ሹሞች “ጥምቀትን በጎንደር” ተብሎ የማስታወቂያ አዋጅ ከበሮ በካድሬዎቻቸው ያስመታሉ። የጥምቀት ሲቃረብ ጉድጓድ የሞላባቸው የገበጣ መጫዎቻ የመሰሉት የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ተመርጠው “በሽሮ ገረፍ” ለብለብ አሸዋ እና ጥቁር ሬንጅ ፈሰስ ይሸፈናሉ። ጽዳቱና ሌላው ሌላው ሥራ ይጀመራል። ነዋሪው ሲያሸሙር “ሽሮ ፈሰስ” የሚለው አስፓልት ሥራ እንደ ርካሹ የቻይና እቃ አምሮ ደምቆ ለሹሞች የቀናት ዲስኩር ማሳመሪያ በላይ ከመሆን በላይ አቅም የላቸውም።
ሀገር በእውቀት ሳይሆን በታማኝ ፖለቲከኞች ሲመራ ጥምቀትን በጎንደር ተብሎ ልማት ትጋቱ በተደሰኮረ ማግስት “አደገ ተመነደገ” ያሉን ከተማ ኢኮኖሚ ደቆ፣ መሠረተ ልማቱ ተጓትቶ ሁሉም ከዳጡ ወደ ማጡ ሲወድቅ ማየት የተለመደ ነው። ትናንትም ሆነ ዛሬ ለ12 ዓመታት አስተዳደር ሹሞች ሲቀያየሩ ሲሳሳቱ ስንመክር ባለመስማማታቸው እነሱ ትክክል ነው ብለው ሰርተው ያሳዩን የመሠረተ ልማት መዳከሙ ነውር ነው። ሰርተው ያሳዩን ወጣቶችን በድርጅት ጠርንፈው ባልተጨበጠ መረጃ እድገት መሻሻልና የኢኮኖሚውን መነቃቃት ነው። ስለ እውነት ስህተትን በተራ የካድሬ ዲስኩር ዘመቻ፣ በአዲስ ፕሮጀክት ሪባን ቆረጣ ድግስ መሸፋፈን እንዴት ይቻላል?!
የጎንደርን ቤተ–መንግሥት እድሳት
ያን ሰሞን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጎንደርን ጎብኝተው ነበር። በጉብኝታቸው በአደጋ ላይ ያለውን የጎንደርን ቤተ-መንግሥት ከተመለከቱ በኋላ እድሳቱን ለማድረግ መደመር መጽሐፋቸው ተሽጦ ሥራው እንዲጀመር ቃል ገብተው ቃል ሰጥተው ተመለሱ። ጠቅላዩ ከተመለሱ በኋላ አብረዋቸው በጉብኝቱ የተሳተፉ እመቤት ወደ ጎንደር ዘልቀው “ቤተ-መንግሥቱን የማስዋብ ሥራ ላስጀምር ነው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተልኬ ነው የመጣሁት” ብለው ብለው የከተማውን የቅርስ ጥበቃ ቢሮውን ከነበረበት የቤተ-መንግሥቱ ግቢ እንዲለቅ አደረጉ። ቀጠሉና ሥራ ለመጀመር ቤተ-መንግሥቱ ለእድሳት ለወራት ይዘጋል እስከሚል ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፍ ሲረማመዱ መረጃው አፈትልኮ ወደ ነዋሪው ጆሮ ደረሰ። የሀገር ሽማግሌ ተዋቅሮ ወደ የከተማው አስተዳደር፣ የከተማው ከንቲባ እና የቅርስና ባሕል መምሪያው የመጡት እመቤት ምን እየሰሩ ነው በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ የተሰማው መረጃ ያስደነግጣል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተልኬ መጣሁ ያሉት እመቤት በቤተ-መንግሥቱ እየተንቀሳቀሱ ቢሮ ሲያስነሱና ሌላም ሥራ ሲያካሂዱ ያለ ምንም ደብዳቤ እና ትዕዛዝ እንደሆነ ታወቀ። በዓለም ዩኔስኮ ተመዝቦ የዓለም ሐብት የሆነውን ታሪካዊ ቦታ ደብዳቤ ያልያዙ እመቤት እንዳሻቸው ለማድረግ ታብየው ሲንቀሳቀሱና የከተማው የብልጽግና ሹሞች ሕጋዊነታቸውን እንኳ አላጣሩም ነበር፡፡ የከተማ ነዋሪ በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ባለሥልጣኖች ቀርቦ ታላላቅ አባቶችና እናቶቻችን ባስረከቡንን ቤተ-መንግሥት ዙሪያ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የቅርስ ጥበቃ መ/ቤትም ሆነ ቱሪዝም ኮሚሽን እውቅና ባልሰጠውና በማያውቀው መንገድ ማስዋብም ሆነ የቅርስ እድሳት መደረግ የለበትም በሚል ሂደቱን ባያስቆሙት የብልጽግና ሹማምንት የሰሩት ስህተት ከፍ ያለ ዋጋ ከማስክፈል ሕዝብ ታድጎታል።
ግዙፉ ዳቦ ቤት በጎንደር ..
ባሳለፍነው የካቲት 2015 ዓ.ም የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ባለቤት ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ እና በሜድሮክ ትብብር በጎንደር ከተማ ተመርቋል። ግዙፉ ዳቦ ቤት ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦና 400 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ሲነገረን ለ150 ነዋሪ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎም ነበር። ይህ ግዙፍ ዳቦ ቤት ገና ማምረት እንደጀመረ ሥራው ተስተጓጉሎ እንደነበር አውቃለሁ። ግዙፉ ዳቦ ፋብሪካ ተመርቆ በከፈተ ማግስት በተራ ጥቃቅን ቴክኒካል ችግር ለወራት ሥራ ከመሥራት ተስተጓጉሎ እንደነበር ሰምተናል። ከወራት በኋላ ችግሩ ተፈትቶ መሥራት ጀመረ ተብሎ ከሰማን መንፈቅ አይደለም ሦስት ወራት በወጉ ሥራ ሳይሰራ በስንዴ አቅርቦትና በተዛማች የምርት አቅርቦት ችግር አዋጭ ሳይሆን አክሳሪ ሆነ ተብሎ ሥራው እንደገና እየተሰነካከለ መሆኑን እየሰማን ነው። በእውቀት ሳይሆን በታማኝነት ሥልጣን እየተቸረ በሚመራ ሀገር ፋብሪካ ተመርቆ በተከፈተ ማግስት በኪሳራ እየተዘጋ ነው መባሉን መስማት ያላሳፈረ ምን ያሳፍራል።
ከዚህ በላይ ያነሳኋቸው ከቸቸላ አዘዞ እስከ ከተማው ሽሮ ፈሰስ አስፓልት መንገድ እና ግዙፉ የወ/ሮ ዝናሽ ዳቦ ቤት መኮላሸት ምክንያቱ የትየለሌ ቢሆንም ክህሎት ያለው ባለሙያ በአመራሩ ላይ ባለመኖሩ ይመስለኛል። በአብዛኛው የመንግሥት አስተዳደር የብልጽግና ፖለቲከኛ ሹሞች ያለ እውቀት በሚያሽከረክሯት ሀገር ጥቂት ያነሳኋቸው ማሳያዎች ያለንበትን አደጋ ለማሳየት ከረዳን ብዬ እንጅ በየመስኩ ያለው ብልሹ አስተዳደር ተነግሮ አያልቅም። በፖለቲካ ታማኝነት ያለ እውቀት ሀገር ሲመራ ትርፉ ውድቀት ነው። ሐቁ የግፍና በደል ቀንበር የጫኑትን ነዋሪ በባዶ ዲስኩር እና ባዶ ቃላት ሊያታልሉት አቅም የላቸውም። ቢሸፍኑት እንኳ ውሎ አድሮ እንደ “ሽሮ ፈሰሱ” ነውረኛ የጥድፊያ ሥራ ለልማት ቀናዒ አለመሆናቸውን ጊዜ ደጉ ያጋልጠዋል።
ለወገኖች ድምጻችን እናሰማ!
በአጠቃላይ ጎንደር በእውቀት የሚያስተዳድራት አላገኘችምና እያደር ከተማዋ እንድትቆረቁዝ፣ ነጋዴው ሰርቶ እንዳያሰራና የወደቀው ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ አዳዲስ መመሪያዎች እየወረዱ ነው። በቅርብ እያየን የሚያመንንና ጽምጽ ሆነን ታግለን መለወጥ የሚቻለንን ጉዳይ ፈንግለን ሕዝብ ሲገፋ እና ሲበደል ዝምታን መርጠናል። በጦርነትና በመልካም አስተዳዳሪዎች የጫና ቀንበር ተጭኖት ወገቡ የጎበጠ ወገን ባለበት ሀገር የመገፋት ሐቅ እውነቱን ነጋሪ ድምጽ እንኳ የሚያሰማለት አጥቷል። ጥቂት የማይባሉ አዋቂ ምሁራን ተብየዎች ከሹም ባለሥልጣኖች ጋር ገጥመው ከአፈ ቀላጤ ባልተናነሰ መልኩ በአድርባይነት እየተሞዳሞዱ በሆዳምነቱ ገፍተውበታል። አወቅን ባዮች ከአፍንጫችን ሥር ያለው ወገን በራሱ ሹሞች እየተበደለ መሐል አዲስ አበባ ስላለው ፖለቲካ ተንታኞች ሆነናል። በቅርብ እያየን የሚያመንንና ድምጽ ሆነን ታግለን መለወጥ የሚቻለንን ጉዳይ ፈንግለን ሕዝብ ሲገፋ እና ሲበደል ዝምታን መርጠናል። መጥኔ ለእኛ ከማለት ባለፈ የምለው የለም፡፡
ጎንደርንም ሆነ የቀረውን ተገፊ ወገን የደመቀ የቀደመ ታሪክ ዝናውን ስበን በፎቶ እያስደገፍን “እናትዋ፣ እምየ…” እያልን ዘወትር ከመደለቅ አቅላችን ገታ አድርገን በከፋ አስተዳደር በደል ስለተደናቀፈው የወገናችን መሠረተ ልማት ድምጽ እንሁነው። የምንኮራበት ባሕል እና ቅርስ በመፍረስ አደጋ ላይ ነውና እንጠብቀው፣ አስተባብረን እናሳድሰው። የቀደሙት የሠሯቸውን ፎቶ እያነሳንና በኩሸት ታይታ ሥራ ተቆርቋሪ መስለን በመታበይ ራሳችን አናታልል። ከኑሮ ውድነቱ በላይ ከዲስኩር ባለፈ በማይሰሩ ልጆቹ ሰቆቃው ከበዛበት ከሚገፋው ነዋሪ ጎን እንሁን።
ማኅበራዊ ሕይወቱን የሚለውጥ የረባ መሠረተ ልማት ግንባታ ላልተገነባለት ወገን ድምጻችን እናሰማ ዘንድ ግድ ይለናል!
ይቀጥላል …
