የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በስፖርት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና አካታች የስፖርት አሠራርን ለማጠናከር በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክስ እና በኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል ውይይት ተካሂዷል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሀመድ፣ ስፖርት ለሁሉም የሚለውን መርህ በመከተል ዜጎች ከስፖርት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመንግሥት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ስፖርት የብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ በስፖርት መሠረተ ልማት ላይ እየተሠራ መሆኑን እና ከአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክስ ጋር በትብብር ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። የአፍሪካ የስፖርት ተቋማት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ እንዲያደርጉ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክስ ፕሬዝዳንትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቻርልስ ናያምቤ፣ በአፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎችን በስፖርት ለማሳተፍ ከመንግሥታት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን የሚያስተሳስር የአየር መንገድ ባለቤት መሆኗ በስፔሻል ኦሊምፒክስ ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማስፋፋትና ውጤት ለማምጣት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። ተቋሙ ለኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የገንዘብና የሥልጠና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ግርማ ዘውዱ፣ ውይይቱ በአገሪቱ የተጀመረውን የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች በስፖርት የማሳተፍ ሥራ ለማጠናከርና የገንዘብ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በውይይቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
