ኢራን በአሜሪካ ወይም በእስራኤል አዲስ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም በግጭቱ ወቅት ከተከናወኑት የበለጠ ሰፊ የሚሳኤል ጥቃቶችን በማንኛውም ሰዓት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኗን አስጠነቀቀች።
የኢራን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሀገሪቱ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አዲስ ጥቃት ከቀደሙት የበለጠ ከባድ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚያስከትል ገልጸዋል።
ኢራን በቀጣይ ግጭት የምትከተለው አካሄድ ከቀደሙት የተለየ ሊሆን እንደሚችል፣ የጥቃቱን ስፋትና የምላሹን አቅጣጫ ለመቀየር ዝግጁ መሆኗንም አሳውቃለች።
ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰማው ኢራን በ«ኦፕሬሽን ትሩ ፕሮሚስ 4» ዘመቻ 28ኛ ዙር የሚሳኤል ጥቃት እንደፈጸመች ከተዘገበ በኋላ ነው። በዘመቻው የቃድር፣ ኢማድና ኸይበር ሸካን የተባሉ ሚሳኤሎች መጠቀማቸው ተገልጿል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) በቀጣይ የሚፈጠር ማንኛውም ወታደራዊ ግጭት የቀድሞውን አካሄድ የግድ እንደማይከተል ፍንጭ ሰጥቷል።
በአካባቢው የሚታየው የወታደራዊ ውጥረት እየጨመረ በመሄዱ፣ ተጨማሪ ግጭት የሚከሰት ከሆነ በክልሉ የሰላምና የደህንነት ሁኔታ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋቶች ተነስተዋል።
