በአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ላይ የወጣው የመለያ ኮድ ለተጨማሪ መገለልና የደህንነት ስጋት የሚያጋልጥ ነው የተባለ ሲሆን፤ አዋጁም ሲጸድቅ እኛን ያማከረ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአሐዱ ተናግረዋል።
የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 በፌደራል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር መጽደቁ ይታወሳል።
መመሪያው ከዚህ ቀደም የክልልሎችን እና የከተማዎችን ሥም ይዞ ይታተም የነበርውን ሰሌዳ የሚያስቀር አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ አዲሱ ሰሌዳ የተሽከርካሪውን እና የአሽከርካሪውን (የባለንብረቱን) መረጃ የያዘ “ቺብስ” የተገጠመለት እንደሚሆን ተነግሯል።
መመሪያው የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ራሱን የቻለ መለያ እንዲኖረው እንደሚደረግም ተመላክቷል።
በዚህ አዋጅ ላይ ለአብነትም አንቀጽ 2 (10) “የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ማለት ለአካል ጉዳተኞች ብቻ የተፈቀደና ከሌሎች ተሽከርካሪዎች የሚለይበት ልዩ ምልክት የሚደረግበት ተሽከርካሪ ነው” ይላል።
በአንቀጽ 5 (15) እንደሚያሳየው ደግሞ፤ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ነጭ መደብ ከጥቁር ፊደላትና ቁጥሮች ጋር የያዘ ሆኖ፤ ከተሽከርካሪው አካል ላይ ከፊት እና ከኋላ የዊልቸር ምልክት፣ “PD” የሚል የላቲን እና የአካል ጉዳተኞች (አጉ) የሚል የግዕዝ ምሕፃረ-ቃላትን ይዞ መደቡ ነጭ፣ ጽሑፉ ጥቁር ቀለም የሆነ ስቲከር እንዲለጥፉ የሚል ያካተተ ነው።
በዚህ አዋጅ ላይ ቅሬታቸውን ለአሐዱ የገለጹት የአካል ጉዳተኞች፤ “አዋጁ ሲጸድቅ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻችን በኩል ምክክር ሳይደረግበት ነው የጸደቀው” ብለዋል።
በተጨማሪ “በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ አካታችነትን ለመተግበር የሚወስን ረቂቅ ተቀብላ ፈርማለች” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ነገር ግን በትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ይሁንታ የፀደቀው አዋጅ በመኪናው ላይ ከፊትና ከኋላ የሚለጠፈው የዊልቸር ምልክት ለእግር አካል ጉዳተኞች ነው እንጂ ሌሎችን የሚወክል አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት አሁንም ቢሆን የሚመለከታቸውን የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በመሰብሰብ፤ ምክክር በማድረግ ማሻሻያ እንዲያደርግም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠይቀዋል።
አሐዱም ቅሬታውን በመቀበል ለተጨማሪ መረጃ ለፌደራል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ምላሽ ማግኘት አልቻለም። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ከተቋሙ ምላሽ የሚገኝ ከሆነ በዘገባ ሽፏን የምንመለስ ይሆናል።
ከአሐዱ ራዲዮ
