እናት ፓርቲ በቅርቡ የተካሄደውን የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጠቃላይ ሂደትና ፍጻሜ በማስመልከት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ሂደቱ “በመርሕና በስክነት የተካሄደ ሳይሆን የእነ አጼ በጉልበቱ ትዕይንት ነው” ሲል በጽኑ ተቃወመ።
ፓርቲው የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ “የይምሰል ምክክር” የሚወጡ ውሳኔዎችን እንዳይቀበል ጥሪ አቅርቧል።
እናት ፓርቲ እንዳመለከተው፣ ኮሚሽኑ ራሱ ላስቀመጣቸው መመሪያዎች አልተገዛም። አብዛኛውን ተሳታፊ የወከለው ገዢው ፓርቲ እንደሆነና ሰፊው ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ በማሳለፉ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሳል ክርክር ሳይደረግ ማለፉን ገልጻል።
በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የአብዛኛው ተመካካሪ ሀሳብ “ከተማዋ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ ትሆናለች” የሚል ቢሆንም፣ ከገዢው ፓርቲ ፍላጎት ጋር ባለመጣጣሙ አዳራሽ ማረበሽ፣ ማስፈራራትና ሂደቱን እስከ አርብ ማራዘም እንግልት መፍጠሩን ፓርቲው ገልጿል።
አዲስ አበባ የነዋሪዎቿና የመላው ኢትዮጵያውያን እንጂ የአንድ ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ልትሆን አትችልም ብሏል።
ኮሚሽኑ በስራ መመሪያው ላይ በውሳኔ አሰጣጥ ወቅት 75% ድጋፍ (Consensus) ማግኘት ያስፈልጋል ብሎ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ ያ ሳይፈጸም በዝምታና በጭብጨባ “ስምምነት ተደረሰበት” ተብሎ የተላለፉት ውሳኔዎች በሙሉ ህጋዊነት የላቸውም ሲል እናት ፓርቲ አስታውቋል።
ለምክክሩ ውጤት አልባነትና ለተፈጠረው አዲስ ውጥረት “ጠበብ ሲል የኦሮሚያ ብልጽግና፣ ሰፋ ሲል ደግሞ ገዢው ብልጽግና” ተጠያቂ ናቸው ያለው ፓርቲው፣ ለምክክሩ ውጤት ሙሉ በሙሉ እውቅና እንደማይሰጥ እና ህዝቡም በአመቸው መንገድ ሁሉ እንዲቃወመው ጥሪ አቅርቧል።
የእናት ፓርቲ ሙሉ መግለጫ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከአዲስ አበባ የተሰጠ ነው
