የ130 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ያሏት ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች ቁጥር ከ540 አይበልጥም ሲል የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የሒሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር፤ እነዚህም ሙያተኞችም በውጭ ሀገር የተማሩና ልዩ ሥልጠና የወሰዱ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያ ከ540 የማይበልጡ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች ሲኖራት #ኬንያ ከ65 ሺህ በላይ፣ ሩዋንዳ ከስድስት ሺህ በላይ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ሙያተኞች ቁጥር አናሳ የሆነው ኢንስቲትዩት ባለመቋቋሙ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት የልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል የሒሳብ አያያዝ ኢንስቲትዩት ከሌላቸው ሦስትና አራት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች ሲሉ ለኢፕድ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የሒሣብ ባለሙያዎችን ቁጥር በብዙ እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት የፋይናንስ ሥርዓቱን ጠንካራና ተዓማኒ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
