የደብብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወርቅ ማእድን ላይ የሚስተዋለው ህገወጥነት ፈተና እንደሆነበት ተገልጿል።
የ ክልሉ ማእድን እና ኢነርጂ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ገ/ማርያም ሰጠኝ ክልሉ ያለዉን የወርቅ ሀብት አዉጥቶ ለመጠቀም የህገወጥ ዝዉዉሩ ጫና እንደፈጠረበት ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ክልሉ እያመረተ በሚገኘዉ የወርቅ መጠን ላይ መሻሻሎች እንዳሉ ቢገለፅም ህገወጥ ዝዉዉር እና ንግዱ እያደረሰ ያለዉ ተፅእኖ ከፍ ያለ ሆኗል ብለዋል።
ክልሉ አሁን ላይ በርካታ የማእድን ሀብት ቢኖረዉም አዉጥቶ መጠቀም የቻለዉ ወርቅ እና የከሰል ድንጋይ ብቻ ነዉ ተብሏል።
በክልሉ የፀጥታ ሀይል እና አድማ በታኝ ሃይል ዝዉዉሩን ለመቀነስ ቁጥጥር እያደረገ ቢገኝም በተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ወርቁ ከሀገር እየወጣ እንደሚገኝ ነዉ የነገሩን።
ህጋዊ ፍቃድ ያልተሰጣቸዉ በብዛት የወርቅ ዝዉዉሩ ላይ እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች እንዳሉ ከማህበረሰቡ ጋር በመወያየት ለማወቅ ችለናል ብለዋል ዳይሬክተሩ
ወርቅ የሚወጣባቸው አካባቢዎች ህገወጦች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት ከመሆኑ አንፃር በቁጥጥር ብቻ ዝዉዉሩን መከላከል አልተቻለም ተብሏል።
በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ልዩ አነስተኛ እና ባህላዊ የወርቅ አዉጪዎች ፍቃድ በመስጠት ወደ ስራ እያስገባ መሆኑን ክልሉ ገልፆል።
በባለፉት ዘጠኝ ወራት 60 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዉ መግባታቸዉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ፍቃድ ያላቸዉ 15 ያህል ወርቅ አቅራቢዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
