አምነስቲ ኢንተርናሽናል በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎች በፀጥታ ኃይሎች “በዘፈቀደ እየተያዙ ነው” ሲል ገለጸ።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ጽህፈት ቤት በተለይ ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ፤ የጤና ባለሙያዎች ላይ የተወሰደው “እርምጃ” ብቸኛው ክስተት ሳይሆን “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ዒላማ ማድረግን ጨምሮ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃ ሰፊ አካል ነው” ብሏል።
አምነስቲ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናታን ዳኛው ግንቦት 4 ቀን 2017 ተይዘው እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ከማህበሩ የደረሰው መረጃ እንደሚያመላክት ገልጿል።
ድርጅቱ “የጤና ባለሙያዎች የሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ባለሥልጣናት እያደረሱባቸው ያለውን ማንገላታት እንዲያስቆሙ” እና “ዮናታን እና ሌሎች በዘፈቀደ የታሰሩ ሁሉንም የህክምና ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ” ጥሪ አቅርቧል።
አምነስቲ በመግለጫው የጤና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት “የከፊል ሰላማዊ አድማ” በማድረግ የተሻለ ደመወዝ እና የሥራ ሁኔታ እንዲኖር በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ገልጿል። ባለሥልጣናቱ “የጤና ባለሙያዎችን በሰላማዊ አድማ ላይ የመሳተፍ መብትን እንዲያከብሩ” እና ሕግ አስከባሪ አካላት “ለተቃዋሚዎች ክብር እንዲሰጡ፣ እንዲያመቻቹ እና ጥበቃ እንዲሰጧቸው” አሳስቧል።
አምነስቲ ይህን ያለው የጤና ባለሙያዎች ለሶስተኛ ቀን በከፊል በሀገር አቀፍ ስራ ማቆም አድማ እያደረጉ ባሉበት ወቅት እየተፈጸመባቸው ያለው እስር መቀጠሉን ተከትሎ ነው።
ማክሰኞ እለት የተጀመረው ከፊል ስራ የማቆም አድማ፤ ፍትሃዊ ደመወዝ ክፍያና የተሻሉ ጥቅማ ጥቅሞች እንፈጸምላቸው የሚጠይቅ የተቀናጀ እንቅስቃሴ አካል ነው።
ይህን ተከትሎ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎች ላይ እስር እየተፈጸመ መሆኑን ባለሙያዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ለአብነትም በሲዳማ ክልል በለኩ ከተማ የለኩ አጠቃላይ ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ደረጀ ትናንት ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ/ም በጸጥታ አካላት መያዛቸውን የቤተሰብ አካል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
ትናንት 8 ሰዓት አካባቢ ቀዶ ጥገና አከናውኖ ሆስፒታሉ ውስጥ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከገባ በኋላ 11 ሰዓት ሲሆን “የታጠቁ አካላት ይዘውት እንደሄዱ” የቤተሰብ አባሉ አክለው ገልጸዋል።
እስሩ የተፈጸመ ቀን ማታ 2 ሰዓት ላይ የሚሰራው ቀዶ ጥገና እንዳለ የገለጹት ምንጩ፤ በሆስፒታሉ ብቻኛ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት መሆኑንም ተናግሯል።
አክለውም፤ “ፖሊሶች ከላይ የመጣ ተእዛዝ ነው የምናውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሸ ለቤተሰብ አባሉ እንደተሰጣቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድቷል።
ቀደም ሲል አዲስ ስታንዳርድ፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሁለት ተለማማጆች እና አንድ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግቧል። ምንጩ፤ የአምስተኛ ዓመት ተማሪውና አንደኛው ኢንተርን ማክሰኞ ግንቦት 5 “እራት ለመብላት ሲወጡ መያዛቸውን” ተናግረዋል።
ሌላኛው ተለማማጅ ደግሞ በማግስቱ ትናንት ረቡዕ ጠዋት “የሥራ ቦታውን ለመሸፈን ወደ ሥራ ሲሄድ” በሦስት የፖሊስ መኮንኖች እንደተወሰደ ምንጩ ተናግሯል።
ሶስቱም በአዲሱ ገበያ አካባቢ ወደሚገኘው ላዛሪስት ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውንና “ከማንኛውም ሰው ጋር መገናኘት አይችሉም… እስካሁን የምናውቀው ይህ ነው” ብሏል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ ለአዲስ ስታንዳርድ፤ “የኦርቶፔዲክ ዲፓርትመንት ቺፍ ሬዚደንት ዶክተር ነቢዩ በፀጥታ ኃይሎች ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ታስሯል። በአሁኑ ሰዓት ስላለበት ሁኔታ አናውቅም” ብሏል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል አጠቃላይ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አወል መሐመድ ከሌሎች ዘጠኝ የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ስራ ሲመለሱ ከሆስፒታሉ በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን እና ከሁለት ዶክሮች ውጭ የተቀሩት መለቀቃቸውን ዘገባው አመላክቷል።
አዲስ ስታንዳርድ የጤና ሚኒስቴርን በአካል እና በደብዳቤ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ከአዲስ እስታንደርድ
