የኢፌድሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የብሪክስ ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (NDB) አባል እንድትሆን የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።
በዚህም መሠረት ሀገሪቱ እያንዳንዳቸው 100 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸውን 2,945 አክሲዮኖች በአጠቃላይ በ295 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ዝግጅቷን አጠናቃለች።
ከዚህ ክፍያ ውስጥ 20 በመቶው (58.9 ሚሊዮን ዶላር) ወዲያውኑ የሚከፈል ሲሆን፣ ቀሪው በ13 ዓመታት ከግማሽ ውስጥ በ14 ተከታታይ ክፍያዎች ይፈጸማል።
ይህ አባልነት ኢትዮጵያ አማራጭ የልማት ፈንድ እንድታገኝ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንድታስፋፋና ማክሮ-ኢኮኖሚዋን እንድታረጋጋ ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል።
በተጨማሪም በግብርና፣ በኃይል እና በታዳሽ ኢነርጂ ዘርፎች ለሚከናወኑ የቅድሚያ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ባንኩ አባላቱ በሀገር ውስጥ ምንዛሬ እንዲገበያዩ የሚያበረታታ በመሆኑ፣ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።
