ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለንም!

Date:

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ
አያሌው ከበደ ተሰማ

እንደኔ መረዳት አባ ይባስ ከቤ የመጨረሻ ዘመኑን እንዳዘነ፣ እንዳለቀስና እንደቆዘመ ቁጭቱን አምቆ፣ የሆድ የሆዱን የሚያጫውተው አጥቶ፣ ለርሱ ባዕድ በሆነ ዓለምና አኗኗር ውስጥ ነው ያለፈው፡፡ የመጨረሻ ዓመታቱ የሀዘን፣ የሱባዔና የብቸኝነት ነበሩ፡፡ አሉባልታውንና ሽሙጡን ፍራቻ ከቤ ልቅሶ አይሄድም ፤ ሠርግ አይታደምም ፤ ቤተ ክርስቲያንም አይስምም፡፡

ያልሆኑትን ተብሎና ምንጬ ባልታወቀ አሉባልታ ተመርዞና ተሸማቆ፣ እንዲያም ሲል የሚያገናዝብ አድማጭ አጥቶ የማለፍን ያህል በደል ይኖር ይሆን? የሥራ ባልደረቦቹ፣ ባልንጀሮቹና ከፍ ዝቅ ብሎ አደግድጎ ያገለገላቸው ንጉሠ ነገሥት ሳይቀሩ በግፍ በተገደሉበት ሰዓት የሚያማክረውና የሚያነጋግረው ሁነኛ ወዳጅ አጥቶ ከፈጣሪው ጋር ብቻ እየተነጋገረ ነበር የመጨረሻ ዘመኑን የቋጨው፡፡

ይህንን ጽሑፍ ለአንባቢና ለታሪክ ለማቅረብ ሳስብ ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከዛሬ ነገ የተሻለ ጊዜና የሚያገናዝብ ትውልድ ይመጣ ይሆናል በሚል ሳመነታ ቆየሁ፡፡ ወላጅ እናትና አባታችን በትዳር ሕይወት ከ54 ዓመታት በላይ አብረው ቆይተዋል፡፡ በዚህም የትዳር ዘመናቸው 12 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ስምንት ወንዶችና አራት ሴቶች፡፡ ስድስቱ ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ የቤተሰቡ የበኽር ልጅ ወደርየለሽ ከበደ በተወለደች በ56 ዓመቷ በጤና መታወክ ሕይወቷ ሲያልፍ ሁለቱ እምቦቃቅላዎች ሲሹህና ብዙነህ ግን ብዙም ነፍስ ሳያውቁ በጨቅላ እድሜያቸው ማለፋቸው ሲነገረን አድገናል፡፡

በሕይወት የነበረው የቤተሰባችን ትልቁ ወንድ ልጅ ካሣ ከበደና የኔ ታናሽ እህትና የመንገሻ ክበደ መንትያ ጥሩነሽ ከበደም በተክታታይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ይህንን ማስታወሻ እያረምኩ ባለበት በዚች ሰዓት ደግሞ ታላቅ እህታችንና የቤተሳብችን ሰብሳቢ የነበረችው፣ ባህልና ታሪክ አዋቂዋ እህታችን አሰገደች ከበደ አረፈች፡፡

ወላጅ እናትና አባታችን በአምስቱ የጠላት ወረራ ዘመን ተራርቀው ከመቆየታቸው ባለፈ ለአንድም ቀን ሳይለያዩ እንደተከባበሩና እንደተፋቁሩ ነበር ከዚህ ዓለም የተለዩት፡፡ እኛም ልጆቻቸው በተለያየ የእድሜ እርከን ላይ ብንሆንም ተከባብረንና ከዘመድ ልጆች ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ታጥረን፣ በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥረን፣ የትምህርትን ጥቅምና የሥራን ክቡርነት አውቀን፣ በሃይማኖትና በብርቱ ሥነ ምግባር ታንፀን ነው ያደግነው፡፡

ወላጅ አባታችንን ደጃዝማች ከበደ ተሰማን አንቱ ብለን ፈርተንና አክብረን፣ የእናታችን ፍቅርን ርህራሄ ሳይለየን፣ ባሕላዊ ወጉን ባልለቀቀ ሥነ ሥርዓት ታንፀን ነው ያደግነው፡፡ ዛሬ በሕይወት የሌሉት ወላጆቻችን የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክን የቤተ መንግሥት ወግ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ አስተዳደር ጋር አጣምረው የሚያውቁ፣ በጽኑ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነታቸው የሚታወቁ፣ በሠፈር አድባርነትና በዘመድ አሰባሳቢነት የሚለዩ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡

የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ግብ ለእናት ለአባታችንም ኾነ ለእኛ ለልጆቻቸው እንቆቅልሽ የሆነውን ከ1967 ዓ.ም ማግስት ተወልዶ ከተለያየ አቅጣጫ ሲናፈስ የቆየውን የአሉባልታ ጭቅቅት ማጥራት ይሆናል፡፡


የወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ይዞ በፍርደ ገምደልነት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን በግፍ እስከፈጀበት ጊዜ ድረስ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ከነመፈጠራቸው እንኳን የሚያውቅ አንድም የቤተሰቡ አባል የለም፡፡

እኔ ይህንን አሉባልታ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በ1970 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በትግል በረሃ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ነበር፡፡ ወንድሞቼና እህቶቼ ቀደም ብለው ሰምተውታል፡፡ ወንድማችን አምባሳደር ካሳ ከበደ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዪ ጋዜጦችና የራዲዮ ጣቢያዎች በሰጠው ማብራሪያና ባስተናገዳቸው ቃለ መጠይቆች ለዚህ ምንጭና መዳረሻው ለማይታወቅ አሉባልታ ማስተባበያ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ለጊዜው ጋብ ይልና መልኩን ቀይሮ በሌላ አጋጣሚና ‹‹ታሪክ አዋቂ ነኝ›› በሚሉ የአሉባልታ ጦረኞች በኩል አዲስ መልክ ይዞ ብቅ ይላል፡፡

የተለያዩ ‹‹ታሪክ አዋቂ ነን›› ባይ አሉባልተኞች በምንግዴ ካሰራጯቸው አሉባልታዎች ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡

ባንዳንዶቹ አቀራረብ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‹‹ጦጢት ከምትባል የንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ የቤት ውልድ ደጃዝማች ከበደ የደቀሉት ነው›› የኢዲዩ ራዲዮ ጣቢያ ይህንን መሳፍንታዊ አሉባልታ ያስራጭ ነበር፡፡

ዶክተር በረከተ አብ ሃብተ ሥላሴ ይህንኑ አሉባልታ ሲያጠናክር ‹‹የመርማሪ ኮሚሽን አባል በነበርኩበት ጊዜ አንዳንድ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚኒስትሮች መንግሥቱ ኃይለማርያም የደጃዝማች ከበደ ዲቃላ መሆኑን ነግረውኛል›› ይላል፡፡ አሉባልታውንም አሳማኝ ለማስመሰል ‹‹ሚኒስትሮች ሁሉ ሲታሰሩ ደጃዝማች ተለይተው የቀሩበት ምክንያት የዝምድናው ውጤት ነው›› ይላል፡፡

ተስፋዬ መኮንን የተባለውና ‹‹ይድረስ ለባለታሪኩ›› የሚለው መፅሐፍ ደራሲ የሆነው በበኩሉ በደርግ እሥር ቤት በነበረበት ጊዜ ‹‹አብሮኝ ታስሮ የነበረ›› ያለው አንድ የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት አልጋ አንጣፊ ሰው እንዲህ ብሎ አጫውቶኛል ይላል፡-

‹‹አዛውንቱ እንዳጫወቱኝ ከሆነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱት ወደ 1934 ዓ.ም ላይ በጎጃም ክ/ሀገር ውስጥ ነው፡፡ አባታቸው የአፈንጉሥ ከበደ ተሰማ ወንድም ፊታውራሪ ኃይሉ የተባሉ ሲሆኑ በወቅቱ በጎጃም የነበሩ መሆናቸው ነው። እናታቸውን አስመልክቶ ገና በይፋ ስማቸውን እንኳን ታሪክ ባያውቀውም የሚታወቀው በፊታውራሪ ኃይሉ ቤት ውስጥ ከነበሩ ሠራተኛ ሴት የተወለዱ መሆናቸውን ነው። እናት ኮ/መንግሥቱንም ከመውለዳቸው በፊት በልጃገረድነት የአገልጋይ እናታቸውን እግር ተክተው በዚያው በፊታውራሪ ኃይሉ ቤት ውስጥ በማገልገል ላይ እንዳሉ ነው ከፊታውራሪው ኮ/መንግሥቱን የሚወልዱ።

በዚህን ወቅት ዛሬ የኮ/መንግሥቱ አባት እንደሆኑ የሚቆጠሩት ወታደር ኃይለ ማርያም ወልዴም በአገልጋይነት በዚያው በፊታውራሪ ቤት ውስጥ የነበሩ ጎረምሳ እንደነበሩ ይነገራል። ታዲያ ፊታውራሪ ‹ስም ለመጠበቅ› ሲሉ ይመስላል የኮ/መንግሥቱን እናትና ኃይለማሪያምን ያጋቡና ኃይለማሪያምን በውትድርና መስክ እንዲሰማሩ ያደርጋሉ። በዚሁ መሠረት ኮ/መንግሥቱ ከእናታቸውና ከእንጀራ አባታቸው በጎጃም ትንሽ ከቆዩ በኋላ ወታደር ኃይለማርያም የተመደቡበት የመድፈኛ ጦር ተቀይሮ ወደ ጅማ ሲያመራ ቤተሰቡም ወደዚያው ይሄዳል።›› በማለት ጨርሶ ተሰምቶ የማይታወቅ ውሽት ይደረድራል።

መጀመሪያ ነገር ደጃዝማች ከበደ ተስማ ፊታውራሪ ኃይሉ የሚባሉ ወንድም አልነበራቸውም። ወንድሞቻቸው አዝዥ ጥላዬ ተሰማና አቶ መታፊሪያ ተሰማ ብቻ ናቸው። ፊታውራሪ ኃይሉ የሚባሉትን ምናባዊ ሰው የሚያውቃቸው ዘመድም ሆነ ወዳጅ የለም። ተስፋዬ መኮንንን ከመሰለ ‹‹ነባር ፖለቲከኛ›› እንዲህ ዓይነቱ የፈጠራ ወሬ ሲሰማ ከማዘን በላይ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ካድሬ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ለእሥራት በመዳረጉና መንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ ቂም በመያዙ ስም ለማጉደፍ ብሎ ያለ ምንም ይሉኝታ የደረደረው የፈጠራ ታሪክ ነው።

ለመሆኑ የንጉሠ ነገሥቱ አልጋ አንጣፊ ተብለው የተጠቀሱትስ ማን ይሆኑ? ምናባዊ ሰው ወይስ በሕይወት ያሉ? *(ይድረስ ለባለታሪኩ መጋቢት ወር 1983 በሆላንድ ሀገር ታተመ ገጽ 171 ይመልከቱ)

በነገራችን ላይ የኮሎኔል መንግሥቱ ወላጅ አባትም ሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተወልደዋል የሚሉት በ1933 ዓ.ም ነው። ደጃዝማች ከበደ ተሰማ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ገዥ ሆነው የተሾሙትና ያገለገሉት ከ1938 ጀምሮ እስከ 1942 ዓ.ም ድረስ ነው። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተወለዱ የሚባለው በ1933 ዓ.ም የካቲት ወር ነው።

ይህንን አባታቸው ሃምሳ አለቃ ኃይለ ማርያም ወልዴም ራሳቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ያረጋግጣሉ። የተስፋዬ መኮንን ምናባዊ ሰው ይኽንን ያውቁ ይሆን? (የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ትግላችን ቁጥር 1 መጽሐፍ ገጽ 220 እና እፎይታ መጽሔት ላይ የሰፈረውን የአባታቸው የሃምሳ አለቃ ኃይለ ማርያም ወልዴን ምስክርነት ይመልከቱ)።

አባት የወለዱትንና አምሳያ ልጃቸውን ልጅህ አይደለም ሲባሉ፣ ልጅም ወላጅ አባቴ የሚላቸውን አባቱን አባትህ አይደሉም ሲባል ምንኛ ሲገርማቸው ኖሮ ይሆን? በጥላቻ ላይ ተመስርቶ የሚነዛ የአሉባልታ መርዝ ‹‹ከረከንድ›› እንደሚሉት ዓይነት ባለ ስድስት እግርና ሁለት ራስ ምናባዊ አውሬ ነው።

የኮሎኔል መንግስቱ ወላጅ አባት የሃምሳ አለቃ ኃይለማርያም ወልዴ ለእፎይታ መፅሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይህንኑ አሉባልታ እንዴት እንደሚያዩት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ‹‹የሸዋ ወሬ›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ስለጋብቻቸው፣ ስለልጆቻቸው፣ ስለመንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ‹‹ከእኛ ቤተሰብ ጋር አለ ስለሚባለው ዝምድና›› ተጠይቀው በራሳቸው አንደበት እንዲህ ሲሉ መስክረዋል፡፡

‹‹አባቱስ ምን ይሉ ይሆን?›› በሚል ርዕስ ስር ከአረፈዓይኔ ሐጎስ በእፎይታ መፅሔት 1ኛ ዓመት ቁ 3 ሚያዝያ 1984 በወጣው ጽሑፍ በገጽ 18 ሃምሳ አለቃ ኃይለ ማርያም ወልዴ በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ እንደዚህ ብለው ነበር።

‹‹እኔ የፓይለቶች አዛዥ ለነበረ ኢጣልያዊ ቦይነት ተቀጥሬ ደጃች ውቤ ነበርኩ። ሹምባሽ ሆዬ ልጂቱን ይዞ እዚያው አካባቢ ኖሯል ያረፈው። ለግብር ውሃ ስትወጣ ከኔ ጋር ግጥምጥም እንላለን። ይሄኔ ደንግጣ ወደቤት መመለስ። ያረፈችበት ቤት ሄጄ ባለቤቷን ብጠይቃቸው ‘ኧረ እኔም ጣሳዬ ከጄ ወደቀ፣ የማውቀው ሰው ይመስለኛል’ ብላለች አሉኝ። ተጠርታ ስትመጣ ሆዴ ደነገጠ። ‘የጋሼ ወልደ አማኑኤል ልጅም አይደለሽ ወይ? ያኔ ያጨሁሽ እኔም አልነበርኩ ወይ? ስል ጠየቅኋት።

ከዚያማ ተግባባን። በመጨረሻም ‘ከኔ ጋር ትሆኚ ወይስ ከርሱ ጋር ትሄጃለሽ?’ አልኋት። እኔን መረጠች። አልብሼ ይዣት ገባሁ። ጠላ ጠጅ ተገዛ። ስንዘፍን አደርን። በማግስቱ ሹምባሹ ቡሊሲያ ካራቢኜሪ አምጥቶ አስወሰደን። ሬዚዲንሳ አመለከተ። እርስዋ መሃል ሆነች። እኔና እሱ ግራና ቀኝ እንድንቆም ተደረገ። ዳኛው ምረጪ አላት። ወደኔ ገልበጥ አለች።


ዳኛውም፣ ‘እርሱን ከወደደችውማ በግድ የሚሆን ነገር አይደለምና ሌላ ፈልግ’ ብሎ አሰናበተው። እኔም ልጅቱን ይዤ ጭልጥ አልኩ።
“ልጂቱ ማነው ስሟ?”
“ብዙነሽ ተሰማ።”
“የአቶ ወልደ አማኑኤል ልጅ ነች አላሉኝም ኖሯል?”
“አያቷ ዘንድ ስላደገች ብዙነሽ ወልደ አማኑኤል ነው የምትባል እንጄ ወላጅ አባቷማ አቶ ተሰማ ናቸው።”
“የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ዘመድ ይሆኑ?”
“ኤድያ! እኛ ከነሱ ጋር ምንም ዝምድና የለን። አቶ ተስማ ቡልጌ ናቸው። ጎበዝ የቤተ መንግሥት ግንበኛ።”
“በቅርቡ የወጣ አንድ መጽሐፍ ላይ መንግሥቱ የጦጢት የልጅ ልጅ መሆኑን አንብቤያለሁ። ይህስ እውነት ነው?”
ከት ብለው ሳቁና፣ “ሆሆይ! ጦጢት እኮ ሦስት፣ አራት ባሎች የነበሯት ሀብታም ወይዘሮ ነች። የድሃ ዘር አልነበረችም። ይሄን ተወው፤ ሸዋ ነው የሚያስወራው። ይልቅ የጀመርኩልህን ልጨርስልህ።”
“በጄ!”


“ልጂቱን ይዤ ጭልጥ አላልኩልህም? ወዲያውኑ ይህን ልጅ አረገዘች። የካቲት 1933 መንግሥቱ ተወለደ። ጨርቆስ የቄስ ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶም አባቱ ወደ ጂማ በመዛወራቸው ወደዚያው ሄደ። ወላጅ እናቱ በ1944 አረፉ።››

ወላጅ አባታችን በሕይወት በነበሩበት ጊዜ የዚህ አሉባልታ ምንጭ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እርሳቸውም እንዲህ አሉኝ፡-

‹‹እኔ ከደርግ ጋር ያገናኙኝ አጋጣሚዎች ሁለት ብቻ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛው በአካል ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ በስልክ ነበር። ‹የጦር መሳሪያ ቤቱ ደብቋል› የሚል ነገር ሠሪ በሀሰት አሳብቆብኝ ኖሮ ከቀበሌ ታጣቂዎችና ከጦሩም ክፍል የተውጣጡ ፈታሾች ከቤቴ መጡ፡፡ አላፊውም ሻምበል ይመስለኛል ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ እየገሰገሰ ሄዶ ሳሎን ቤት ምድጃው ላይ የተቀመጠውን የልጄ የአያሌው ከበደን ፎቶግራፍ አንስቶ ሲያበቃ ይኸ ቀንደኛ ኢህአፓ ወዴት ገባ? ሲል ጠየቀኝ፡፡ እኔም አንተ ያለበትን ብትነግረኝ ወረታውን በከፈልኩህ አልኩት፡፡ ሆኖም ፎቶግራፉን ከፍሬሙ ውስጥ አውጥቶ ወሰደ፡፡

እንዲሁ ደግሞ የግርማዊ ጃንሆይ ከብር የተሠራ ምስልም (bust) ከሳሎኑ ምድጃ በላይ ይቀመጥ ስለነበረ ወደ ምስሉ እየጠቆመ ዋናው አድሃሪ ኖትና ይህንን እስካሁን እንዴት እዚህ ያስቀምጣሉ በማለት ከምድጃው ላይ ጎትቶ መሬት ላይ ጣለው፡፡ እኔም ይህን ጊዜ ንድድ አለኝና ‹እኪስህ ወስጥ ያለውም ብር እኮ የጃንሆይ ምስል አለበት አይተኸዋል ወይ?› ስለው ከኪሱ ውስጥ አንድ የብር ኖት አውጥቶ ሲመለከተው እውነትም የጃንሆይ ምስል ያለበት መሆኑን አስታውሶ በራሱ ላይ ሳቀ፡፡

‹‹ከዚያ ቀጥሎም ፍተሻው ወደመኝታ ቤቴ አመራና መኝታ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት የተቀመጠ ፊት ለፊቱ በመስታወት የተሠራ አነስተኛ ቁም ሳጥን ነበር፡፡ እዚያ ውስጥም አንድ ሰደፉ ላይ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነግሥት ዘኢትዮጵያ ስም የተፃፍበት የፊሻሌ ሽጉጥ ነበር፡፡ ይህም ሽጉጥ በማይጨው ጦርነት ጊዜ ለዘመቻ የታጠቅሁትና በወቅቱም ቆስዬ ስለነበር በሽልማት የተሰጠኝ ሆኖ ለማስታወሻነት በጥንቃቄ ያስቀመጥኩት ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ለንግሥት ዘውዲቱ በመታሰቢያነት የተሰጠ የብር ጎራዴና ንግሥቲቱ በአባታቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስም ሙዚየም ተሠርቶ እዚያ እንዲቀመጥ ያዘዙበት የአደራ ደብዳቤም አብሮ ነበር፡፡ በተለይ ይኸኛውን አደራ ለማንም እንደማልሰጥና የሚረከበኝም መንግሥታዊ አካል የፊርማ ደረሰኝ እንዲሰጠኝ አሳስብኩ፡፡ በዚህን ጊዜ ሻምበሉ ይህንን ጉዳይ እዚያው ለኃላፊዎቹ ያስረዳሉ በማለት አብረን ወደ ደርግ ጽሕፈት ቤት እንድንሄድ ጠየቀኝ፡፡

‹‹በዚህም ምክንያት ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ እኔ ከልጄ ከካሳ ከበደ ጋር፣ እነርሱ ደግሞ በወታደር መኪና እያጀቡን ወደ ደርግ ጽሕፈት ቤት ሄድን፡፡ በዚህን ጊዜ ነው አንድ መልኩ ቀላ ያለ የኮሎኔል ማዕረግ ያለው ይመስለኛል ትዕቢት ያዘለ በሚመስል መልክ ‹እርስዎ ከማን ይበልጣሉ? ለምንስ ነው የጦር መሳሪያ አላስረክብም የሚሉት?› በማለት ጠየቀኝ፡፡ እኔም ቀጠል አድርጌ ‹እኔ ከማንም አልበልጥም ታሪክ ግን ከሁላችንም ይበልጣል፡፡ እናንተ ደግሞ አሁን መንግሥት ስለሆናችሁ በአደራ የተረከብኩትን ስትወስዱ በፊርማ ደረሰኝ ሰጥታችሁኝ ልትረከቡኝ ትችላላችሁ› ብዬ መለስኩለት፡፡ በዚህን ጊዜ ወደቀልቡ ተመለሰና ‹እኝህ ሰውዬ የታሪክ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ ባልደረባ ይመደብልዎትና የመታሰቢያ ቤቱን ሥራ ተከታትለው እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል፡፡ ያን ጊዜ ጎራዴው ታሪካዊ ቦታው ይቀመጣል› በማለት አሰናበተኝ፡፡››

ከዚሁ ጋር አያይዘውም ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹በሌላ አጋጣሚ ከደርግ ጋር የሚያገናኘኝ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር ፤ ይሁንና እኔ አልፈቀድኩትም፡፡ የሆነው እንደዚህ ነው፡፡ እኔ የጻፍኩትን ‹የታሪክ ማስታወሻ› መፅሐፍ መብቱን ለወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር ሰጥቼ ነበር፡፡ ከደርግ ሥልጣን ላይ መውጣት በኋላ፣ ድርጅቱ ተወርሶ በስፖርትና ባሕል ሚኒስቴር ሥር እንዲተዳደር ተወስኖ ስለነበር ቀሪ የነበሩትም መጻሕፍት አብረው ተወረሱ፡፡ እኔም በጡረታ ከተገለልኩ ወዲያ የነበሩኝን ቅጂዎች ለዘመድ ወዳጅ በማደልና እንደሠርግ ስጦታም እየፈረምኩ በማከፋፈል ጨረስኩና ለራሴም የሚቀር አንድ ቅጂ እንኳን አጣሁ፡፡ ይህን ጊዜ አንዳንድ ሊጠይቁኝ የሚመጡ የቅርብ ወዳጆቼን ሳማክር ለምን ለደርግ አታመለክትም በማለት አግባቡኝና ማመልከቻ አስገባሁ፡፡ ጥቂት ጊዜ ቆይቶም አንድ ቀን ስልክ ተደወለልኝ፡፡ ደዋይዋ ሴት ስለነበረች ማንነቷን ስጠይቅ ከጓድ ፍቅረ ሥላሴ ቢሮ እንደሆነና፣ ወደዚያው እንድመጣ ቀጠሮ ለመያዝ መሆኑን ገለፀችልኝ፡፡ እኔም ጥቂት አሰብኩበትና ‹ስሞታውንና አሉባልታውን› ፍራቻ ትንሽ ጤንነት ስለማይሰማኝ አይመቸኝም በማለት ጥሪውን ሳልቀበል ቀረሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ደርጎችንም ሆነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን እንደሌላው ሰው ሁሉ በቴሌቪዝን ከማያቸው በስተቀር ምንም የተለየ አጋጣሚም ይሁን ትውውቅ አልነበረኝም፡፡›› ሲሉ አጫውተውኛል፡፡

በመቀጠልም ‹‹እንዲህ ዐይነቱ የወሬ ተላላፊ በሽታ ይሁነኝ ተብሎ የሚረጭ ስለሆነ እግዚአብሔር በቃ ሲልና የሕሊና ወቀሳ ሲታከልበት ከሚገታ በስተቀር በእኔ አቅም የምከላከለው አልሆነም›› በማለት እያዘኑ ነበር የመጨረሻ የሕይወት ዘመናቸውን የገፉት፡፡

እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ከቶ ለምን ይሆን ይህ አሉባልታ እስካሁን ሲንከባለል የቆየው?

ከደጃዝማች ከበደ ተሰማና ከወይዘሮ ይታጠቁ ኪዳኔ የምንወለደው ሁሉ ወንድምነታቸውንና ዝምድናቸዉን የማናውቀው የደርጉ ሊቀ መንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ስለዚህ አሉባልታ ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ ባላውቅም፣ እንዲህ ዓይነቱ አሉባልታ ሲላከክባችው ምን እንደሚሉ ለመረዳት አይችግርም። የአሉባልታውን ምንጭ አባታችው አምሳ አለቃ ኃይለ ማሪያም ወልዴ እንዳጣጣሉት ‹‹የሸዋ ወሬ ነው›› ብሎ ማለፍ ይቻላል። ሆኖም አንዳንድ ተጓዳኝ ሁኔታዎች ይህንን አሉባልታ አላገዙም ብሎ መደምደም ከቶም አይቻልም።

ከነዚህ ምክንያቶች መካከል፡-

አባታችን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነውና በእንዳልካቸው ካቢኔም ውስጥ የግቢ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ እንደቆዩ ይታወቃል። ስለሆነም ሌሎቹ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በግፍ ሲገደሉ እሳቸው እንዴት ተረፉ? የሚል የሴራ ትንተና አሉባልታ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለነገሩ ከእስራትና ከርሸና ከተረፉት ውስጥ እንደራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ የመሰሉ በሥልጣንም ሆነ በንግሥና ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ቅርብ የነበሩና ከእኛ አባት በጣም የላቁ ሰዎችም ነበሩበት።

ወንድማችን ካሣ ከበደ በደርጉ ሥርዓት ውስጥ በሚኒስትርነትና በአምባሳደርነት እንዲሁም የካድሬዎች ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ በቅርበት ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር በመሥራቱና የግምባር ሥጋ ሆኖ ያገለገለበትን ሥርዓት ሲከላከል በመቆየቱ አያሌ ጠላቶችን አፍርቶ እንደነበር ይታወሳል። እርሱም ቢሆን በተለያዩ ጊዜያት ለጦቢያ መፅሔት፣ ለግዮን መፅሔትና በኢሳት ቴሌቪዥንም ጭምር ቀርቦ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ይኽንን አሉባልታ ሲያስተባብል እንደቆየ ይታወቃል።

ሌላው ግምት ደግሞ ከፊውዳላዊ ትምክህት የሚወለድ የሴራ ትንተና ውጤት ነው። ‹‹እንዴት አንድ ማንነቱ የማይታወቅና በመልኩም ሆነ በልደቱ የመሳፍንት መሠረትና አምሳያነት የሌለው ሰው›› አላንዳች መካሪ ለፖለቲካ ሥልጣን በቃ ከሚል በመነሳትም ጭምር የኢድህ ራዲዮ በቀዳሚነት አሉባልታውን ፀያፍ በሆነና የመደብ ማንነትን በሚያናንቅ መንገድ ሲያሰራጭ እንደነበር ይታወቃል። የምንትስ ልጅ ….እንደማለት ዓይነት ነው።

አባታችን በሞት ከዚህ ዓለም ከተለዩ በመጪው ሚያዝያ ወር 40 ዓመት ይሆናቸዋል። እሳቸው እውነተኛው የፍርድ ቦታ ሄደዋል። እራሳቸውን ሊከላከሉ በማይችሉበት ቦታ ናቸው። ሆኖም ስማቸው እንደወሬ ማጣፈጫ አሉባልተኞች በቅመምነት ሲጠቀሙበት ማየቱ ያማል። ያልሆኑትን እንደሆኑ፣ ያላደረጉትን እንዳደረጉ፣ ለርሳቸውም ሆነ ለቤተሰቡ ባዕድ በሆነ ወሬ እንዲሁ ስንታመስ ቆይተናል። የቅርብ ወዳጆቻችን የምንላቸው ሳይቀር ይህ አሉባልታ በተረጨ ቁጥር እንደ አዲስ ሁኔታውን ለማጣራት ይጠይቁናል። ‹‹የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ወንጀል›› ቤተሰቡ በግድ እንዲጋራ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። ቤተሰባችን ኮሎኔል መንግሥቱን የሚያውቃቸው እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በርቀት ነው። በሀገር ላይ አድርሰውታል ለተባለው በደልና በአስተዳደር ዘመናቸው ለፈፀሙት ጥፋት መጠየቅ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። እኔ በሕይወት ዘመኔ አንድም ቀን ኮሎኔል መንግሥቱን አግኝቼም ሆነ አነጋግሬ አላውቅም። እሳቸውም ቢሆኑ ከወንድማችን ከካሳ ከበደ በስተቀር የሚያውቁት የቤተሰብ አባል እንደሌለ በእርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ።

ምነው ታሪክ አዋቂ ነን የሚሉት እንኳን ቢጠነቀቁ? በሕይወት ያለነውንም የቤተሰብ አባላት ቢጠይቁ? እንዲያው በተገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ጨዋታ ለማሳመር በሕይወት የሌለና ራሱን ሊከላከል የማይችልን ሰው ስም በታሪክ ውስጥ መዘነቅ ሊያሳፍርና ሕሊናን ሊቆረቁር ይገባል። አንዳንዴ ይገርመኛል! እኔ የቤተሰቡ አባል የማላውቀውን ሌሎች ያልተወለዱንና አብረውን ያልኖሩ ደፋሮች ወሬ ለማሳመር ብቻ የደረደሯቸውን አሉባልታዎች ለመዘክዘክ ጊዜም ዓላማም የለኝም። እንዲያው ሁልጊዜ ትዝ የሚለኝ አንድ ታሪክ አለ።

ሰውዬው ድንኳን ሰባሪ ነው አሉ። ባልተጠራበት ግብዣ፣ ሠርግምን ይሁን ተዝካር ሲያይ በክራባት ታንቆና የክት ልብሱን ዠቅ አድርጎ ድንኳን እያሰሰ ራሱን የሚጋብዝ ደፋር ነበር አሉ። ታዲያ አንድ ቀን እንዲሁ ደንኳን ተከትሎ ትኩስ ለቅሶ ያለበት ቤት ያይና ወሬውን በቅጡ ሳያጣራ ‹‹አባቴ አባቴ!›› እያለ ይገባል። እንዳጋጣሚ ሆኖ የሞቱት ሴት ነበሩና እደጃፍ ላይ የቆመና ይህንን ሁኔታ ይታዘብ የነበረ አንድ አጋፋሪ ‹‹ኧረ እባክህ የሞተው እኮ ወንድ አይደለም ሴት ናቸው›› ቢለው ድንኳን ሰባሪውም መልስ በኪሱ እንዲሉ ነበርና ‹‹የሞተውማ አረፈ ለቆመው ነው እንጂ ማልቀስ›› ብሎ መለሰ አሉ። እባካችሁ ድንኳን ሰባሪ ከመሆን እንታቀብ!

እውነት በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ልናከብረውና ልንቆምለት የሚገባ ክቡር ሉዓላዊ እሴት ነው። ሰለማንም ሰው ቢሆን ያልሆነውንና ያልተደረገውን ፈጥሮ ማውራት፤ የሚነገረውን ደግሞ ሳናመዛዝንና ማስረጃ ሳንጠይቅ እንዳለ ተቀብለን የገደል ማሚቶ ኾኖ ማስተጋባት እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው። ከፈጣሪያችንም ኾነ ከሕሊና ጋር የሚያጣላ ነው። ያለበቂ ማስረጃ ሰለግለሰቦች የምናስተጋባው አሉባልታና የምንግዴ አነጋገር ውሎ አድሮ ስለ ተለያዩ የሃገሪቱ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጭምር እየተዛመተ ስለመሆኑ በአመዛኙ በሃሰት ትርክት ሳቢያ የምትናጠው ሃገራችን ጉልህ ምስክር ናት። ለእውነት በጽናት እስከቆምን ድረስ ዛሬ መፍትሔ የጠፋው የሚመስለው በመካከላችን ያለው አለመግባባት እንኳን ውሎ አድሮ መፍትሔ አግኝቶ አንድነታችንን መልሰን የመጎናጸፍ ተስፋ ይኖረናል። ስለሆነም እውነት የጊዜያዊ ፖለቲካ ጥቅም ሰለባ እንዳትሆን በጽናት እንቁምላት።

እባካችሁ ለእውነት አክብሮት ይኑረን። ስንናገርም ሆነ ስንጽፍ በእውነት ላይ ብቻ ተመሥርተን ይሁን። እውነት ከሁሉ ትልቃለችና ለእውነት ብቻ እንታመን። የእኔ ምክር ይኸው ነው።

ከአክብሮት ጋር!

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 መጋቢት 20 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...