ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ እና ፕሮፌሰር ወርቅአበባ አበበ ላለፉት 25 ዓመታት በትዳር አብረው ኖረዋል። ጥንዶቹ የተዋወቁት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ ነበር። ይህ ትውውቃቸው አድጎ በኋላ ላይ በጋብቻ ተጣመሩ።
በትዳራቸው ስኬታማ የሆኑት ጥንዶቹ በተለይ በልጅ አስተዳደጋቸው ለብዙ ወላጆች ምሳሌ መሆን መቻላቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር ሰለሞን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ሲሆኑ፤ የሬናሰንት የአዕምሮ ሕክምናና ተሃድሶ ማዕከል መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅም ናቸው።
ፕሮፌሰር ወርቅአበባ አበበ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ዲፓርትመንት ሃላፊ እና የሕፃናት ተላላፊ በሽታዎች ሕክምና ስፔሻሊስት ናቸው።
ናሰንት የአዕምሮ ሕክምናና ተሃድሶ ማዕከል በአልኮል እንዲሁም በተለያዩ አደንዛዥ እና አነቃቂ እጾች ሱስ የተጎዱ ሰዎች የሚታከሙበት ነው።
ማዕከሉን እንዲመሰርቱ ምክንያት የሆናቸው የቤተሰባቸው ታሪክ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሰለሞን፤ አያይዘውም ወላጅ አባታቸው ከአልኮል ሱስ ጋር በተያያዘ በገጠማቸው ሕመም ሕይወታቸው ማለፉን ይገልፃሉ።
ታላቅ ወንድማቸውም በተመሳሳይ ችግር በወጣትነቱ እንደተቀጠፈ ያወሱት ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ምክንያት የናሰንት የአዕምሮ ሕክምናና ተሃድሶ ማዕከል መታሰቢያነቱ ለወላጅ አባታቸው እንዲሆን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከተቋቋመ 2 ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከ500 በላይ በሱስ የተያዙ ሰዎች በማዕከሉ ታክመው ወደ ጤንነታቸው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይም በርካታ ወጣቶች በማዕከሉ ከሱስ የማገገም ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ፕሮፌሰር ሰለሞን ተናግረዋል።
