በ103 አመታቸው ያረፉት የእማሆይ ዋሪት መልዕክት

Date:

ለምታከብሩኝና ለማከብራችሁ፤ ለምትመኩብኝና ለምመካባችሁ ለመርኬና አራዳ ልጆቼ እንዲሁም ወዳጆቼ!

መልዕክቱ ሰፋ ያለና ረጅም ነበር፡፡ በሌላ ጊዜና በሌላ መድረክ እዘረዝረዋለሁ፡፡ ለዛሬው ግን በአጭሩ ወቅታዊውን ”እናታዊ መልዕክቴን” ከመልዕክተኛዬ አድምጡት፡፡

ልጆቼ ሆይ!
ትለፋላችሁ፤ ትደክማላችሁ፡፡ በእኩል ባይሆንም ታፈራላችሁ፤ ታገኛላችሁ! ግና ብዙዎቻችሁ ብኩኖች ሆናችሁብኝ። አጥፊዎች ሆናችሁብኝ። ለፍታችሁ ደክማችሁ፤ ወጥታችሁና ወርዳችሁ፤ በፀሐይ በሀሩሩ ተቃጥላችሁ፤ በዝናብና በብርድ ተኮማትራችሁ ያፈራችሁትን ንብረት ውለታዬን ረስታችሁ ታባክኑታላችሁ። የእኔንም ሆነ የናንተን የታታሪነትና የተደናቂነት ስያሜ ወደ ተቃራኒው በመለወጥ ላይ ትገኛላችሁ። ለምን? ኧረ ለምን?

ልጄ ሆይ!
ጥረህ፤ ግረህ ወጥተህና ወርደህ፤ ምለህ አስምለህና ተገዝተህ በላብህ ባገኘኸው እንጂ በውርስ፣ በቅሚያ፣ ወይም የሰፊውን ሕዝብ ሃብት እንደጥቂቶቹ በስጦታ፣ በጉቦ፣ በሽልማት መልክና በሙስና አልተቀራመትከውም። በዚህ እኮራብሃለሁ!

ታዲያ ያገኘኸውንና የሰጠሁህን ያንተን ስምና የኔንም ዝና በሚያስጠራ መልኩ እንዲሆን ለምን ጠቅመህ አትጠቀምበትም? ያልተማሩ የልጅ ልጆች የሉኝም? የታመሙ፣ የተራቡና የታረዙ እናትና አባት፣ ያልተማሩ ፊደል የናፈቃቸው፣ ንፁህ ውሃ የጠማቸው የባላገር ወገኖች የሉኝም? አደራ የሰጠኋችሁ እኮ ለአንተና ላንቺ ነው። ታዲያ ምን ሆናችሁብኝ?

እናንተ እኮ ከታታሪነት፣ ከጠንካራነትና ከትጉህነት ባሻገር በሁሉም ዘርፍ የስር ነቀል ለውጥ ምንጮች ናችሁ። ለምሳሌ፦ በብልህነታችሁና በአርቆ አስተዋይነታችሁ ያስቀራችሁትን የ”ሠልስት” ሁኔታ ከአገር ውስጥ ተቀባይነትና ተፈፃሚነት አልፎ በአውሮፓና አሜሪካ አድናቆትን በተቸረ ሁኔታ በተመሳሳይ መልኩ አድናቆትና ተቀባይነት አግኝቶ ተከታዮችን አብዝቷል። ታዲያ በሌላውስ?

ልጄ ሆይ!
ተጨንቀህ ያበላሃው ብቻ ሳይሆን ያጎረስከው፤ ያጠጣሃው ብቻ ሳይሆን የጋትከው፤ በሞኝነት መሳቂያና መሳለቂያ ሲያደርግህ ይታያል። በልዩ ሁኔታ ያተኩርብሃል። ይፈርጁሃልም። በአጠቃላይ ለሁሉም ነገር ኢላማ ያደርጉሃል። ታዲያ ብልህነትህ የት ሄደ?

ልጆቼና ወዳጆቼ ተጠንቀቁ። ያለፈው አልፏል። አስተውሉ፤ ምክሬንም ስሙኝ። የትም ብትኖሩ የትም፤ ከአያት-ሰበታ፣ ከአቃቂ-ሱሉልታ፤ ከእንጦጦ-ፒያሳ፣ ከፒያሳ-ቦሌ፣ ከቦሌ- ካራቆሬ፣ ከገፈርሳ-ላፍቶ፣ ልዩነት አላውቅም። የሁሉም እናት ነኝ። የሁሉም ምንጭ ነኝ።

የናንተው መርካቶ፤ ማን እንደ እናት!!
❤❤❤
ከሰሞኑ በ103 አመታቸው ያረፉት እማሆይ ዋሪት “ስሞት የህይወት ታሪክ ተብሎ እንዳይቀርብልኝ፡፡ ይልቁኑም ልጄ (የዋሪት-ዝ መስራች አቶ ለገሰ ዘሪሁን) ካለ እሱ ከሌለም ሌላ ሰው አጭር መልዕክት ብሎ ያቅርብልኝ” ብለው ያስተላለፉትና በስርዓተ-ቀብራቸው ወቅትም በልጃቸው አቶ ለገሰ ዘሪሁን-ዝ አማካይነት የተነበበላቸው መልዕክት ነው፡፡

ስመጥሯ እማሆይ ዋሪት በስርዓተ-ቀብራቸው እለት ሊነበብላቸው የሚችል ሌላ ታሪክ አጥተው ወይም ሳይፈጽሙ ቀርተው አይደለም፡፡ ይልቁኑም ይህ መልዕክት እማሆይ ዋሪት አንድም በወቅቱ የነበረውን፤ ሁለትም አሁን ላይ በግልጽ የሚታየውን የሀብት አባካኝነት በሚገባ የተረዱበትና ይህንንም በ”መርካቶ” አስመስለው የገለጹበት ነው፡፡

ከ18 አመት በፊት ልጃው (የዋሪት-ዝ መስራች አቶ ለገሰ ዘሪሁን) በመርካቶ አብሮ አደጎች ማሕበር ክብረበዓል ወቅት እንደ ንግግር የተጠቀሙት ሲሆን የኋላ ኋላም “ዝክረ መርካቶ”በተሰኘ የማህበሩ መፅሄት ታትሞ ነበር፡፡

አሁን ላይ አንዳንድ ባለህብቶች በዚህ መልኩ ያፈሩትን ጥሪት ምንምና ማንም ረዳት ከሌላቸው ወገኖች ጋር ተካፍሎ በመጠቀም ወይም በማገዝ ፈንታ በለቅሶ፣ በሰርግ፣ በማህበርና በቸግ ዝግጅቶቻቸው ሳይቀር ከልክ ባለፈ መጠን ሲያባክኑት ሲታይ ይህን መልዕክት ”ጊዜውን ቀድሞ የተረዳና የተነበየ መልዕክት” ያስብለዋል፡፡ አንዳንዴ መልካም ስም ከመቃብር በላይ የሚውለው በመልካም ንግግርም ነው!

ነፍስ ይማር!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ግዮን መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 9 2019 ዓ.ም ገበያ ላይ ውሏል !!!

-የግዮን እንግዳ አምዳችን :- ‹‹ምንጩና ጸሐፊው በማይታወቅ መረጃ መመራት አደገኛ...

ሸኽ መሃመድ አል አሙዲ ተጨማሪ 40 ሺህ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ አቅጣጫ ሰጡ

የMIDROC Investment Group ሊቀመንበር ሼክ መሃመድ ሁሴን አል...

የወርቅ ማዕድን ሠራተኛው ከመገደላቸው በፊት ቤተሰባቸው ከታጣቂዎች ጋር ያደረገው የመጨረሻው የስልክ ምልልስ

ማስጠንቀቂያ፡ ቀጥሎ የሚያነብቡት ታሪክ ሊረብሽዎት ይችላል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ...