ከትግራይ ‹‹ቤተ ክህነት›› ፕሮጀክት ጀርባ ያለው ማን ነው?

Date:

በሓጎስ ፍስሓ ጽዮን ተ/ማርያም (ቀሲስ)

ለትግራይ ከትግራይ ዐሥር ኤጲስ ቆጶሳትን እንሾማለን ከተባለ ትንሽ ቆይቷል። ምን አልባት ብዙ ሰው የሰማው ግን ከሰሞኑ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በሚዲያ ከተነገረ በኋላ ነው። እዚህ ትግራይ የምንገኝ ካህናት እርስ በርሳችን እንዲሁም ከብዙ ምዕመናን ጋር በዚህ ጉዳይ ተነጋግረናል። ሁላችንም በጋራ የጠየቅነው “ለመሆኑ ይህ እራስን ገንጥሎ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፈቃድ ውጭ የሚደረገው ሹመት ለትግራይ ህዝብ የሚያመጣው ጥቅም ምንድር ነው?” የሚል ነው። በተሰራብን ግፍ ቤተሰቦቻችንን በክፉ ጦርነት ላጣን፤ ተምረን እንዳልተማርንና እያለን እንደሌለን ሁነን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ልመና ለወጣን፤ በጦርነቱ ምክንያት አካለ ስንኩል ሁነን የሰው እጅ አይተን እንድንኖር በግፍ ለተፈረደብን የሚደረገው ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ምንድር ነው ፋይዳው?  የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነት ተመስርቶ ያማጣልን ጥቅም ምንድር ነው? ምን ተቀየረ?  ምንስ ተለወጠ? ዓላማውስ ምንድር ነው?

ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስን ቢቢሲ ትግርኛ ኤጲስ ቆጶሳትን ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፈቃድ ውጭ መሾሙ ጥቅሙ ምንድር ነው ብሎ ሲጠይቃቸው እንዲህ ብለው መለሱለት “ለሕዝባችን ደስታ የሕዝባችንን ልብ የሚያረሰርስ ነው”። አይ ጋዜጠኛ ምን ቢበድሉህ ነው እንዲህ ያሳጣሃቸው? እያወቅህ። እሳቸው ምንም እንደሚያውቁ። ከሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳቸው እንኳን የዚህን ጥያቄ መልስ አያውቁትም።

የግንቦት 24ቱን ጨምሮ በየሚድያው ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት በንባብ በየሚድያው የሚያቀርቡትን አንዱንም መግለጫ አልጻፉትም። አላጻፉትም። እረቂቁን እንዲያዩትና ለሚዲያ ከመቅረቡ በፊት ሀሳብ እንዲሰጡበት እንኳን እድል አልተሰጣቸውም። ታድያ ማን ነው እየጻፈ የሚያድላቸው? ማን ነው ከኋላ ሁኖ የሚዘውራቸው? ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፈቃድ ውጭ እንዲሁም ቀኖና ቤተ ክርስትያን እየጣሰ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ የሚወተውተው ማን ነው? የ‹‹መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነት›› የሚባል መሥርቶ የሚዘውረውስ ማን ነው? መሪዎቹና  ዘዋሪዎቹ የተለያየ ዓላማ ያላቸው ሁለት አካላት ናቸው።

አንደኛ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ህወሃት በትግራይ የሚገኝ እያንዳንዱ ቤተ እምነት በሚዲያ እየወጣ አዲስ አበባ ከሚገኘው ማዕከሉ መገንጠሉን እንዲያውጁ አደረገች። ‹‹መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት›› ጽ/ቤት የሚባልም ለኦርቶዶካሳዊት ቤተ ክርስትያን አቋቋመች። የሌሎች ቤተ ዕምነቶች እንዲሁ አጃቢዎች ስለነበሩ ጦርነቱ ቆሞ ጦረኞች ተቃቅፈው ሲሳሳሙ ቤተ ዕምነቶችም ከማዕከላዊ አሰተዳደራቸው ጋር እንደገና ተስማምተው ቀጠሉ። ኦርቶዶካሳዊት ቤተ ክርስትያንን ግን ህወሓት በደንብ ጠርንፋ በመያዝ በፖለቲካ ላልተሳካው ዓላማ ቤተ ክርስትያንን መያዣ አድርጋ ለወደቀው ፖለቲካ ማገገሚያ ለተበታተነው ደጋፊዎቿ መሰብሰብያ እና ለወደፊቱ ፖለቲካዋ መቀስቀሻ አድርገዋለች። ለዚህም ይረዳት ዘንድ አባቶችን ዕለት ዕለት የሚከታተል የሚያወጡትን መግለጫዎች የሚጽፍ ሦስት ብርቱ ካድሬዎች ያሉበት ቡድን አቋቁማለች። ይህ በሓለቃ ጸጋየ የሚመራው የካድሬዎች ቡድን ሀይማኖታዊ ዓላማ ይዘው ህወሃት ተጠቅመው ኦርቶዶካሳዊት ቤተ ክርስትያንን የመበታትን አጀንዳ የሚያራምዱት ተሃድሶ መናፍቃን የሚሰራ ነው።

ሁለተኛ ሀይማኖታዊ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ የሆነው ገፊ ምክንያት ዋናው በትግራይ ለሚገኙ አባቶች ተገንጥለናል ተለይተናል ኤጲስ ቆጶሳትንም አንሾማለን እንዲሉ የሚያደርገው ነው። ተሃድሶ መናፍቃን በመላው ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ከብዙ ስልጠና በኋላ ጠንካራ አደረጃጅት ፈጥረው በ1990ዎች  እጅግ ተጠናክረው በየሰንበት ትምህርት ቤቱ እና በየገዳማቱ ተበተኑ። ነገር ግን እንዳሰቡት ሳይሆን በማኅበረ ቅዱሳን መሪነት ወጣቱ ከየቦታው እየለቀመ አጋለጣቸው። በትግራይ ደብረ ዳሞ ሳይቀር በመግባት መነኮሳትን ለማስኮብለል ሲሞክሩ ደብረ አባይ ተማሪዎችን ሲያግባቡ እና ከእንዳ ማርያም ጀምረው ሰንበት ተማሪዎችን ለመቀሰጥ ሲጥሩ ምንም ማጭበርበር በማይችሉበት መረጃ እየተያዙ ተለቀሙ። የተወሰኑት ሙሉ በሙለ ተመለሱ። ሌሎች ተለይተው ሄዱ። የቀሩት በተለያየ ምክንያት እዚሁ እኛው ቤት ቀርተው ቀሰ በቀስ መስፋፋት ጀመሩ።

እነዚህ በተለያየ ቦታ ተደብቀው የነበሩ መናፍቃን በትግራይ የበለጠ ተጠናክረው እንዲወጡ  ማኅበረ ቅዱሳንን ማሰጠላት። መበተን። ማፈራረስ። ትልቁ ታክቲካቸው አደረጉ። ይህም በትግራይ ተሳካላቸው። በመቀጠል ትግራይ ያለችው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኃይልም ሆነ ጉልበት እንዳታገኝ ከማዕከሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ በመለየት አስተዳደሩን መቆጣጠር ቻሉ። ጦርነቱ ትግራይን አወደመ። ተሐድሶ መናፍቃን ግን ጦርነቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው የሀገረ ስብከቶችን አስተዳደር እስከሚችሉት ድረስ ተቆጣጠሩ። ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ ድርጅት ከትግራይ አጥፍተነዋል አሁን ደግሞ የዘራውን የሸዋን ዕምነትና ተከታዮችን እናጠፋለን›› ብለው በዚያ አሰቃቂ ጦርነት ወቅት ሳይቀር ብቸኛ መጽናኛ ቤታችንን አማናዊት ምስካየ ኅዙናንን አመሷት። ልጆቿን አሳደዱ። የተወሰኑትንም ከቤተ ክርስትያን አባረሩ። “ማርያም አማላጃችን ናት ቅዱሳን ያማልዳሉ” የሚለው የሸዋ ትምህርት ነው እያሉ የሚቃውማቸውን ሁሉ “ሸዋ፣  ማኅበረ ቅዱሳን፣  “ባንዳ”  እያሉ ያሳድዳሉ። “አማላጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” እያሉ በቤተ ክርስትያን  አውደ ምህረት በይፋ ያስተምራሉ። መሰረታዊ የቤት ክርስትያን መጽሃፍትን እየቆነጻጸሉ ወደ ትግርኛ እየተረጎሙ ነው። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በትግራይ ለመቆጣጠር ከቅዱስ ሲኖዶስ ትግራይን ነጥለን የራሳችንን ኤጲስ ቆጶሳትን እንሾማለን ብለው ተነስተዋል። በመቀጠል በአንድ ዓመት ውስጥ የትግራይ ኦርቶዶክስ  ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ይቋቋማል። የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ፓትርያሪክ ይሾማል። እዚህ ላይ “ተዋሕዶ” የሚለው ስም እንደሚቀርም ወስነዋል። “በመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሲኖዶስ አማካኝነት ትግራይ ወደ ጥንቱ እምነቷ ትመለሳለች። የሸዋ ዕምነት ይወገዳል”። ይላሉ። ይህ የጥንት እምነት የሚሉት ቅጥፈት ክርስቶስ አማላጃችን የሚል በወላዲት አምላክ እና በቅዱሳን አማላጅነት የማያምን ጾሞ ጸሎትን የሚጸየፍ ስሙን ብቻ የቀየረ የፕሮስቴንታንት እምነት ነው።

ምንም እንኳን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በትግራይ ለመገንጠልና አስር ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመን በመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሲኖዶስ እናቋቁማለን የሚለው የመሰሪዎቹ የተሃድሶ መናፍቃን ልዩ ፕሮጀችት ቢሆንም ህወሓትን ከወቀሳ፣ ብፁአን አባቶችንም ከተጠያቁነት አያድንም።

ለሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ፤ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ እና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፖለቲካን ሽፋን አድርጎ የሚንቀሳቀሰውንና የቤተ ክርስትያንን መገንጠል ፕሮጀክት ባለቤት የሆነው ተሃድሶ መናፍቃን መሆኑን በተፈለገው መጠን ባይሆንም በተለያየ መንገድ ተነግሮአችኋል.። በቀጣይነት ግን ስንነግራችሁ የነበረውን እየዘረዘርን መናፍቃንንን በስም እየጠቀስን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆነ ሁሉ እውነቱን እንዲያውቅ እንደርጋለን።

አንድ ጥያቂ እንጠይቃችሁ?

ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፈቃድ ውጭ እና ቀኖና ቤተ ክርስትያንን በመጣስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹሞ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የሚባል ሲኖዶስ እናቋቁማለን የምትሉት ለትግራይና ለትግራውያን የሚሰጠው ጥቅም ምንድር ነው? ዛሬ እናንተን ማየት የምንፈልገው ያለአባት ለቀሩ ልጆች እንደወላጅ ስትሆኑ ጧሪ ደጋፊ ልጃቸው አንደወጣ ለቀረባቸው አዛውንት ድጋፍ ስትሆኑ ልጇ ይኑር ይሙት ለማወቅ ተቸግራ ቀኑ ለጨለመባት እናት መፍተሄ ስትፈልጉ ማየት ነው። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እንኳን ስንቱ ትግራዋይ በረሃብ አልቋል። መቼ ነው እንደ ሊቃነ ጳጳሳት  ከፍ ብላችሁ በዓለም መድረክ ተገኝታችሁ መድኃኒና ምግብ የምትፈልጉልን? እኛ ካህናት በርሃብ እያለቅን ነው። ልጆቻችን እንደውጡ ቀርተዋል። ብዙ አብያተ ክርስትያናት በቀዳስያን እጥረት ተዘግተዋል። መቸነው ለእኛና ለቤተ ክርስትያን ማሰብ የምትጀምሩት?

መጪው ግዜ በትግራይ ለምትገኘው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ አስፈሪ ነው።

ለመሾም የተሰለፉትን መነኳሳት እያወቅናቸው ነው። በእርግጠኝነት የምንነግራችሁ አንዳቸውም ቢሆኑ በየትኛውም ትግራይ በምትገኝ አጥብያ ቤተ ክርስትያን ኤጲስ ቆጶሳት ሁነው አይገቡም። ቤተ ክርስትያንን የመናፍቃን መናኸርያ ስታደርጉ የሀገረ ስብከታችሁ አስተዳደር ለተሃድሶ አሳልፋችሁ ስትሰጡ በጦርነት ወስጥ ስለነበርን ብዙ ገፍተን አልነገርናችሁም። አሁንም በየሀገረ ስብከታችሁ የተሾሙላችሁ ተሃድሶ መናፍቃን አዲስ አበባ ከሚገኙ አለቆቻቸው ጋር ተቀናጅተው በየገዳማቱና አድባራቱ ሰዎችን እየመለመሉ ስልጠና እየሰጡ ነው። እናንተም ኤጲስ ቆጶሳት ልትሾሙላቸው ደፋ ቀና እያላችሁ ነው። ጽዋዉ ሞልቷል። ትግራይ ሰላም ይራቅሽ ተብላ የተረገመች ይመስል አሁን ደግሞ ሌላ ጦርነት። አሁን ደግሞ በእናንተ ሊቃነ ጳጳሳት የተቀሰቀሰ ጦርነት። አሁን ደግሞ በሃይማኖት ምክንያት የስንቱ ሰው ደም ይፈስ ይሆን? አንቺ መከረኛ እናት አሁንስ የትኛው ልጅሽ ይሆን እንደወጣ የሚቀረው?

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ ገጽ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ የተኩስ አቁሙ መራዘሙን አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሠረት ከኢራን ጋር የገቡትንየተኩስ...

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈቀደ

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB...

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...