ኢምራን ካን ለራሳቸውና ለባለቤታቸው የሕክምና ክትትል እንዲደረግላቸው ጠየቁ

Date:

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን፣ ለራሳቸውና በእስር ላይ ለሚገኙት ባለቤታቸው ቡሽራ ቢቢ ተገቢው የሕክምና ክትትል እንዲደረግላቸው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ።

በሙስና ወንጀል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት ካን፣ ደብዳቤያቸውን ለፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለፌዴራል ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እና ለኢስላማባድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ዳኞች መላካቸውን ጠበቃቸው በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባጋሩት ጽሑፍ አስታውቀዋል።

ካን ከባለቤታቸው ቡሽራ ቢቢ ጋር በሰሜን ምሥራቅ ፓኪስታን በምትገኘው ራዋልፒንዲ ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ቅጣታቸውን እየፈጸሙ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ለዓይን ሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተገልጿል።

ካን በደብዳቤያቸው ከውጭው ዓለም ተነጥለው በቀን እስከ 22 ሰዓታት በብቻ እስር እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል። እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ፣ ጠበቆቻቸውን እንዳያገኙ፣ ለልጆቻቸው በስልክ እንዳይደውሉ፣ መጻሕፍትና ቴሌቪዥን እንዳያገኙ መከልከላቸውን አቤቱታ አቅርበዋል።

“ምንም ዓይነት ልዩ ውለታ አልጠይቅም። የምጠይቀው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዞች እንዲፈጸሙና ለጤና ችግሮቻችን ተገቢው ሕክምና እንዲሰጠን ብቻ ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ጽፈዋል። በተጨማሪም የንጹሕነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት በሕይወት ከቆዩ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ዳኞቹ ጉዳዩን እንዲመለከቱ ተማጽነዋል።

በሌላ በኩል የፓኪስታን መንግሥት ለካን በቂ የሕክምና አገልግሎት አይሰጥም የሚለውን ክስ አስተባብሏል። መንግሥት ካን በሌሎች እስረኞች የማያገኙትን የሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶች እያገኙ እንደሆነ ገልጿል።

የፓርላማ ጉዳዮች ፌዴራል ሚኒስትሩ በኢስላማባድ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ ልዩ ባለሙያ ሐኪሞች ካንን በመደበኛነት እንደሚመረምሯቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም በመጻሕፍት፣ በቴሌቪዥንና በምግብ ላይ ገደብ ተጥሏል የሚለውን ክስ አጣጥለዋል።

ኢምራን ካን ከነሐሴ 2023 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አትሌት ሱሌ ኡቱራ የፍትህ ጥሪ አቀረበች

አትሌት ሱሌ ኡቱራ ያለኝን ሀብት በፍርድ ተዛብቶ ተቀማሁ በማለት...

ከድሬዳዋ እስከ ዱባይ የተዘረጋው የሌብነት ሰንሰለት፤ ተከሳሾቹ እስከ 14 ዓመት ከ4 ወር እስራት ተቀጡ

በድሬዳዋ ከተማ ከመኖሪያ ቤት የተለያዩ ዘመናዊ ሞባይል ስልኮችን በመስረቅ...

ኢትዮጵያ ወረርሽኞችን ቀድሞ የመከላከልና ፈጥኖ የመቆጣጠር አቅሟን እያጎለበተች ነው

ኢትዮጵያ ሀገራዊ አቅሞችንና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን በማቀናጀት ወረርሽኞችን ቀድሞ...

አረንጓዴ አሻራ በተመድ ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 አዘጋጅነት እንድትመረጥ አስተዋጽኦ ያደረጉት የአረንጓዴ አሻራ...