ተመስገን አበበ የ28 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ነዋሪነቱ በሀዋሳ ከተማ ሲኾን፣ ሁሌም ቢኾን ብሩህ ተስፋ እና ሕልሞችን ሰንቆ ያንን ተግበራዊ ለማድረግ ይተጋል፡፡ ተመስገን የመጀመሪያ ዲግሪውን በማኔጅመንት በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ሙያውን በተግባር ለመተርጎም ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን አከናውኗል፡፡ ወደ ተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቢዝነስ ፕሮፌሽናልነት እና በአሰልጣኝነት ከመሥራት ጀምሮ የተለያዩ የሥልጠና መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፏል።
ተመስገን ሌሎችን ለማበረታታት እና ለመርዳት ባለው ውስጣዊ ፍላጎት የተነሣ ተገቢውን ሥልጠና የማግኘት ፍላጎቱን ለማሟላት አጋጣሚዎችን በእጅጉ ይፈልግ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ ታዲያ ስለ ከፍታ ፕሮጀክት ከጓደኞቹ አንደበት አንዳች ነገር ሰማ፡፡ ፕሮጀክቱ ሰፊ ውጤታማ ሥልጠናዎችን በመስጠት መልካም ሥም ማትረፉን የሰማው ተመስገንም ፕሮጀክቱ ውስጥ ታቅፎ ዕድሎቹን ለመሞከር ወሰነ። ወደ ስኬት የሚመራውን ጉዞ ለመጀመር የመጀመሪያ ያደረገው እርምጃ ደግሞ፣ ፕሮጀክቱ በሚያከናውናቸው የሥልጠና መርኃ ግብሮች በፈቃደኝነት አስተባባሪ መኾን ነበር፡፡ ተመስገን በዚህ መልክ ከፍታን ተቀላቀለ።
በዚህ መልኩ ከፍታን የተቀላቀለው ተመስገን በሒደት ያለው ትጋት እና ቁርጠኝነት ዕውቅና ተሰጥቶት በአሰልጣኞች ሥልጠና ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ የሚኾንበት እድል ተሰጠው። እንዲህ ያለው ዕድል ተመስገን ለበርካታ ጊዜያት ሲያልመው ከነበረው ምኞቱ ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ ነበርና፣ በፕሮጀክቱ ውስጥ የሥራ ፈጠራ እና የቢዝነስ ክህሎት አሰልጣኝ ለመኾን አበቃው፡፡
ተመስገን በዚህ ኃላፊነቱ የገዛ የሥራ ምግባሩን ከማላቅ ባለፈ ከሌሎች አሰልጣኞች ጋር በመተባበር እና ከወጣቶች ጋር በመተሳሰር የማይናቅ ልምድ የቀመረ ሲኾን፣ ከከፍታ የቡድን አባላትም ትልቅ ትምህርት አግኝቷል።
ተመስገን በዚህ የሥራ ትጋቱ፣ በከፍታ ፕሮጀክት ውስጥ ‹‹የኢኮኖሚ ማጎልበት›› የሚል መጠርያ ካለው የሥራ ዘርፍ መኮንን ጋር ተቀራርቦ በመሥራቱ ትልቅ ጥቅም አግኝቷል። ከዘርፉ መኮንኗ እውቀት እና አመራርን በእጅጉ በመቅሰሙም በሥራ ልምዱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ ረድቶታል። መኮንኗ ከፍታ ውስጥ ከነበረችበት ኃላፊነት ለቃ ስትወጣ በተመስገን ሙያዊ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችላ ነበር። የከፍታ ቡድንም ይኽንን የተመስገንን ትጋት እና ብቃት በመገንዘብ በከፍታ ፕሮጀክት በዩዝ ኤንድ ካልቸራል ፋውንዴሽን (YCDF) የኢኮኖሚ ማጎልበት መኮንን ኾኖ እንዲሰራ ትልቅ እድል ሰጠው።
በአሁኑ ወቅት በተሰጠው ኃላፊነት ተመስገን በዘርፉ መኮንነት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በሥራው በሕብረተሰቡ ውስጥ ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ እድገት እና መብቃት በንቃት አስተዋፅኦ እያደረገም ይገኛል፡፡ ተመስገን የከፍታ ፕሮጄክት ተሳትፎው የሥልጠና ፍላጎቱን እንዲያሳካ ከማስቻሉም በላይ የግል እና ሙያዊ ብቃቱን በማሳለጥ በመረጠው የሥራ ዘርፍ ስኬታማ መንገድ እንዲዘረጋ አስችሎታል ማለት ይቻላል።
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 217 ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም
