በደቡብ ጎንደር ዞን በይፋግ ንዑስ ፖሊስ ጣቢያ በደረሰ የትራፊክ አደጋ፤ የ7 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
አደጋው የደረሰው 18 ሰዎችን አሳፍሮ ከጎንደር ወደ ባህር ዳር የሚጓዝ አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ፤ ልዩ ቦታው አምባርጌ ዘይት ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቆመ ኤፍ ኤስ አር የጭነት መኪና ጋር ተጋጭቶ በመገልበጡ ነው ተብሏል።
በአደጋውም አሽከርካሪውን ጨምሮ የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፤ የይፋግ ንዑስ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያ ዋና ሳጅን ያለው ሞላ ተናግረዋል።
በተጨማሪም 7 ከባድ እና 4 ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር አዲስ ዘመን ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
አደጋው የደረሰው ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑን ያነሱት ዋና ሳጅን ያለው፤ “አሽከርካሪዎች ሕግና ስርዓትን አክብረው በማሽከርከር በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ መከላከል ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
(አሐዱ ሬድዮ)
