ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት ኤልሳቤጥን ልትጠይቃ ስትሔድ፣ የሰላምታ ድምጿን በሰማች ጊዜ በሆዷ ያለው የስድሰት ወር ጽንስ አምላኩን አወቀውና በደስታ ዘለለ። በእርሷም መንፈስ ቅዱስ መልቶባት “የጌታዬ እናት ወደኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል” አለች። ከሠላሳ ዘመን በኋላም በዮርዳኖስ ልጇ ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችን አምላክነት መሰከረ፡፡
በነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ የተባለው እርሱ ነበር፡፡ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል 3÷3-6 እንደተነገረውም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ! እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ሁሉ ወጣ፡፡
ዮሐንስ ማለት “እግዚአብሔር ጸጋ ነው” ማለት ነው። በዮርዳኖስ ወንዝ የንስሐ ጥምቀት ሲያምቅም የይሁዳ አገር ሰዎች ሁሉ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር፡፡ በጥፋታቸው ይገስጻቸው፣ በመልካም ምግባርና በልግስና፣ በእውነትና በርትዕ እንዲኖሩ ይነግራቸው ነበር፡፡
በዋናነት ግን ስለጌታችን ይነግራቸው ነበር፡፡ “እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገርግን የጫማውን ጠፍር እንኳን መፍታት የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚበረታ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በውኃ ያጠምቃችኋል” አላቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጣ ቢመለከተው “የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያርቅ የእግዚአብሔር ልጅ” ብሎ መስከረለት፡፡ ጌታችንንም “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፣ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን? ባሪያ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ እንዴት ጌታ ወደ ባሪያው ይመጣል?” አለው።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሷ ከጥምቀት ይልቅ እንኳ ንጹህ ነውና ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ መሔዱ፣ የሚደንቅ ትህትና ነው ይላል፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ኢየሱስም በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ሲጠመቅ ሰማያት ተከፈቱ፣ አብ በደመና መሰከረ፣ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡
የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ክብሩ እጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ ጌታችን ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ሲል በማቴዎስ 11÷9-11 መስክሮለታል፡፡ ራሱን ከዓለም የለየው ፍጹም ባሕታዊ፣ የመናንያን፣ ፈቃደ ስጋን የተዉ ሁሉ ድንቅ ምሣሌ ነው፡፡
ጌታን ለማጥመቅ የተመረጠ ሆኖ ሳለ በበረሀ ይኖር ነበር። ገዳማውያንም ስለክርስቶስ ፍቅር ዓለምን ሁሉ የተው ጸሎታቸው ኃይልን የሚያድርግ ሆነው ሳለ እገዛችንን ይጠይቃሉ፡፡ ገዳማትን እናግዝ፣ በዓታቸውን እናጽና፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391 ወይም አቢሲኒያ ባንክ 141029444
ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957
