ግዮን መጽሔት :- የኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ፣ በተለይም ነጻው ፕሬስ፣ ዛሬ ላይ በሕይወት ሳይሆን በሞት አፋፍ ላይ የሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ ይኽ ጆሮን ጭው ሊያደርግ የሚገባ፣ በትውልድ የንባብና የሥነ ጽሑፍ ተስፋ ላይ እንደ ድማሚት የፈነዳ ክፉ መርዶ ነው፡፡
ይኽ የሐሳብ፣ የፍልስፍና እና የሥርዓታዊ ጽሕፈት ዕድገት በሚገዳቸው ዜጎች አእምሮ ላይ የተወነጨፈ መርዶ፣ ሀገርንና ትውልድን የመስበር አቅም እንዳለው መረዳት የቻለ የመንግሥት አካል አለመኖሩ ደግሞ አስደንጋጭ ነው፡፡
መጽሔታችን ግዮን እንዲህ ባለው እጅግ ከባድና ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ አልፋ፣ ስምንተኛ ዓመቷን ደፍና 230ኛ ዕትሟን ወደ እናንተ ውድ አንባቢዎቿ ቀርባለች፡፡
ግዮን በነጻው ፕሬስ ውስጥ ረጅም ልምድ ባላቸው ጋዜጠኞች የምትሰናዳ፣ ባለፉት ከሩብ ክፍለ ዘመን ለሚልቁ ዓመታትም እንደ ዕንቁ፣ ሐምራዊና ሐበሻ ሪቪው ባሉ የሕትመት ውጤቶች የታሸች የጽናት ተምሳሌት ናት፡፡
ከየካቲት 2010 ዓ.ም ወዲህ ‹‹ግዮን›› እና ‹‹ኢትዮ ሐበሻ›› በሚሉ ስሞች ደግሞ፣ ነባሩን የነጻ ፕሬስ ኃላፊነት ለመወጣት ስትታትር ቆይታለች፡፡
ኾኖም በኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ ላይ የተደቀነው የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ግዮንን ጨምሮ ሁሉም የፕሬስ ውጤቶች ዛሬ ለደረሱበት የሞት አፋፍ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ብቻ የወረቀትና የማተሚያ ግብዓቶች ዋጋ ከሚገመተው በላይ በሦስት ዕጥፍ በመጨመሩ፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ከገበያ ውጪ ኾነዋል፡፡
ይህ የዋጋ ንረት በገበያው ውስጥ ‹‹የጨውና የበርበሬ ነጋዴዎች›› በሚባሉ ጥቂት ግለሰቦች ሞኖፖሊ የተያዘ በመሆኑ፣ ዘርፉ አብዮት የማይመልሰው ውድቀት ውስጥ እንዲዘፈቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ ውስጥ ያለው የሕግ ከለላና የመዋቅር ድጋፍ ማጣትም ሌላኛው የነጻው ፕሬስ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ምንም እንኳ የብዙኃን መገናኛ ሕጉ አንዳንድ በጎ የሚባሉ አሠራሮች በዐዋጅ ቢኖሩትም፣ የሕትመት ውጤቶች ያለ ምንም መንግሥታዊ ፖሊሲና የሕግ ከለላ ብቻቸውን እንዲጋፈጡ በመደረጉ አቅማቸው በእጅጉ እንዲዝል ሆኗል፡፡
በተለይም የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያው ከመንግሥታዊ ተቋማት ፍትሐዊ የሆነ ማስታወቂያ እንዲያገኝ አሠራሩን በማሳለጥ ረገድ ተጥሎበት የነበረው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የመንግሥት መዋቅሩ ዛሬም ነጻ የሕትመት ውጤቶች ማበብ በሚያቃዣቸውና በሚያባንናቸው ግለሰቦች የተጠለፈ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አወሳስቦታል። እነዚህ ወገኖች ለጉዳዩ ዋጋ ከመስጠት ይልቅ፣ ስልታዊ በሆነ መንገድ ዘርፉን ለማዳከም ተባባሪ የሆኑ ይመስላል።
ሃይ ባይ በሌለው የበይነ መረብ የሚዲያ ማዕበል በተጥለቀለቅንበት በዚህ ዘመን፣ ሥርዓት ባለው የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚመራን የሕትመት ዘርፍ ከገበያ ማስወጣት ምን የተለየ ትርፍ እንደሚያስገኝ የሚያውቁት እነዚሁ አካላት ብቻ ናቸው፡፡
ፈጣን የሆነ የአሠራር ሥርዓት ካልተዘረጋለት በስተቀር፣ ዘርፉ ወደ ታሪክነት ላለመቀየሩ አንዳችም ዋስትና የለውም፡፡
በኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ ላይ የተደቀነው ይኽ የመኖርና አለመኖር ፈተና፣ ግዮን መጽሔትን ወደ አዲስ የስትራቴጂ ምዕራፍ እንድትሸጋገር አስገድዷታል፡፡
መጽሔታችን እንዲህ ባሉ የወረቀትና የማተሚያ ግብዓቶች በብዙ ዕጥፍ መወደድ እንዲሁም በሌሎችም ገፋፊ ጫናዎች ውስጥ አልፋ፣ የ230ኛ ዕትሟን ብርሃን ማሳየት መቻሏ ተአምር ሊባል የሚችል ጽናትን ይጠይቃል፡፡
ከፍ ብለን እንደጠቆምነው፣ ባለቤት አልባ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሀገሩን በተቆጣጠረበት በዚህ ዘመን፣ የሕትመት ውጤቶች ብቻቸውን የሕዝብን የመረጃ ጥማት ለማርካት ያላቸው ዕድል እየጠበበ መጥቷል፡፡ በመሆኑም ግዮን በዘርፉ የነበራትን ወርቃማና የማይረሳ ተሳትፎ አጠናክራ እንድትቀጥል፣ ዘመኑ በወለዳቸው የሚዲያ አማራጮች ሁሉ ራሷን ለመከሰት እየሞከረች ነው፡፡
ይህ የዲጂታል አማራጮችን የመጠቀም ውሳኔ፣ መጽሔቷ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያካበተችውን ነባር የነጻ ፕሬስ ኃላፊነትና ሥርዓት ያለው የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ሲኾን፣ ግዮን የጀመረችውን የ230 ዕትሞች ጉዞ ይበልጥ እንድታሰፋም፣ አንባቢያን በዌብሳይትና በሌሎቹም ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻችንን እንዲቀላቀሉና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናችን እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 230 መጋቢት 2018 ዓ.ም
