የሩሲያ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት በመላው ዩክሬን ቢያንስ 13 ሰዎችን የገደለ ሲሆን፥ ዘጠኙ በዲኒፕሮ እንዲሁም አራቱ በዋና ከተማዋ ኪቭ መሆናቸው ተገልጿል።
ይህም በቅርብ ወራት ውስጥ ሞስኮ ከሰነዘረቻቸው ትላልቅ ጥቃቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
በሌሊት በተፈጸመው የአየር ጥቃት የመኖሪያ ህንፃዎች የተመቱ ሲሆን፥ በርካታ ህጻናትን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።
በዚ ሰአት በኪቭ ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረዋል ተብሎ የሚታሰቡ ሰዎችን ለማግኘት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በከፍተኛ ፍጥነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ ቀደም ሲል ዩክሬን ላደረሰችው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ መሆኑን ገልጾ፥ የጥቃቱ ዓላማዎች በሙሉ መሳካታቸውን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ኪቭ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለው የምስራቅ ዩክሬን ክፍል በሚገኝ የተማሪዎች መኝታ ህንፃ ላይ ለፈጸመችው ገዳይ ጥቃት ሞስኮ ባለፈው ሳምንት ‹‹ስልታዊ ጥቃቶችን›› እንደምትሰነዝር አስጠንቅቃ ነበር፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር ‹‹መጠነ-ሰፊ ጥቃት›› ሊሰነዘር እንደሚችል አስጠንቅቀው የነበረ ሲሆን፤ነዋሪዎች ለአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
ማክሰኞ ጠዋት ዘለንስኪ እንደተናገሩት፥ ሩሲያ በሌሊቱ ጥቃት 6መቶ56 የጥቃት ድሮኖችን እና 73 የተለያዩ የሚሳኤል አይነቶችን (ባሊስቲክ፣ ክሩዝ እና ፀረ-መርከብ ሚሳኤሎችን) ተጠቅማለች።
