የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፈ
የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በ2026 የክላይሜት ስካነር የላቀ ተፅዕኖ ሽልማት (Climate Scanner Impact Awards 2026) በምድብ ሦስት፣ “ለተቋማዊ አሠራር መጎልበት ያለ ቁርጠኝነት” በተሰኘው ዘርፍ አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ።
መሥሪያ ቤቱ ሽልማቱን ሊያገኝ የቻለው፣ መንግሥት በአየር ንብረት ጥበቃና ለውጡን ለመከላከል እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በኦዲት ሂደት መረጃ በመሰብሰብ፣ በመተንተንና በማስረጃ በማረጋገጥ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ በመቻሉ መሆኑ ተመልክቷል።
ለዚህ ውጤት መሠረት የሆነው እ.ኤ.አ. ከጁላይ 24 እስከ 26 ቀን 2024 በሩሲያ ፌዴሬሽን የአካውንትስ ቻምበር አዘጋጅነት በኡፋ ከተማ የተካሄደው 4ኛው የብሪክስ አገራት ዋና ኦዲተሮች ጉባኤ ላይ የተደረሰ ስምምነት መሆኑ ተገልጿል።
በጉባኤው የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ፣ ከመድረኩ ጎን ለጎን በወቅቱ የአየር ንብረት ጉዳይ አስተባባሪ ከነበሩት የብራዚል ዋና ኦዲተር ጋር ተወያይተው፣ የመጀመሪያውን የአየር ንብረት ጥበቃ ተነሳሽነት ሰነድ ተቀብለው በሀገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸውም ተጠቅሷል።
በስምምነቱ መሠረት ቡድን በማደራጀት፣ በመምራትና በማስተባበር ግምገማው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መደረጉ ለውጤቱ መመዝገብ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተገልጿል።
